ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይስደቡን! ከፈለጉ….

ክቡር ጠ/ሚኒስትር አይስደቡን! ከፈለጉ….

ተመስገን ደሳለኝ (ከአዲስ አበባ)

የተከበሩ የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ፣ (አንዳንደ አፍቃሪዎችዎ የአፍሪካ መሪ እያሎትም ነው..፣የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ የህወሓት ሊቀመንበር … መለስ ዜናዊ ሆይ ባለፈው ሀሙስ (ጥቅምት 9/2004) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከብዙ የኢህአዴግ አባላት፤ ከአንድ የኢህአዴግ ደጋፊ እና ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪል በቀረበ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡

ይሄ መቼም አንድም የፓርላማ ስርዓት ነው፡፡ ሁለትም እኛ ግብር ከፋዮች እርሶን ጨምሮ ለሁሉም ክቡራን ሚኒስትሮች ደሞዝ የምንከፍልበት የስራ ድርሻ ነውና የፁሁፌ አላማ ..ለምን ማብራሪያ ሰጡ.. የሚል እንዳልሆነ በትህትና ይረዱልኝ ዘንዳ እጠይቃለሁ፡፡

ዛሬ ልፅፍሎት የተነሳሁበት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሀገሬ መኖር ስጋት እና ሰቀቀን ሆኖ ስለተሰማኝ ነው፡፡ ይሄ ስሜት የመጣው ደግሞ እርሶ በፓርላማው ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ (ነገሩ እንኳ ማብራሪያ ሳይሆን ማስፈራሪያ ሊባል የሚችል ነው ..የተነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጠ/ሚኒስትር በተጨማሪም የጦር ሰራዊቱን አዛዥነት ስልጣን የጨበጠ፤ በአናቱም ..አምባገነን.. እያሉ የሚተቹት ተቀናቃኝ ያለው መሪ ከሀገሪቱ ህግ እና ደንብ ውጭ ዜጎችን ያውም የህዝብ አይን እና ጆሮ ናቸው የሚባሉትን ነፃ ጋዜጠኞችን ..ማን የማን አባል..የአሸባሪ ድርጅቶች ለማለት ነው) እንደሆነ እናውቃለን፣ ጋዜጠኞቹም ከማን አመራር እንደሚሰጣቸው እናውቃለን፤ ነገር ግን በምናውቀው ልክ እርምጃ አልወሰድንም፤ በተመረጠ መልኩ እርምጃ ወስደናል፡፡ ይህ እርምጃ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ ነው የሚለው የቁራ ጩኸት ነው፡፡ በዚህ ስራ ለተሰማሩ መልእክቴ ማሰር ብንፈልግ ከበቂ በላይ መረጃ አለን፡፡ ያላወቅን ከመሰላቸው እየተሳሳቱ ነው.. ሲሉ የተናገሩት ማስፈራሪያ እና ዛቻ በእውነቱ እኛን ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ጉዳይ ሆኖ ማለፉን እርሶም የአወቁት ይመስለኛል፡፡

ለምን መሰሎት? ያ ትውልድ (እርሶንም ይጨምራል) የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና ህዝባዊ መንግስት አመጣለሁ በሚል በወታደሮች ከተዋቀረ መንግስት ጋር በፈጠረው ትግል አንድ ትውልድ አልቆአል፤ ወይም ተኮላሽቷል፤ ወይም መክኖአል፡፡ እናም ይህንን ተከትሎ በኢትዮጵያ ..ፖለቲካ እና ኮረንቲ.. በሩቁ የሚል ፍልስፍና ከሙሴ ህግ በላይ ተከታይ እና አክባሪውን ፈጥሮአል፡፡ በእርግጥ እርሶ እና ጓደኞቾ የትጥቅ ትግሉን በአሸናፊነት ተወጥታችሁ የመንግስት ስልጣን ከያዛችሁ በኋላ በሰኔ 1983ቱ ኮንፈረንስ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የታገልነው ዴሞክራሲን ከእውነተኛ ባለቤቷ (ህዝቡ) ጋር ለማገናኘት ነው ማለቶትን ተከትሎ ብዙ ተቃዋሚ ድርጅቶች እና ብዙ ነፃ ሚዲያዎችን ማየት ችለን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? ብዙም እድሜ አልነበረውም እንጂ፡፡ በተለይ የተቃዋሚዎቹ እጣ ፈንታ፡፡ ለሄዋን መሳት ምክንያት እንደሆነ እንደሚነገርለት ..እባብ.. አናት አናቱን እየተባለ እድገቱ እንደ ካሮት ቁልቁል መሆን የጀመረው ገና ዛሬ ሊናድ ነው፣ሊገነደስ ነው፣ ሊወድም ነው፣ጂኒ ቁልቋል…የሚሉት ህግ መንግስት ሳይፀድቅ ነው፡፡ ነፃ ሚዲያው ግን በአንፃራዊ ሁኔታ ካየነው ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ..ሀሳብን በነፃነት ያለገደብ መግለፅ.. ከሚለው ህገ መንግስታዊ መብት አኳያ ከታየ፡፡ ይሄም ቢሆን ግን ከ97ቱ ምርጫ ማግስት እንዲያልፍ አልተፈቀደለትም፡፡ እናም ክቡርነቶ ከ97ቱ ድህረ ምርጫ በኋላ በነፃው ፕሬስ ሰፈር የተፈጠረውን ለእርሶ አልነግሮትም፡፡

የሆነ ሆኖ እኛም ..ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቁ.. በሚባልበት ሀገርና ማህበረሰብ ..ማን እንደ ሀገር….. በሚል በተጨማሪም በወረቀት ላይ የሰፈረውን ህገ-መንግስት በማመን የፖለቲካ ጋዜጣ አዘጋጆች ሆንን፡፡ በዚህም ሊደግፉን እና ሊያበረታቱን ይገባል ብለን ስንጠብቅ፤ እርሶ ግን በግልባጩ ጠረጴዛ እየደበደቡ ይዝቱብናል፡፡ …በቂ ማስረጃ አለን፤ አሸባሪዎች ስለመሆናቸው እያሉም ይፎክሩብናል፤ ጥርስም ይነክሱቡናል፡፡ መቼም ይህ ንግግሮት የእርሶን ፊት እያዩ የሚያድሩ ተቋማት በእኛ ላይ ለጀመሩት የአጥፍቶ መጥፋት ዘመቻ የልብ-ልብ እንደሚሰጣቸው ግልፅ ነው፡፡.. ለነገሩ ይሄ አይነቱ ጫና እንዲፈጠር የእርሶም ፍላጎት ይመስለኛል)

ክቡር ሚኒስትር፡- እውነት ግን ..በቂ ማስረጃ እያለ ነው ያላሰርናችሁ.. ሲሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው? መቼም እኔ በግሌ ፈንጅ ታጥቄ ህዝቤን ለማጋየት እየተንቀሳቀስኩ እያለ መረጃ አግኝተው ለማሰር ስላልፈለኩ ተውኩህ እያሉኝ ከሆነ ጥፋተኛው እኔ ሳልሆን፤ ህዝቦትን ከአሸባሪ ጥቃት ለመከላከል ያልፈለጉት እርሶ ኖት፡፡ አሊያም በምናቀርበው ዘገባ፣ የአይዶሎጂ ትንተና፣ የፖሊሲዎች ትችት ፣ ሙስናን ማጋለጥ… ተበሳጭተው ከሆነም ደግሞ ምንም እኮ ዳር ዳርታ አያስፈልግም፡፡ በቀጥታ ትእዛዝ ሰጥተው ጋዜጣውን ማዘጋት ይችላሉ፡፡

በተቀረ ባልዋልንበት ሜዳ አንዴ አሸባሪ፣ ሌላ ጊዜ ነጭ ለባሽ፣ የሻዕቢያ ተላላኪ እያሉ እኛን፣ ቤተሰቦቻችንን እንዲሁም የጋዜጣው ተከታታዮችን ጭንቀት እና ፍርሃት ውስጥ መክተቱ ዛሬ በህግ ተጠያቂ ባያደርግም፤ ቀን የካደ እለት ግን በህግ እንደሚያስጠይቅ እርሶም አያጡት፡፡ እንደ እድል ሆኖ እንኳን በህግ ባያስጠይቅ እመኑኝ ከመጨረሻው ዳኛ ከታሪክ ተጠያቂነት በምንም መልኩ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ የኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን እጣ እንይ፡፡ ..አንድ ጥይት እና አንድ ሰው….. ሲሉ እምቧ ከረዩ እንዳላሉ ሁሉ በመጨረሻው ሰዓት ሀገር ጥለው ፈረጠጡ፡፡ እናም ለፍርድ ከመቅረብ እና እስር ቤት ከመግባት አመለጡ፡፡ ይሄ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከታሪክ ተጠያቂነት አምልጠዋል እንዴ? ጱረ በጭራሽ.. እኔን ካላመኑ እስቲ ኮለኔሉ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የተፃፉ የታሪክም ሆነ የፖለቲካ መጽሐፍትን ገልበጥ ገልበጥ ያድርጉ፡፡ ስለኮለኔሉ የአፈና አስተዳደር አንድም ሳይቀር ያገኙታል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ለ20 አመት ከታሰሩበት ወህኒ ቤት በምህረት የተለቀቁት የኮለኔሉ መንግስት ባለስልጣናት እንኳ ምህረት ያገኙት ፍርድ ቤቱ ከጣለባቸው ቅጣት እንጂ ከታሪክ አይደለም፡፡ እናም የታሪክ ተጠያቂነትን በምህረት ወይም በሽሽት ከቶ ማንም ሊያመልጠው አይችልም፡፡ እርሶም ቢሆኑ፡፡

የሆነ ሆኖ ከላይ እንደገለፅኩት በአለፈው ሳምንት ንግግሮት ያልጠበኩትን ነው የሰማሁት፡፡ እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ካሉ አዛውንት አፋሽ አጐንባሾች ማስፈራሪያ እና ነፃ ጋዜጦችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለማጥላላት ስም ለማጥፋት ለማቃለል.. የሬዲዮ ጣቢያ እንዳቋቋሙት (ከአሜሪካ ድምፅ በስነ ምግባር ጉድለት እና የጋዜጠኝነትን ሀሁ ባለማወቅ የተባረሩም አሉበት) ህገ ወጥ ድርጊት ይከላከሉልናል፣ ይጠብቁናል፣ ይገስፁልናል… ብለን ስንጠብቅ፤ ምን ዋጋ አለው በግልባጩ የእነዚህን ..የጥፋት ግንባር.. ቋንቋ በመጠቀም እኛው ላይ ዝተው አረፉት፡፡ እኛኑ… ብቻ ይቅር፡፡

ክቡርነትዎ፡- ሌላው በጣም ያሳዘነኝን ጉዳይ ከንግግርዎ መሀል ላንሳልዎ፡፡ ..ማሰር ብንፈልግ ለማሰር ከመጠን በላይ በቂ ምክንያት አለን፡፡ ማን የየትኛው አሸባሪ ድርጅት አባል እንደሆነ በዝርዝር እናውቃለን፡፡ ስለታገስን ያላወቅን የሚመስላቸው ካሉ እየተሳሳቱ ነው፡፡ መርጦ እርምጃ መውሰድን ስለመረጥን ብቻ ነው፡፡ ምን አልባት መንግስት ማስረጃ አይኖረው ይሆን ብለው የሚጠራጠሩ ካሉ ማስረጃው እስከሚቀርብ ድረስ አንድ ሁለት ሳምንት ይታገሱ፡፡ አሳማኝ ማስረጃ ሳይዝ መንግስት ጣልቃ አይገባም፡፡ ስለዚህ የሚሰሩት ድራማ በዝርዝር መገለፁ አይቀርም.. ያሉት ነገር ነች፡፡ እዚህች ጋር ግራ ስለገባኝ ነገር ልጠይቆት፡፡ እርሶም እንደሚያውቁት ..ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው.. ነው የሚባለው፡፡ እርሶ ደግሞ ..መርጦ እርጃም መውሰድን ስለመረጥን ብቻ ነው.. እያሉን ነው፡፡ ይሄ ታዲያ ምን የሚሉት የህግ የበላይነት ነው፡፡ ክቡርነትዎ ምን አልባት እባኮዎ ጊዜ ካሎት ..የሚታሰር እና የማይታሰር እያላችሁ የመረጣችሁበትን መስፈርቱን ቢነግሩን አንድም ከአጓጉል ጥርጣሬ እንድናለን፤ ሁለትም እንዳሉት የጋዜጠኝነትን ሀሁ ለመማር ይረዳናል፡፡ ቆይ ቆይማ የጋዜጠኝነት ሀሁ… ሲሉ ምን ትዝ እንዳለኝ ልንገሮዎ? ኢቲቪ፣ አዲስ ዘመን እና ዛሚ ላይ ያሉ ..ጋዜጠኞች..፤ የምሬን ነው የምጠይቆት እኛ ሀሁ ካልገባን፣ የተጠቀሱት ሚዲያ ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች ምን ሊሏቸው ይሆን? እርግጠኛ ነኝ የእነዚህን ተቋማት ጋዜጠኞች የሙያ ደረጃ (አቅም) ለመግለፅ ከ..ሀሁ..ም የሚያንስ ማነፃፀሪያ ይኖሮታል ብዬ አስባለሁ፡፡

አሁን ደግም ከንግግሮት ልጥቀስ ..ምን አልባት መንግስት ማስረጃ አይኖረው ይሆን ብለው የሚጠራጠሩ ካሉ ማስረጃው እስከሚቀርብ አንድ ሁለት ሳምንት ይታገሱ፡፡ አሳማኝ ማስረጃ ሳይዝ መንግስት ጣልቃ አይገባም፡፡ ስለዚህ የሚሰሩት ድራማ በዝርዝር መገለፁ አይቀርም.. የሚል ነገር እናገኛለን፡፡ መቼም ይሄ አባባል የተያዙትን ሰዎችን የሚመለከት ከሆነ የመንግስቶትን ስራ በገሃድ የሚያስተች ነው፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ ከታሰሩ አምስት ወርም የሞላቸው አሉና ነው፡፡ እናም ..ማስረጃ የላችሁም ብሎ.. ለሚጠራጠራችሁ የዚህን ያህል ጊዜም ቆይተው ..ማስረጃው እስኪቀርብ አንድ ሁለት ሳምንት ይታገሱ.. ማለትዎ ሰዎቹ የተያዙት ማስረጃ ሳይኖራችሁ እንደሆነ ያሳያልና ነው፡፡

በእርግጥ እርሶ እንዳሉት ከአንድ ሁለት ሳምንት በኋላ የኢቲቪ የፊልም ባለሞያዎች እንደ ነጎድጓድ የሚጮኽ ርዕስ ሰጥተው ኮሚንኬሽን አካባቢ ባሉ ሰዎች የተቀመረ አንድ የህንድ ፊልም የመሰለ ፊልም እንደሚያሳዩን አንጠራጠርም፡፡ ሆኖም ግን እስከ ዛሬ ድረስ በኢቲቪ በሚቀርቡ ልብ ወለድ ፊልሞች ላይ የእርሶ ድርሻ ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ስህተተኛው ለካስ እኔው ነኝ፡፡ ኢቲቪ ላሉ ወዳጆቻችን ምስጋና ይግባና ፊልሙ በእነማን ላይ እንዳነጣጠረ ሹክ አሉን፡፡ (አየር ላይ እስኪውል ግን ስለፊልሙ ከመናገር ልቆጠብ)

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ከረጅሙ ንግግሮት የጠቀስኳቸውን ብቻ ጠቅሼ ፅሁፌን ብጨርስ ምሉዕ ሆኖ ስላልተሰማኝ አንድ ነገር ልጨምር፡፡ እንደሚያውቁት እኛ ኢትዮጵያውያኖች ከማንም የተሻለ እና የተለየ ባህል አለን፡፡ ታላለቆች ለታናናሾች አርአያ የሚሆኑበት እና የምንከባበርበት፡፡ መቼም በዚህ አይነቱ ነገር ታላላቆቹ እነ አሜሪካ እንኳ ከአጠገባችን አይደርሱም፡፡ ይሄ የኢትዮጵያዊ ማንነታችን መገለጫ ነውና፡፡ ታናናሾች ለታላላቆች ወንበር እና መንገድ መልቀቅ፣ ቅድሚያ መስጠት፤ ታላለቆች ደግሞ ታናናሾች ባሉበት ነውር የሆኑ ንግግሮችን አለመናገር፡፡እርሶዎ ደግሞ በንግግርዎ “ውርጋጦች”፣ “እብድ ውሾች”፣ “ወራዳዎች …” ይሉናል፡፡ በእውነቱ ይሄ እንኳን ከመሪ፤ እንኳን 60 አመት ከሞላው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የወጣትነት ትኩስ እድሜ ላይ ካለም ቢሆን ሲሰማ ያሸማቅቃል፡፡
ይበልጥ ደግሞ ጋዜጠኞችን ..ውርጋጦች .. እያሉ መስደብ ምን ያህል ያማል መሰሎት፣ ካጠፋን ህግ አለ በህግ መጠየቅ አለብን፡፡ ከዚህ በተረፈ ህዝባችንን፣ ሀገራችንን፣ ባንዲራችንን… ባልን መሰደብ የለብንም፡፡ እኔ በበኩሌ ከሚሰድቡኝ ልብዎ የፈቀደውን እርምጃ ቢወስዱብኝ እመርጣለሁ፡፡ እናም ክቡር ጠ/ሚኒስትር ሀገራችንን ባገለገልን አይስደቡን፡፡ ከፈለጉ…

የሆነ ሆኖ የአለፈው ሳምንት ንግግርዎ ከዚህ ቀደሙ ጋር ብዙ ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይሄ ማለት ግን አዲስ ነገር የለውም ማለት አይደለምና አዲስ ነገርም አለው፡፡ እርሶም እንደሚያስታውሱት ከሁለት አመት በፊት በሀገሪቱ ፕሬስ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ የነበረው የ..አዲስ ነገር ጋዜጣ.. ባልደረቦች መንግስት ..አሸባሪ.. ብሎ ሊከሰን ነው በሚል ሀገር ጥለው ተሰደው ነበር፡፡ እናም ይህንን አስመልክቶ ሲጠየቁ (ጋዜጣውን አላውቀውም ለማለት ይመስለኛል) ..አዲስ ነገርንም አዲስ ዘመንንም.. አላነብም ብለው ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ስለሀገር ውስጥ ጋዜጣ በደንብ መረጃ እንዳሎት በሚያሳብቅ ሁኔታ አሰራራችንን አስመልክቶ ..የጋዜጠኝነት ሀሁ የማያውቁ..፣ ..ጋጥወጦች ….. እያሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ይሄ አንዱ አዲስ ነገር ነው፡፡ወይም አዲሰ ነገርንም አዲስ ዘመንንም አላነብም ካሉት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሀገር ቤት ጋዜጣን አላነብም፣ ካሉት አኳያ ሲታይ ማለቴ ነው፡፡ ሁለተኛው አዲስ ነገር እና በጣም አስደንጋጩ ስለአልታሰርነው ጋዜጠኞች አሸባሪነት ሲናገሩ ..አሁን ይፎክራሉ የቁርጥ ቀና መጥታ ስንይዛቸው ይዘፍናሉ.. ያሉት አባባል ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር፡- ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ዘፋኝ ይሆናሉ እንዴ? የምንዘፍነውስ ምን የሚል ዘፈን ይሆን? ..ታጋይ የህዝብ ልጅ በላቡ በደሙ…..ን ወይስ ..አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ.. የሚለውን ነው? ይቅርታ ስላልገባኝ ነው፡፡ እነ እስክንድር ነጋስ ምን ብለው ይሆን የዘፈኑት?
የሆነ ሆኖ ግን ይህች አባባልዎ ለእኔ እንደመሰለኝ ባሰርናችሁ ጊዜ እየደበደብን እናስጮሃችኋለን የሚል ውስጠ ወይራ አባባል ነው፡፡ መንግስትዎ ደጋገሞ የእስረኞችን ሰብዓዊ መብት እንደሚያከብር እየነገሩን እያለ እርሶ ደግሞ እናዘፍናችኃለን እያሉን ነው፡፡ በጣም ግራ ያጋባል፡፡

በመጨረሻም የመጨረሻ ሀሳቤን ላካፍሎት፡፡እርስዎ እኛን በእልህ በቁጭት የዘለፉን የታሰሩት ጋዜጠኞች ነፃ ናቸው እያሉ በፍርድ ቤት ስራ ጣልቃይገባሉ በሚል ነው፡፡ግን እኮ ነገሩን ..አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው.. አስመሰሉት፡፡ እርሶም በፍርድ ቤት ስራ ጣልቃ ገብተው በቂ መረጃ አለኝ፤ ያሰርናቸው ሰዎች አሸባሪ ናቸው እያሉ ቃል በቃል ተናግረዋል፡፡ መቼም በሀገራችን ህግ መሰረት በፍርድ ቤት ወንጀለኝነቱ ያልተረጋገጠበት ሰው ወንጀለኛ እንደማይባል ነው፡፡ ለዚህም ነው እኛን እየዘለፉ እርሶም ከእኛ እንደአንዱ ሆኑ ያልኩት፡፡የሆነ ሆኖ ለመጨረሻ ጊዜ ልድገመውና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አይስደቡን…… ከፈለጉ…

ምንጭ – ፍትህ ጋዜጣ

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close