ሓየሎም ከ ጀሚል ጋር በሚል ርእስ ባለፈው ሳምንት ማስነበባችን ይታወቃል ቀጣዩ ክፍል እንዲህ ተቀናብሮላችኋል መልካም ቆይታ ..ዳዊት ከበደ

ቀደም ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ውስጥ ይሰራ የነበረ ጋዜጠኛ፤ የኃየሎምን ሞት የሰማበትን ቀን አይዘነጋውም። የካቲት 7 1988 ዓ.ም. ነው። ወደኋላ ተመልሶ ያንን እለት ሲያስታውሰው እንዲህ ይላል። “ጠዋት ስራ ቦታ ገብቼ ሳለሁ፤ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አማረ አረጋዊ በንዴት ፊቱ ተለዋውጦ ሲገባ አየሁት… ወዲያው እንባ እየተናነቀው፤ ‘አስገደሉት! አስገደሉት!’ እያለ የለቅሶ ያህል ጮኸ። መጀመሪያ ማን እንደሞተ ወይም ማን እንደተገደለ ስላላወቅኩ ነገሩ ግራ አጋብቶኝ ነበር። ወዲያው ግን የተገደለው ኃየሎም እንደሆነ አወቅኩ። ‘አስገደሉት! አስገደሉት’ የሚለው የአማረ አረጋዊ ጩኸት ግን ምንጊዜም አይረሳኝም።” ሲል ነበር ትዝታውን ያጫወተኝ።

እንግዲህ ዜናው በሬድዮ ከመነገሩ በፊት፤ “አማረ አረጋዊ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” ብላችሁ እንዳትሞግቱኝ። የቀድሞ የህወሃት አባልና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ሃላፊ የነበረ ሰው በመሆኑ  እምብዛም የሚደንቅ አይሆንም። እናም እሱ “አስገደሉት!” ካለ፤ ሟች እና ገዳይ ብቻ ሳይሆን፤ ሁኔታውን ያስፈጸሙ አስገዳዮች መኖራቸውንም ያመላክታል።
(የኔ ትረካ አላማ ግን አስገዳይ ስለሚባሉት ሳይሆን፤ ስለ ገዳይ እና ሟች የማውቀውን ለመመስከር ነው። ከዚህ በታች የምገልጽላችሁ አንኳር አንኳሮቹ ጉዳዮች እራሴው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለሁ የዘገብኳቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ አገር ቤት ሳለሁ በወቅቱ አፈና ምክንያት ለህዝብ ለማቅረብ አስቸጋሪ የነበሩ ናቸው። እናም ጥቂቱን ካልሆነ በቀር አብዛኛውን ነገር ለማካተት ሞክሬያለሁ)
ኃየሎም የተገደለ ሰሞን ህወሃት ቆሌ የራቀው ድብኝት መሰሎ ነበር። የኃየሎም አርአያ አሟሟት በጥያቄ ውስጥ በነበረበት ወቅት ላይ አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ፖስተር በየቦታው ተለጠፈ። ፖስተሩ ላይ “ኃየሎምን አስገደሉት!” የሚል ጽሁፍ ታትሟል። የዘፋኝ ፎቶ አለበት። ትንሽ ዝቅ ብሎ “በቅርቡ በሁሉም ሙዚቃ ቤቶች ያገኙታል፡፡” የሚል ጽሁፍ አለ።
ዘፈኑ በጉጉት ሲጠበቅ ቆየና በተባለው ቀን በየሙዚቃ ቤቱ ተለቀቀ። ዘፈኑ በትግርኛ ነው። ከሙሉው ዘፈን አንዷ ብቻ… “ኃየሎምን አስገደሉት” በሚል አዝማች እና… “ድድም! ድድም!” በሚል ከበሮ ታጅቦ የኃየሎምን ገድል የሚያትት ዘፈን ነበር።
በወቅቱ ኢህአዴግ ዘፈን የታተመ ካሴት ሲያፍን ታይቶ አይታወቅም። ነገር ግን ይህች ትግሪኛ ዘፈን ለመታፈን የመጀመሪያዋ ሆነች። ታጣቂዎች በሁሉም ሙዚቃ ቤቶች በአንድ ቀን ፈሰሱና ሙሉውን ካሴት ለቅመው ወሰዱ። ዘፋኙ የት እንደደረሰ የሚያውቅ ይወቀው። ነገር ግን ዘፈኑን ሲሰማ የተገኘ ሰው ሳይቀር እየታደነ ታሰረ። ይህንን የትግሪኛ ካሴት ከጓዳ ጀምሮ እስከሙዚቃ ቤት ድረስ… በሚገርም ሁኔታ አፈኑት – አጠፉት።
ይህ በህወሃት የደህንነትና ወታደራዊ መዋቅር አማካኝነት የተደረገ… የካሴት ለቀማ ኦፕሬሽን በተለይ ትግርኛ ተናጋሪውን አነጋገረ። “ለምን?” የሚለውም ጥያቄ ውስጥ ለውስጥ ይሰማ ነበር። የነጻ ፕሬስ ጋዜጦች ይህንኑ የካሴት አፈና ተግባር የዜና ሽፋን ሰጥተው አወጡት።
“ኃየሎምን አስገደሉት!” የሚለው ወሬ ግን ውስጥ ውስጡን እየነደደ መጣ። በካሴቱ ላይ የተደረገው አፈና… ይበልጥ ጥርጣሬን አጫረ። ገደሉት እንጂ አስገደሉት ብሎ ለመናገር ሁሉ አቅም አጣ። (አሁንም ድረስ የዘፋኙን እና የዘፈኑን መጨረሻ አላውቅም። የምታውቁ ካላችሁ ንገሩን)
እንግዲህ በዚህ የወሬ መላምትና ውዝግብ መካከል ነው… ራሴ ለተከሰስኩበት የነጻ ፕሬስ ጉዳይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ችሎት የተገኘሁት። ጉዳዬን ከአንደኛ ችሎት ጨርሼ ስወጣ… ወደ ሁለተኛ ችሎት የገባሁበትን ምክንያት ባለፈው ጽሁፌ ስለገለጽኩ፤ አሁን በቀጥታ ወደዚያው ሁለተኛ ችሎት እመልሳችኋለሁ።
በፌዴራሉ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ውስጥ ነው ያለሁት። ባለጉዳዮች አለፍ አለፍ ብለው ተቀምጠዋል። አቶ ሃጎስ ወልዱ የሚፈርዱበት ችሎት ነው። የጀሚል ሃሲንን ጉዳይ በጋዜጣዬ ላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ጽፌያለሁ። ሆኖም በተፈጠረው አጋጣሚ ግጥምጥሞሽ ምክንያት፤ እራሴው በፍርድ ቤት ተገኝቼ ሁኔታውን ስታዘብ የመጀመሪያዬ ነበር።
ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ከሌሎቹ ችሎቶች ይልቅ የሚያስፈራ ነው። ባለጉዳዮችና ተከሳሾች የሚሰደቡበትና የሚንጓጠጡበት ችሎት በመሆኑ ይታወቃል። ችሎቱ ይህንን አስፈሪ ድባብ የተላበሰው በመሃል ዳኛው አቶ ሃጎስ ወልዱ አማካኝነት ነው። የፖለቲካ እስረኛና ጋዜጠኞች እዚህ ችሎት ሲገቡ፤ የመሃል ዳኛው በመሳደብ ነው የሚጀምሩት። የፖለቲካ ድርጅት አዛዥ እንጂ ዳኛ አይመስሉም። ፖሊሶቹ ሳይቀሩ የሚፈሯቸው ሰው ናቸው – አቶ ሃጎስ ወልዱ።
አቶ ሃጎስ ወልዱ ኢህአዴግ እንደገባ የክልል 14 የዳኞች ፕሬዘዳንት ሆነው ተሹመው ነበር። ይህንን ሹመት ያገኙት የአዲግራት፣ ትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው መሆኑ በሰፊው ይወራ ነበር። ነገር ግን ሌሎች ከአዲግራት ውጪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በሙስና ወንጀል ከሰሷቸውና ከክልል 14 ፕሬዘዳንትነታቸው ወርደው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኑ። በዚህ የዳኝነት ዘመናቸው በተለይ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ታስረው ለሚመጡ ሰዎች አንዳችም ሃዘኔታ አልነበራቸውም። እንደፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እና ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት ላይ የፈረዱባቸው አቶ ሃጎስ ወልዱ ናቸው።
ችሎቱ ውስጥ የተቀመጠው ሰው ዝም ብሏል። ሰዓቴን አየሁ። ዳኞች ለምሳ የሚወጡበት ሰዓት ነው። ከዚህ ሰዓት በኋላ ችሎት አይሰየምም። በመውጣትና በመቆየት መካከል ሆኜ ሳቅማማ፤ ዳኞች የሚገቡበት በር ተከፈተና አንድ ፖሊስ ብቅ ብሎ ችሎቱ ውስጥ ያለውን ሰው ገርመም አደረገ። ከዚያም ከውጭ ለቆመው ታጣቂ ምልክት ሰጠው። ችሎቱ ሊሰየም መሆኑ ስለገባኝ፤ ዳኞቹ ከመግባታቸው በፊት የማስታወሻ ደብተር እና ብዕሬን አዘጋጀሁ።
አንድ ያልገባኝ ነገር ግን አለ። ‘የጀሚል ያሲን ጉዳይ ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚታየው በአንደኛ ችሎት ሆኖ ሳለ፤ ያለቀጠሮ ለምን ወደዚህ ችሎት መጣ?’ የሚለው ጥያቄ አሁንም ድረስ ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ነው። ጥያቄውን እናንተም በልቦናችሁ ጻፉትና የአቶ ሃጎስ ወልዱ ችሎት እስከሚሰየም ድረስ የአቃቤ ህግ ምስክሮች በአንደኛ ችሎት የሰጡትን ቃል መሰረት በማድረግ… ኃየሎም አርአያ በተገደለበት ምሽት የሆነውን ላውጋችሁ።
ከዚህ ቀደም በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውስጥ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ሰዎች… ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በስፍራው ከነበሩት ሰዎች ጀምሮ፤ ጀሚል ሽጉጥ ተኩሶ ኃየሎም አርአያን ሲገድል የተመለከቱት ሰዎች እየቀረቡ ምስክርነት ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም እንዳደረኩት ከምስክሮቹ ቃል በመነሳት የታሪኩን ሃዲድ ተከትዬ የሆነውን ነገር እተርክላችኋለሁ።
የካቲት 6 ቀን 1988 ዓ.ም. ለሊት ከጀሚል ያሲን የተተኮሰች ጥይት፤ የኃየሎም አርአያን ግንባር መታች… ከዚያም ተከትሎ አዲስ አበባን የድንጋጤ ምች መታት። አይበገሬ ይመስል የነበረው ጄነራል፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተሸነፈ።  (በጀሚል ያሲን የተተኮሰችው ጥይት በኃየሎምን ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በሰራዊቱ ውስጥ ያመጣችውን መዘዝ በኋላ ላይ አወጋችኋለሁ)
ጀሚል ያሲን አምባ ራስ ያቆማትን መኪና አስነስቶ እንደሄደ አካባቢው፤ በጩኸትና በኡኡታ ተሞላ። ቡና ቤት ውስጥ ረብሻ እንደተነሳ አብረውት የነበሩ ሰዎች መኪናቸውን እያስነሱ አፈተለኩ። ፖሊስ አካባቢውን ሞላው። ጀሚል በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ ነው። አምስተኛው ሰው ከቤት የወጣው በድንገት ስለሆነ በኪሱ ምንም ገንዘብ አልያዘም ነበር… እናም በኮንትራት ታክሲ አካባቢውን ለቅቆ ሄደ። ለታክሲም ሹፌር “ገንዘብ አልያዝኩም። እቤት ስንደርስ እሰጥሃለሁ።” አለው።
ታክሲ ሹፌሩ ምንም ችግር እንደሌለው ነግሮት፤ አምባ ራስ ሆቴል ስለተፈጠረው ግርግር ጠየቀው። 5ኛው ሰው ቡና ቤቱ ውስጥ ረብሻ መነሳቱን፤ ከዚያም ተኩስ እንደነበረና በተኩሱ አንድ ሰው መጎዳቱን ገለጸለት። እንዲህ ያለ ነገር በህይወቱ እንዳላጋጠመው እየነገረው፤ ሹፌሩም እየሰማና እየነዳ ቤቱ አደረሰው። እቤት ሲደርሱ አምስተኛው ሰው “ገንዘብ ከቤት አምጥቼ ልስጥህ” አለው።
ሹፌሩም መለሰ። “የለም አልፈልግም”
“እርግጠኛ ነህ”
“አዎ” አለው።
ያንን ሁሉ መንገድ ይዞት መጥቶ፤ ሂሳቡን ስላላስከፈለው አመስግኖ ተለያዩ።
ለፍርድ ቤቱ ከተሰጠው የምስክርነት ቃል፤ ሌላውን ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ።
በዚያው ለሊትና ደቂቃ ጀሚል ያሲን ቤቱ ገባ። እህቱ ነበረች መጀመሪያ ያገኘችው። ቀኝ ጉንጩ እየደማ ነበር። እቤት እንደገባ ሽጉጡን ለትንሽ እህቱ ሰጣት እና ማልቀስ ጀመረ።
ምን እንደተፈጠረ ያላወቀችው እህቱ ተደናግጣለች። “ምንድነው የተፈጠረው?” አለች።
ጀሚል በስካርና ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ነበር። በትክክል እገሌ ላይ ተኩሻለሁ ወይም ገድያለሁ አላላትም። ነገር ግን አንድ ትልቅ ጥፋት እንደተሰራ ነገራት።
በጀሚል ያሲን ጉንጭ ላይ የሚወርደውን ደም ስትጠርግለት፤ በወንድሟ ላይ ይህን ጉዳት ያደረሰበትን ሰው ጠየቀችው። እቤቱ እየነዳ የመጣው ጀሚል ያሲን ከስካር መንፈስ ሙሉ ለሙሉ አልወጣም። ማን ይህንን ጉዳት እንዳደረሰበት አልነገራትም፤ ነገር ግን በንዴትና በድንጋጤ ተዘቅዟል።
ደሙን ሙሉ ለሙሉ ጠርጋ ስትጨርስ በጀሚል ያሲን ጉንጭ ላይ በጉልህ የሚታይ የሰንበር ቅርፅ ወጣ።   ኃየሎም አርአያ በግራ እጁ ጣት ላይ የሚያስረው ቀለበት ምልክት በጉንጩ ላይ ታትሟል። በኋላ ለፍርድ ቤቱ ምስክርነቷን ስትሰጥ እንደሰማሁት በወንድሟ ጉንጭ ላይ ታትሞ የነበረው የሰንበር ቅርፅ “የሞዓ አንበሳ” ቀለበት ምስል ነበር። (አንዳንድ ሰዎች… ኃየሎም የሞዓ አንበሳ ምስል ያለው ቀለበት ማድረጉ ይገርማቸው ይሆናል። እኔን በጣም ይገርመኝ የነበረው ኃየሎም በአይበሉባ ጥፊ ተማትቶ ያን ያህል ምልክት ከተወ፤ ጀሚልን በቦክስ መትቶት ቢሆን መጀመሪያ የሚሞተው ሌላ ሰው ይሆንና በኃየሎም ላይ የሚሰጠውን ፍርድ እያሰብኩ እገረማለሁ።)
በዚህ መሃል የነጀሚል ቤት በሃይል ተንኳኳ። ታናሽ እህቱ ከመጀመሪያው በዚህ ሽጉጥ አንድ ነገር እንደተደረገ አውቃለች። እናም ሽጉጡንና ጥይቶቹን ለመደበቅ ሞከረች… ከዚያም በሃይል የሚንኳኳውን በር ስትከፍት… የታጠቁ ሰዎች በጩኸትና በሃይል እየገፈታተሩ ወደ ውስጥ ጥሰው ገቡ። ጀሚል ያሲን በሰላማዊ መንገድ እጁን ከመስጠት ውጪ አላንገራገረም። ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ተደረገበት።
ግድያ የፈጸመትን መሳሪያ እንዲያመጣ ሲጠየቅ በስካር መንፈስ ውስጥ ነበር። ባልጠበቀችው ሁኔታ ታላቅ ወንድሟ ሲደበደብ ያየችው እህቱ፤ ሽጉጡን የት እንደደበቀች መርታ አሳየች። ታጣቂዎች ሁለቱንም እየደበደቡ ከቤት አስወጥተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። (በኋላ ላይ እሷ ወንጀል የተሰራበትን መሳሪያ በመደበቅ ወንጀል ተከሰሰች።)
በሌላ በኩል አምስተኛው ሰው የሰጠውን ቃል እንመልከት። ጀሚልን እንጂ ኃየሎምን የማያውቀው 5ኛው ሰው፤ ቤቱ ገብቶ አንድ ሰዓት ያህል እንደቆየ ግቢው የውጭ በር በሃይል ተንኳኳ። በሩን ሲከፍትለት… በንዴት እሳት ውስጥ የነበረ ታጣቂ የአምስተኛውን ሰው ስም ጠርቶ “…የት ነው?” ሲለው ደነገጠ። ‘እኔ ነኝ’ ቢለው ሊመጣበት የሚችለውን አበሳ በመፍራት፤ በድንጋጤ “እዚህ የለም” አለው። አብረው የመጡትን ሰዎች ውጪ ትቷቸው… ጠመንጃውን ደግኖ፤ ሰውን ለመግደል የተዘጋጀ በሚመስል መልኩ… ወደ መኖሪያ ቤቱ ገባ። ሁኔታው አስፈሪ ነበር።
ሆኖም ከታጣቂው ሰው ጋር አብረው የመጡት ሰዎች፤ ከቤተ መንግስት ተቀስቅሰው የመጡ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ጭምር በፒጃማ ሆነው ውጪ ቆመዋል፤ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ባስቸኳይ እንደመጡ ያስታውቃል።  ከጥቂት ሰአት በፊት እቤቱ ያደረሰው የታክሲ ሹፌርም ከባለስልጣናቱ ጋር ነው።
ስሙን ጠርተው “እገሌ… ማለት አንተ አይደለህም እንዴ?” አሉት – አምስተኛውን ሰው።
ምንም አላመነታም። ገፍትሮት ወደቤት ከገባው ወታደር ይልቅ፤ በቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ የሚያውቃቸው ባለስልጣናት ይሻሉኛል ብሎ… “አዎ እኔ ነኝ!” አለ። ባለስልጣናቱ ምረው አልማሩትም። ጎሸም ጎሸም አድርገው መኪና ውስጥ አስገቡት። ከዚያም አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ጨለማ ክፍል ተወረወረ።
      ጀሚል ያሲን እና አምስተኛው ሰው በተለያዩ ጨለማ ቤቶች ውስጥ ታስረው ሲሰቃዩ እንደነበር በኋላ ላይ ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል። ብዙዎቹ የአቃቤ ህጉ ምስክሮች ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ እንደነበር ለፍርድ ቤት የሰጡት ቃል ያመለክታል።
እኔም ከነዚያ ፍርድ ቤቶች መካከል አቶ ሃጎስ ወልዱ ያሻውን በሚያዙበት ችሎት ውስጥ ተቀምጫለሁ። ሁለተኛ ችሎት ፀጥ እረጭ ብሏል። በዚህ መሃል… ድንገት ግን ከውጭ በሚያስገባው በር በኩል ያልጠበኩትን ድምፅ ሰማሁ። “አላህ አኩበር!” የሚል ድምፅ ሰምቼ ዞር አልኩ። ጀሚል ያሲን ነው።
 ከፊት ከፊት የሚሄደውን የፍርድ ቤት ተላላኪ እየተከተለ በአጃቢ ወደ ውስጥ ሲገባ “አላህ አኩበር!” ማለቱን እንደቀጠለ ነበር። በአቶ ሃጎስ ችሎት ውስጥ፤ እንኳንስ በጩኸት “አላህ አኩበር!” ተብሎ ይቅርና በሹክሹክታ ማውራትም ያስፈራል። የዚህ ችሎት ፖሊሶችም ቢሆኑ፤ ከሌሎች ችሎት በባሰ ሁኔታ ቁጥጥር ያበዛሉ። ወደ ውስጥ ሲገባ ከሚደረገው ፍተሻ ጀምሮ ቁጥጥሩ የበዛ ነው። ስነስር ዓት አስከባሪዎቹ እርስ በርስ መነጋገር፣ እግርን ወይም እጅን አጣምሮ የተቀመጠ ሰው ሲመለከቱ በቁጣ ፊታቸውን ከስክሰው፤ “ፍታ!” ይላሉ። ብዙ ሰዎች የዚህን ችሎት ጉዳይ ስለሚያውቁ ተሳቀውና ተሸማቀው ነው ሁኔታውን የሚከታተሉት። ይህንን የጸጥታ ድባብ ነው ጀሚል የሰበረው።
በኢትዮጵያ እንደልማድ ሆኖ፤ እስረኞች ዳኛው ፊት ሲቀርቡ የእጃቸው ሰንሰለት ይፈታል። አሁንም የጀሚል ያሲን የእጆቹ ሰንሰለት ሲፈታ፤ ድምጹን ቀነስ አድርጎ። “አላህ አኩበር!” አለ። ሁኔታውን ስመለከት ፍርድ ቤት በመቅረቡ ደስ የተሰኘ ይመስላል። “አላህ አኩበር!” ወይም “አምላክ ይመስገን!” ያለውም ምናልባት ፍትህ ለማግኘት ካለው ጉጉት ሊሆን ይችላል።
በዚህ አይነት ትንሽ እንደቆየን፤ ዳኞች የሚገቡበት የኋላ በር ሲከፈት ስነ ስርአት አስከባሪው ፖሊስ በእጁ ምልክት ሰጠ። ሁሉም ሰው ብድግ አለ። አቶ ሃጎስ ጥቁር ካባቸውን እንዳደረጉ ግራና ቀኙን እየገረመሙ ቁጭ አሉ። ፖሊሱ በእጁ እንድንቀመጥ ምልክት ሰጠ። ሁሉም ሰው ቁጭ አለ። እኔም ማስታወሻ ደብተሬ ላይ መጻፍ ጀመርኩ። የጀሚል ያሲን ጠበቆች በስፍራው የሉም። መርማሪ ፖሊሱና ታጣቂዎች ናቸው የሚታዩት። እንደ ደንቡ የግራና ቀኝ ዳኞች አብረስ መኖር አለባቸው… የሉም። የፍርድ ቤት መዝገብም መቅረብ አለበት… ይሄም የለም።
ምን አይነት የፍትህ አካሄድ እንደሆነ ግራ ገብቶኝ ሳለ… አቶ ሃጎስ – ገና ገብተው ቁጭ ከማለታቸው ጀሚል ያሲንን በግልምጫ አነሱት። ከዚያም የችሎቱ ስነ ስርአት አስከባሪ ላይ አፍጥጠው፤ “ለምንድነው ታስሮ ያልቀረበው?” አሉት። ስርአት አስከባሪው እና ፖሊስ፤ እየተጣደፉ እንደገና በሰንሰለት አሰሩት። ጀሚል እንደገና እየታሰረ እያለ፤ “እዚያም ታስሬ ነው የምውለው…” ሲል፤ አቶ ሃጎስ “እሱን በኋላ ትናገራለህ!” ብለው ችሎቱ ውስጥ ወደተቀመጥነው ሰዎች አፍጥጠው፤ “ማነው ያስገባቸው?” አሉ። የፈረደበት የችሎቱ ስርዓት አስከባሪ እየተጣደፈ… ችሎቱ ውስጥ የተቀመጥነው ሰዎች እንድንወጣ ምልክት ሰጠን። ሰዉ እየተንጓፈፈ ሲወጣ፤ እኔም ማስታወሻ ደብተሬን ወደ ኪሴ መለስኩ…
ሰዉ ከችሎቱ ከወጣ በኋላ፤ ከፊት ለፊት ካሉት ፅዶች ጋር ሄጄ ለተወሰነ ደቂቃ ብቻዬን ቁጭ አልኩ። እስረኛ ያለቀጠሮ ሊመጣ የሚችለው በተለይ ከእስር ቤቱ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ችግር ሲያጋጥም መሆን አለበት። ለምሳሌ እስረኛው አስቸጋሪ ከሆነ፤ ከፖሊስ ጣቢያውም አቅም በላይ ከሆነ፤ ሊወሰድበት የሚችለውን እርምጃ ለማስፈረድ በ’ንዲህ አይነት ሰበር ችሎት ቀርቦ ሊሆን ይችላል። በወቅቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር አራንሺ በኃየሎም ጉዳይ በሚደረገው ምርመራ እጁ ስላልነበረበት፤ ውሳኔ መስጠት አይችልም ነበር። ‘ምናልባት ሃጎስ ወልዱ የፖሊስ ኮሚሽነሩን ቦታ ተክተው ይሆን?’ የሚል መላ ምት ከመስጠት እና ፍትህ በጥቂት ሰዎች የምትሽከረከር መሆኑን ከማሰብ በቀር በዚህ ጉዳይ ብዙ ለማለት አልችልም። ከዳኛ ሃጎስ ወልዱ 2ኛ ችሎት… የጀሚል ያሲንን ጉዳይ ወደያዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ ልወስዳችሁ ነው።
      የፌዴራሉን ከፍተኛውን ፍርድ ቤት ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ… ብዙ ጊዜ ራሴን የምጠይቀውን ጥያቄ በጋዜጣዬ ላይ ለማውጣት እየተዘጋጀሁ ነበር። የአንድን ነገር ሚስጥር ለማግኘት እንደሚጣጣር ጋዜጠኛ… “የኃየሎምን የግድያ ሚስጥር ለማወቅ ሰዎቹን ብቻ ሳይሆን፤ ግድያው የተፈጸመበትን ሪቮልቨር ሽጉጥ መከታተል ያስፈልጋል።” የሚል አቋም ነበረኝ። ጀሚል ያሲን በኤርትራዊነት ከተፈረጀ… የሌላ አገር ዜጋ ሆኖ ሽጉጥ እንዲታጠቅ ማን ፈቀደለት? ከየት አመጣው? ማን ሰጠው? የሚለውን ጥያቄ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ያህል በጋዜጣዬ አትሜያለሁ። ‘ይህም በህዝቡ ዘንድ የሚወራውን ጥርጣሬ ለአንዴና ለሁሌውም ያጠራዋል’ የሚል እምነት ነበረኝ።
      ይህንን ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ በጋዜጣዬ ላይ ሳወጣ ሊያመጣ የሚችለውን ሌላ አስደንጋጭ ወሬ አላሰብኩበትም ነበር። የዚያኑ ቀን ቢሮዬ ተደወለ። አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የሚሰራ መርማሪ ነው። ከኔ ጋር የተዋወቅነው፤ ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት ሱር ኮንስትራክሽን ከአለም ባንክ የ80 ሚሊዮን ዶላር (ትክክለኛውን የገንዘብ መጠን አሁን ረስቼዋለሁ) ብድር እንዲያገኝ ማስደረጋቸውን የሚያጋልጥ ዜና ያቀረብኩ ጊዜ ነው። መርማሪ ፖሊሱ በጉዳዩ ላይ ለጥያቄ እንደምፈለግ ገልጾልኝ ፖሊስ ጣቢያ ስሄድ፤ ከመረጃዎቼ አንዱ የሆነውን ለአለም ባንክ የተጻፈውን ደብዳቤ ኮፒ ይዤ ነበር። ክሱን አንብቦልኝ ቃሌን ከመስጠቴ በፊት ትንሽ ተጨቃጨቅን። “በፕሬስ ህጉ መሰረት መረጃዎቼን ለፖሊስ ለመስጠት አልገደድም። ነገር ግን በጋዜጣው ላይ ላወጣነው ዜና መነሻዬ ይሄ ነበር።” ብዬ በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር በአቶ ታምራት ላይኔ ለሱር ኮንስትራክሽን ግልባጭ ተደርጎ የተጻፈውን ደብዳቤ ሰጠሁት። መርማሪው ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ በሁኔታው አዘነ።
መርማሪው በቀድሞው መንግስት በፖሊስ ኮሌጅ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን… የቀድሞውን መንግስት እና ከአሁኑ የኢህአዴግ አስተዳደር ጋር እያነጻጸረ የውስጡን አወራኝ። ቃሌን ተቀብሎ፣ መረጃዬን አያይዞ የዋስ መብቴ ጠብቆልኝ ወጣሁ። ከዚህ መርማሪ ፖሊስ ጋር አልፎ አልፎ ፒያሳ እንገናኝ ነበር።
      ዛሬ የደወለው ግን በቀጠሮ ተገናኝተን እንድንነጋገር ፈልጎ መሆኑን ነገረኝ።
      ማታ ላይ ስንገናኝ በሲቪል ልብስ ነበር የመጣው። ምንም ፍርሃት ወይም ስጋት አይነበብበትም። “ዛሬ የወጣውን ጋዜጣህን አንብቤዋለሁ” ሲለኝ በየትኛው ርዕስ ሊያናግረኝ እንደፈለገ ጠርጥሬያለሁ። ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በተያያዘ የማወጣው የትችት ጽሁፍ ደስ እንዳላለው ነገረኝ። “ይሄ በኃየሎም ጉዳይ የምታወጣውን ወሬ ቀንሰው ወይም ተወው። ምንም አያደርግልህም።” አለኝ።
“ለምን?”
“ይሄ ነገር የነሱ የውስጥ ጉዳይ ሆኗል።” ብሎ ደህንነቱና ፌዴራሉ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩና መከላከያው ሳይቀር የሚታመሱበት ነገር መሆኑን ነገረኝ። “ደግሞ ይሄንን ‘የውስጥ ሽኩቻ’ ብለህ ጋዜጣህ ላይ እንዳታወጣ!” አለኝና ፈገግ አለ።
ረዥሙን ታሪክ በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል… የነገረኝ ታሪክ የሚከተለው ነበር።
የጀሚል ያሲንን የምርመራ ጉዳይ የሚያካሂደው ተስፋይ አብርሃ ሪፖርቱን በቀጥታ የሚያቀርበው ለክንፈ ገብረመድህን ቢሮ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ውይይቶች ወይም የስልክ ልውውጦች በትግርኛ ብቻ ነው የሚደረጉት። አሁን አንተ የምትለው የጦር መሳሪያ የፈቀደለትና የሰጠው ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?” አለኝ።
“የኔም ጥያቄ እሱ ነው። ማነው የሰጠው?” አልኩት።
ድምፁን ዝቅ አድርጎ፤ “ሽጉጡን የፈቀደለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ነው” ሲለኝ ለምን እንደሆነ ሳላውቅ ድንግጥ አልኩ።
“አራንሺ ነው ማለት ነው መሳሪያውን የፈቀደለት?” ጆሮዬን ማመን አቅቶኝ በድጋሚ ጠየኩት።
“አዎ አራንሺ ነው። በዚህ ምክንያት ከስልጣኑ ተነስቷል። ይሄንን ነገር ጋዜጣ ላይ እንዳታወጣ። ላንተ የምነግርህ እንድትጠነቀቅ ነው። ሰዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ቁጥጥር ስር ይሁኑ እንጂ፤ ምርመራውን የሚከታተለው የፌዴራል ፖሊስ እና የደህንነት ክፍሉ ነው። ደህንነቱ ደግሞ ከፊቱ የሚጋረጡበትን ስዎች አያስርም፤ ያጠፋቸዋል። ይሄንን ነገር ደጋግመህ የምታወጣ ከሆነ ወይም የምታውቅ መሆንህን ካወቁ አንተንም ሊያጠፉህ ይችላሉ።” ማስጠንቀቂያው ሲበዛብኝ፤ እኔን ለማስፈራራት የላኩት መስሎኝ ነበር።
በኋላ ላይ በእርግጥም የአዲስ አበባው ፖሊስ ኮሚሽነር አራንሺ ገብረተኽለ የውስጥ ግምገማ ተደርጎበት፤ በእጁ ያለውን መሳሪያ አስረክቦ በቁም እስር ላይ ነበር።
ከኃየሎም አርአያ ግድያ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሰዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ የጨለማ እስር ቤት ውስጥ ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ ሆነው ሲሰቃዩ… የዚያው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር አራንሺ የቀን ጨለማ ውጧቸው ኖሯል። ደጋግሜ የማነሳው “መሳሪያውን ማን ሰጠው? ማን ፈቀደለት?” ለሚለው ጥያቄ መልስ አገኘሁ። ይህንን በወቅቱ ይሄንን በዜና መልክ ማቅረቡ አንድም ወሬውን የሰጠኝን ፖሊስ ችግር ውስጥ መጣል ሲሆን፤ እሱም እንደነገረኝ የጋዜጣውን እድሜ ከማሳጠር ውጪ የሚሰጠው ፋይዳ አልነበረም። (ቆይቶ መረጃውን የሰጠኝ ፖሊስ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ መዛወሩን ሰማሁ። አራንሺም ያለ ስራ ብዙ ከቆየ በኋላ፤ ወደ ትግራይ ተዛውሮ በክልሉ ውስጥ በሆነ ኃላፊነት ውስጥ እየሰራ ነበር። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ በግል የጥበቃ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርቷል።)
የኃየሎም አርአያ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሲታይ፤ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ህጉ ግድያ የተፈጸመበትን መሳሪያ ምንጭ አልጠቀሱም። በዜግነት ኤርትራዊ ለሆነ ሰው የመሳሪያ ፈቃድ መስጠት በህግ የሚያስቀጣ ቢሆንም፤ ህግም ለሁሉ ዜጋ እኩል ማገልገል ሲገባው፤ የሽጉጡ ምንጭ የሆነው አራንሺ ገብረተኽለ  የድርጅት እንጂ ህጋዊ እርምጃ ሳይወሰድበት ቀረ።
እንግዲህ በመግቢያዬ ላይ ከገለጽኩት የአቶ አማረ አረጋዊ እና የዘፋኙ… “አስገደሉት” ከሚለው ቃል ተነስተን፤ በኋላም በ22ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ ላይ የተፈጸመውን ሁኔታ ስንመረምር… የጥርጣሬያችን ቀስት ወደ ህወሃትና ሻዕቢያ ሊሄድ ይችላል። እኔ ግን እላለሁ። አይንና ህሊናችን እሩቅ እንዲያይ በተደረገ ቁጥር፤ የኢህአዴግ የፍትህ ተቋማት የሰሩትን የአድልዎ ግፍ እንዳናይ እየተደረገ ነውና እባካችሁን አይናችንን ገልጠን፤ ህሊናችንን ከፍተን በህግ ሽፋን የሆነውን እንመልከት።
የሞት ፍርድ ውሳኔው በሚሰጥበት ሰሞን፤ ኃየሎም ከሞተ አንድ አመት እየተቆጠረው ነበር። በዚሁ ሰሞን ደግሞ አልፎ አልፎ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ግጭቶች መፈጠር ጀምረው ነበር። በተለይም በባድመ አካባቢ የጋሽ ሰቲትን ወንዝ ተሻግሮ በታህታይ እና በላዕላይ አዲያቦ በኩል… የሻዕቢያ የትንኮሳ መስፋፋቶች ይታዩ ነበር። ከሚሊሻው ጀምሮ እስከ ሰራዊቱ የበታች ሹሞች ድረስ ማለትም ሻምበል እና ሻለቃዎች ይሄንን ጉዳይ ያውቃሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሻምበሎችና ሻለቆች ግማሽ ኤርትራዊና የትግራይ ሰዎች በመሆናችው፤ ሪፖርቱን ወደ ላይ እንዳላቀረቡ ይነገራል… ከዚህም ጋር ተያይዞ የመጣውን ጉዳትና ቅጣት በሚቀጥለው ጽሁፌ የምመለስበት ነው።
አሁን እዚያው ትግራይ ውስጥ ላቆያችሁ። የኃየሎም ሃውልት ተሰርቶ (የአሁኑ አይደለም) ሙት አመቱ ሊከበርለት ዝግጅቱ ተጠናቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህዝቡ፤ “ኃየሎም ቢኖር ኖሮ ሻዕቢያ የጋሽ ሰቲትን ወንዝ አትሻገርም ነበር” እያሉ ያወራሉ። ከዚሁም ጋር አያይዘው፤ “ቀደም ብለው ጥናት አድርገውበት ኃየሎምን ያስገደሉት እኮ ለዚሁ መስፋፋት ብለው ነው።” እያሉ በሰፊው ያወራሉ። ነገሩ እውነት ይመስላል። በመጀመሪያ ሰሞን፤ እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እኔም የዚህ መላምት ሰለባ ነበርኩ። ፍርድ ቤት እየሄድኩ የምስክሮቹን ቃል እየሰማሁ ስመጣ ግን ጭብጥ ከሌለው መላምት ራሴን ነጻ አውጥቻለሁ። እርስዎንም ወደ ፍርድ ቤቱ ውሎ ልውሰድዎ።
በፍርድ ቤቱ ሂደት ወቅት አቃቤ ህጉ በጀሚል ያሲን ላይ ሞት ለማስፈረድ ይረዱኛል… ያላቸውን ምስክሮች አቅርቧል። በሚገርም ሁኔታ ግን ሁሉም የአቃቤ ህግ ምስክሮች፤ “በኃየሎም እና በጀሚል መካከል ፀብ ሲነሳ፤ ተከሳሹ በስካር መንፈስ ውስጥ እንደነበርና ፀቡም በድንገት የተፈጠረ ነው።” ሲሉ መስክረዋል።
5ኛውም ምስክር ተመሳሳይ ቃል ነው የሰጠው። ነገር ግን፤ “ተከሳሹ ሽጉጡን ከመኪናው አውጥቶ አይተሃዋል?”
“አዎ”
“ሲተኩስ አይተሃል?”
“አዎ”
“አንተ ሲተኮስ የት ነበርክ?”
“ውጪ ነበርኩ”
“እሱ በሚተኩስበት ጊዜ አንተ ምን አደረክ?”
“ተው አልኩ” አለ። አቃቤ ህጉ ይህንን ነጥብ ያዘ።
ይህንን ነጥብ መሰረት በማድረግ፤ በአቶ መስፍን ግርማ የሚመራው አቃቤ ህግ አለ፤ “ጀሚል ያሲን ግድያውን የፈጸመው አስቦና አቅዶ በአሰቃቂ መንገድ ነው” ብሎ ደመደመ። ስለዚህ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 522፣ ቁጥር 1፤ ህዝባር ሀ መሰረት ግድያው የተፈጸመው ቀደም ብሎ ታስቦበት፤ ከዚያም በጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመሆኑ ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣ፤ በማለት ሲጠይቅ የጀሚል ጠበቃ አቶ አህመድ ደግሞ “ይህ በጊዜያዊ ግጭት የተነሳ የተፈጸመ ግድያ ነው” አሉ።
በእርግጥም አቃቤ ህጉ ለራሱ ይበጁኛል ያላቸው ምስክሮች በሙሉ፤ በወቅቱ ስካር እንደነበር… ፀቡም ድንገተኛ መሆኑን ነው የመሰከሩት። ሆኖም አቃቤ ህጉ በወቅቱ ከአገር ውጪ የሄደውን፤ የ5ኛው ምስክር ቃል እንደፓሮት ይደጋግመው ጀመር። …“ተው” ሲለው እምቢ ብሎት ሄዶ መግደሉ ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ ያሰበበት መሆኑን ያሳያል” በሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ላይ ሙጥኝ አለ።
የዳኝነቱ ውሳኔ ምን ይመስል እንደነበር ከመግለጼ በፊት፤ እናንተም የዳኝነት ፍርድ ትሰጡ ዘንድ በጀሚል ያሲን ጠበቃ በኩል የነበረውን የመከራከሪያ ነጥብ ልጥቀስላችሁ። የመከላከያ ጠበቃው ፀቡ ሲነሳ መጀመሪያ የተማታው ኃየሎም መሆኑን የጀሚልም እርምጃ ራስን መከላከል እንደሆነ፤ ከዚህም በተጨማሪ ሲጠጣ ራሱን የሚጣላና የሚረሳ መሆኑን ምስክር በማቅረብ ጭምር ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል። ከምስክሮቹ መካከል የቀድሞዋ የጀሚል ያሲን ሚስት አንዷ ነበረች። በመጠጥ ምክንያት ስለሚረሳው ጉዳይ ስትመሰክር፤ “አንዳንድ ጊዜ መኪናውን አንድ ቦታ አቁሞ ሲጠጣ ያመሽና መኪና መያዙን ረስቶ፤ በኮንትራት ታክሲ ሲዞር አምሽቶ ይመጣል። ያቆመበትን ቦታ ስለሚረሳ ጠዋት ላይ ጓደኞቹና ሰራተኞች ተልከው መኪናውን ፈልገው ያመጡለታል።” በማለት ምስክርነቷን መስጠት ብቻ ሳይሆን በዚህ ባህሪው ትዳሩን እስከማጣት የደረሰ መሆኑን ምስክር ሆናለች።
አንባቢዎችን ማሰልቸት እንዳይሆንብኝ እንጂ፤ በጀሚል ያሲን ጠበቃ በኩል እንዲህ ያሉ በርካታ ምስክርነቶ ተሰጥተዋል። በእርግጥ በመጠጥ ምክንያት ሰው አዕምሮውን የሚስት መሆኑ እና የጀሚል ያሲን የአዕምሮ ጤንነት በሃኪም እንዲረጋገጥ፤ የተከላካይ ጠበቃ ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አደረገባቸው። ይህም “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።
የተከላካይ ጠበቃ በዚህ አላበቁም። በኢትዮጵያ ህግ መሰረት፤ የሰው ልጅ በስካር መንፈስ ሆኖ የሚፈጽመው ጥፋት ጤነኛ ሰው ከሚያደርገው ጥፋት ጋር እኩል አይታይም። በመሆኑም የጥፋት ማቅለያ አንቀጾች አሉ። ከነዚህ አንቀጾች ጀምሮ፤ በጀሚል ላይ የተፈፀመውን ድብደባ በመግለጽ ድርጊቱ የ“አልሞት ባይ ተጋዳይ” መሆኑን የኢትዮጵያን ወንጀለኛ መቅጫ ህጎች እየጠቀሱ ተከራከሩ። ይህም በመሃል ዳኛው አማካኝነት በወቅቱ ውድቅ ሆኖ ነበር።
ወደ ማጠቃለያዬ ከመሄዴ በፊት… ይህንን ለሚያነቡ ሁሉ ቀላል የህሊና ፈተና ልሰጣቸው ወደድኩ። “አሁን ከሞላ ጎደል ያዩትን እንኳን መሰረት ቢያደርጉ፤ በጀሚል ያሲን ላይ ሞት ይፈርዱበታል?” አንድ ነገርም ልጨምርበት። እንበል እርስዎ የኃየሎም ወዳጅ ነዎት፤ ጀሚል በፈጸመው ድርጊት ደስተኛ አይደሉም” ብለን እንገምት። እናም ከፖለቲካ፣ ከዘር እና ወገናዊነት እንዲሁም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጭምር ነጻ ሆነው ፍርድ ይስጡ ቢባሉ ምን አይነት ፍርድ ይሰጣሉ?
እርስዎ የህሊና ፍርድዎን እያሰላሰሉ ወደ ፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ አንደኛ ችሎት ልውሰዳችሁ። እኔ እና ሌሎች ጋዜጠኞች መታወቂያችንን እያሳየን፤ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ከገቡት ሰዎች መካከል ነን። ውጪ የነበረውን የህዝብ ብዛት ፍርድ ቤቱ የሚችለው አይመስልም። ነገር ግን ሰልፉ ከበራፉ አልፎ መንገዱን አጨናንቆት ነበር። ስነ ስር ዓት አስከባሪዎች በቅድሚያ የሟች የኃየሎም ቤተሰብና ጓደኞች እንዲገቡ አድርገው በፍርድ ቤቱ የግራ መደዳ አስቀመጧቸው። ከዚያም የጀሚል ያሲን ሰዎች… ሚስቱ፣ እህቶቹ፣ አባቱና ሌሎች ሰዎች ገብተው ተቀመጡ።
በሟች እና በገዳይ ቤተሰቦችም ፊትለፊት… አቃቤ ህጉ መስፍን ግርማ በግራ በኩል፤ የተከሳሽ ጠበቃ አቶ አህመድ በቀኝ ሆነው፤ መጽሃፍ፣ ሰነድና ማስታወሻዎቻቸውን ጠረጴዛዎቻቸው ላይ አድርገው፤ የዳኞቹን መምጣት ይጠባበቃሉ።
ጋዜጠኞች ከተቀመጥንበት አግዳሚ ወንበርና ጠረጴዛ ፊት ለፊት ተከሳሾች የሚቆሙበት ጉርድ ሳጥን አለ። ጀሚል ያሲን በፖሊሶችና በታጣቂዎች ታጅቦ… ወደዚህ እስረኞች ወደሚቆሙበት ሳጥን ውስጥ መጥቶ ሲቆም ፀጥታ መስፈን ጀመረ። አለባበሱ ቀለል ያለ ነበር። በቀኝ እጁ የ’ስላም መቁጠሪያ ይዟል። በፊቱ ላይ ምንም አይነበብም። በዝምታ ውስጥ ዝም ብሏል።
ሶስቱ ዳኞች ወደ ችሎቱ ገብተው ሲሰየሙ ህዝቡ ብድግ አለና ዳኞቹ ሲቀመጡ ሁሉም እንደገና ተቀመጠ። ሶስቱ ዳኞች ዛሬ የሚያሰሙት ውሳኔያቸውን ነው። የመሃል ዳኛው አቶ ደሳለኝ ዓለሙ ክብረት ችሎቱ ረፍዶ ስለተጀመረ ይቅርታ ጠይቀው በቀጥታ ወደ ጉዳዩ አመሩ። አቃቤ ህጉና የተከሳሽ ጠበቃ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው… የመሃል ዳኛውን ጥያቄ ይመልሱ ነበር። ተከሳሽ መቅረቡን የመሳስሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ፤ እነሱም ሲመልሱ ቆቱና በብዕራቸው ዳጎስ ብሎ በሚታየው ትልቁ መዝገብ ላይ እየጻፉ ነበር።  ዛሬ የውሳኔ ቀን የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ በንባብ ያሰሙ ጀመር። እርሳቸው ሲያነቡ ጀሚል ያሲን የያዘውን የ’ስላም መቁጠሪያ እየቆጠረ ከንፈሩ ብቻ እየተንቀሳቀሰ… ምናልባትም ፀሎት እያደረገ ነበር።
ከመሃል ዳኛው በቀኝ በኩል ያለው አቶ ተገኔ ጌታሁን አቀርቅሮ ይጽፋል። የአባታቸውን ስም የዘነጋሁት የግራ በኩል ዳኛ፤ ችሎቱ ውስጥ ያለውን ሰው ትክ ብለው ሲመለከቱ ቆጠራ የሚያደርጉ ነበር የሚመስለው።
ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ የመሃል ዳኛው አቶ ደሳለኝ ዓለሙ የአቃቤ ህግና የተከላካይ ጠበቃ ለውሳኔው ዝግጁ መሆናቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ጠይቀው ሲጨርሱ የፍርድ ውሳኔውን በንባብ ሊያሰሙ ተዘጋጁ። በዚህ አንደኛ ችሎት ውስጥ ያሉትን ዳኞች በጓደኝነት ሳይሆን በደንበኝነት አውቃቸዋለሁ። በጋዜጠኝነት ዘመኔ ከተከሰስኩባቸው 12 ክሶች መካከል አራቱ በዚህ ችሎት ይታዩ የነበሩ ናቸው። ከሌላው ችሎት አንጻር ይሄኛው ችሎት ለኔ ቀለል ይለኛል። ሌላው ቀርቶ በዚህ ችሎት ለአንድ ክስ የ500 ብር ዋስትና ከፍዬ ስወጣ፤ ሌሎች ችሎቶችን ግን ሶስትም፣ አምስትም ሰባት ሺህ ብርም ከፍዬ እንድወጣ ነው ያደረጉኝ። “ምናላት?” እንዳይሉኝ፤ ከ14 አመታት በፊት፤ 7ሺህ ብር ቢያንስ አንዲት ትንሽ ቤት ያስገዛ ነበር።
እናም ይህ ችሎት በጀሚል ያሲን ላይ ሊሰጥ የሚችለው ፍርድ ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል፤ የሚል እምነት ነበረኝ። የዳኞቹን ውሳኔ ከመግለጼ በፊት ያራስዎን ውሳኔ ይስጡ። ልብ ይበሉ። ከላይ እንዳልኩት  ዳኝነት ሲሰጥ ህሊናዎ ነጻ መሆን አለበት። ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካና ከዘር ጉዳይ ወይም ደግሞ ‘የወያኔ ሴራ፤ ሻዕቢያ ስራ’ ከሚለው ውጥንቅጥ ራስዎን ነሳ ማድረግ አለብዎ። ፍርድ የሚሰጠው ያሉትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ነው። በዚህም መሰረት እርስዎ “በጀሚል ያሲን ላይ የሞት ፍርድ ይሰጣሉ?ወይስ ስካር እና ጊዜያዊ ፀብ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የሞት ፍርዱን ያቀሉለታል?” የመሃል ዳኛው አቶ ደሳለኝ የፍርድ ውሳኔውን ማንበብ ቀጠሉ። ምስክሮች የሰጡትን ቃል እያነበቡ 1ኛ ምስክር ይሄን ብሏል… የተከላካይ ጠበቃ ምስክርም እንዲህ ብላለች። በመጠጥ ምክንያት… በጊዜያዊ ፀብ የተነሳ መሆኑን መስክረዋል… ሌላም ሌላም እያሉ ንባባቸውን ሲቀጥሉ… “በቃ ሞት አይፈረድበትም ማለት ነው” ብዬ አሰብኩ። ከኛ መቀመጫ ያለውን ጀሚል አሻግሬ ሳየው አንገቱን አቀርቅሮ፤ አቡሻክሩን እየቆጠረ፤ ከንፈሩ እየተንቀሳቀሰ ዝም ብሏል።
እርስዎም ውሳኔውን ከማንበብዎ በፊት ለጥቂት ሴኮንዶች ወይም ደቂቃዎች ያህል አይንዎን ጨፍነው፤ ከራስዎ ጋር ይነጋገሩና ፍርድ ይስጡ። የራስዎን ፍርድ ከሰጡ በኋላ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ልግለጽላችሁ።
የመሃል ዳኛው የፍርድ ውሳኔ ንባባቸውን ቀጠሉ፤ የምስክሮቹን ቃል በአጫጭሩ ሲያሰሙ ቆዩና… ‘ሆኖም’ አሉ። ‘ሆኖም’ ተብሎ ነገር ከተጀመረ መፍረሱ እንደሆነ ገብቶኛል። ‘ሆኖም’ ብለው ቀጠሉ። “ሆኖም“5ኛው ምስክር ‘ተው’ ሲለው… ‘እምቢ’ ብሎ ሟውችን ግንባሩ ላይ መትቶመግደሉ የሚያሳየው ጭካኔውን ነው” ከዚያም ቀጠሉ የመሃል ዳኛው፤ ሽጉጡን ከመኪናው ውስጥ ሄዶ አምጥቶ መግደሉ፤ ቀደም ብሎ አስቦበት የመጣ ለመሆኑ ምስክር ነው። ከዚያም… የገዛ እህቱን ምስክርነት አንስተው፤ “እቤት ከገባ በኋላ ሽጉጡን እና ጥይቱን እንድትደብቅለት መስጠቱ ጭካኔውን ያሳያል። በዚህም መሰረት በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 522/1/ሀ መሰረት በሞት እንዲቀጣ ሁለት በአንድ በሆነ ድምፅ ወስነናል።” ሲሉ ፍርድ ቤቱ ጭምር በድንጋጤ በድን ሆነ። “ነገር ግን” ብለው ቀጠሉ የመሃል ዳኛው።
ተስፋ ያጡት ቤተሰቦች አይናቸውን መሃል ዳኛው ላይ እንደሰቀሉ ማዳመጣቸውን ቀጠሉ። “ነገር ግን ይህ የሞት ውሳኔ የሚፀናው…” አሉና ህጉን ጠቀሱ። “ውሳኔው የሚፀናው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲፈርሙበት ነው።” በማለት ውሳኔያቸውን ሰጡ። ከዚያም ሰዉ ከመውጣቱ በፊት፤ በቅድሚያ እስረኛው ካቴና ገብቶለት፤ ከዚያም ዳኞቹ በራሳቸው የጎንዮሽ በር ወጡ። ጠበቆችና ጋዜጠኞችም በዚህኛው በር ስንወጣ… የመንግስት ጋዜጠኞች ውሳኔውን ለምሽቱ ዜና ለማቅረብ እየተጣደፉ ወጡ። እኔም በፍጥነት እርምጃ ከህንጻው ለመውጣት ተጣደፍኩ። የኔ ጥድፊያ ግን ከአንደኛ ችሎት መግቢያ በር ላይ ሊኖር የሚችለውን ትርምስ ለማየት ነበር።
ከህንጻው በፍጥነት ወጥቼ አንደኛ ችሎት በራፍ ላይ ስደርስ፤ የኃየሎም ቤተሰቦች እየወጡ ነበር። ውጪ ሆነው ይጠብቁ የነበሩት የጀሚል ቤተሰቦች ምን እንደተፈረደበት ገና አላወቁም። ድምጻቸውን ዝግ አድርገው በትግሪኛ ይነጋገራሉ። የኃየሎም ቤተሰቦች ወጥተው ካለቁ በኋላ መጀመሪያ የወጣችው የጀሚል ያሲን የቀድሞ ሚስት ነበረች። ድምጿ አይሰማም… ነገር ግን ሁለት እጆቿን ወደ ሰማይ ዘርግታ እንባዋ በጉንጮቿ ላይ እየወረደ ስትወጣ፤ ውጪ የነበረው ሰው አንገቱን ሰብሮ ማልቀስ ጀመረ።
የጀሚል የቀድሞ ሚስት ውጪ ከነበሩት ሰዎች ጋር እንደተገናኘች ለቅሶው በረከተ። ወዲያው ግን የጀሚል ያሲን አባት በትግሪኛ እየተቆጡ ተናገሩ። ምን እንዳሉ አላወኩም። ነገር ግን በጩኸት ሊቀጥል የነበረ ለቅሶ ጋብ አለ። እናም ከፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስንወጣ… ስንወጣ ቤተሰቦቹ እጃቸውን እያወዛወዙ ጎንበስ ቀና እያሉ ያለቅሱ ነበር። ግቢውን ሲወጡ የጀሚል ያሲን አባት፤ ከልጃቸው የቀድሞ ሚስት ጎን ለጎን ሆነው… አልፎ አልፎ እያፅናኑ እና እየተቆጡ… ድምጻቸው መጠኑን አልፎ ሳይሰማ እያለቀሱ እና እየተላቀሱ ግቢውን ሲለቁ፤ እኔም በዚያው ወጣሁ።
ቀደም ሲል የርስዎን ውሳኔ የጠየኩት ያለ ምክንያት አይደለም። እናስ ውሳኔዎ ምን ሆነ? “ሞት ይገባዋል” ብለው ከሆነ፤ ኢህአዴግ ከሰጠው ተመመሳሳይ የፖለቲካ ውሳኔ ጋር መሳ ለመሳ ገጠሙ ማለት ነው። በእርግጥ “መሞት አይገባውም” ብለው ከነበረም፤ ከኢህአዴግ በትር አያመልጡም። እንግዲህ ሁለት ንርጫ ከፊታችን አለ። መልሱ ግን አንድ ነው። “እውነትን ተናግሮ፤ የሚመጣውን መቀበል ወይም የፖለቲካውን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ የኢህአዴግን መስመር መከተል?” ምርጫው የርስዎ ነው።
የሞት ውሳኔው 2 ለ 1 በሆነ የድምፅ ልዩነት ሲፀድቅ፤ “በሞት የሚያስቀጣ ጥፋት አይደለም” ብለው ያሉት ዳኛ አቶ ግርማ ይባላሉ። ከዚህ ውሳኔ በኋላ ምንም ያህል ጊዜ ሳይቆዩ ስራቸውንም አቆሙ።
ሁለቱ ዳኞች በዚህ ውሳኔያቸው ብቻ ስልጣን አገኙ ማለት ውሸታም ያስብለኛል። ስለዚህ በሌላም የታማኝነነት ስራቸው ጭምር ብዬ ላስተካለው። እናም በሌላውም ታማኝነታቸው ጭምር በስልጣን ላይ ስልጣን አግኝተው እላይ ደርሰዋል። የመሃል ዳኛው አቶ ደሳለኝ ዓለሙ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ከስሜን የመጡ የፓርላማ ተወካይ ነበሩ። በወቅቱ ለፓርላማ ተመራጮች አጭር የህግ ኮርስ እየወሰዱ፤ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸው ነበር። እሳቸውም በዚያ መልክ የምስክርነት ወረቀት ያገኙ ናቸው። በደርግ ጊዜም በታችኞቹ ፍርድ ቤቶች አገልግለዋል። ኢህአዴግ አገሪቱን ኬቆጣጠረ በኋላ አቶ ደሳለኝ – የአቶ መለስ ዜናዊ ሚስት የአዜብ መስፍን ዘመድ ሆነው ተገኙ። የብዙ ጊዜ የዳኝነት ልምዳቸውና ዝምድናቸው አንድ ላይ ተገምዶ የከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ ብሎም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እስከመሆን ደረሰዋል። (በነገርዎ ላይ በኋላም በደህንነት ኃላፊው በክንፈ ገብረ መድህን ገዳይ፤ ሻለቃ ፀሃይ ላይ ሞት የፈረዱት እኚሁ ዳኛ ናቸው)
ሌላኛው ዳኛ አቶ ተገኔ ጌታሁን ናቸው። ህጉን ተምረዋል። ማስትሬታቸውንም የሰሩት እንግሊዝ አገር ነው። እንደዘመኑ ባለስልጣን የማጎብደድ ባህሪያቸው ደስ አይልም እንጂ፤ የህግ እውቀቱ እንዳላቸው ይነገራል። በተለይ በጋምቤላው እልቂት ጉዳይ የሰጡት ዳኝነት በነመለስ ዘንድ ተወዳጅ እንዳደረጋቸው ይነገራል። በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ሌሎችም ስልጣናቸውን ሲረከቡ ቃለ መሃላ የሚያስፈጽሙት አቶ ተገኔ ጌታሁን ናቸው።
ምሽቱን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ዜና እንደማንኛውም ሰው በሬዲዮና በቴሌቭዥን ሰማሁ። ይህ ዜና የኃየሎምን ሙት አመት ለማክበር ትግራይ ውስጥ እየተዘጋጁ ላሉት ሰዎች፤ መልካም ዜና ሊሆናቸው ይችል ይሆናል። ዜናውን ተከትሎ በማግስቱ ሌላ ዜናም ሰማን። አቶ መለስ ዜናዊ የኃየሎምን (አሁን የተሰራውን ሳይሆን የመጀመሪያውን) ሃውልት ለመመረቅ ወደ ትግራይ መሄዳቸው በዜና ተነገረ።
የኃየሎም ገዳይ ጀሚል ያሲን የወቅቱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሞቱ ውሳኔ ላይ እስከሚፈርሙ ድረስ በህይወት መቆየት ይችላል። ከዚህ በኋላስ ግን ርዕሰ ብሔሩ ፈረሙ? አሟሟቱስ ምን ይመስላል? በሚቀጥለው ሳምንት እንመለስበታለን።
ስለሙት አመቱ እና የሃውልት ምረቃው ስነ ስርዓት ጥቂት ለማለት አሰብኩና ተውኩት። በዚያ ፈንታ በሚቀጥለው ሳምንት የመጨረሻውን ክፍል ከማስነበቤ በፊት የማተኩርባቸውን ጉዳዮች ልግለጽላችሁ።
–    በዚህ የፍርድ ሂደት መካከል የኢትዮጵያን የ ኤርትራ ጦርነት መከፈቱና ከዚያ ጋር ተያይዞ በሰራዊቱ ውስጥ የነበረው ውጥረት እና የነበረውን ጫና እገልጽላችኋለሁ። መቀመጫው 4ኛ ክፍለጦር የነበረው… በወጣቶች የተገነባው 22ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ወደ ባድመ ዘምቶ መደምሰሱን እናወጋለን። ሰራዊቱም “ሻዕቢያ በመጀመሪያ ኃየሎም አስገደለች… አሁን ደግሞ በመለስ ዜናዊ የተሾሙት በሻምበል እና በሻለቃ ደረጃ ያሉት መኮንኖች ጦሩን አስጨረሱት።” የሚል ተቃውሞ አቅርበው፤ “ጥያቄያችን ካልተመለሰ አንዘምትም።” እስከማለት መድረሳቸውን እንመለከታለን።
ከዚያም ሳሞራ የኑስ ብርጋዲየር ጄነራል ተብሎ ሲሾም… አልፎ በትግሪኛ አንድ ግጥም ተቀርጾ ተበተነ። ህዝቡንም ሰራዊቱንም ያነሳሳ ግጥም ነበር።

ሳሞራ ሕኪ ቁሪ አትዩካ፤

 ጄኔራል ተባሂልካ ክምቀካ?” ተባለ።

በሚቀጥለው ሳምንት ሌላውንም ግጥም ጨለፍ አድርገን እናስነብባችኋለን።
ከዚያም የጀሚል ያሲንን አሟሟት፤ የኑዛዜውን የኑዛዜውን ቃል… በመጨረሻ እኔም ቤተሰቡ ጋር ሄጄ ሳለ፤ ያጋጠመኝን ያልታሰበ ሁኔታ በሚቀጥለው ሳምንት እንጨዋወታለን።
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close