እራሱን ስላቃጠለው ወጣት ዝርዝር ዘገባውን ስሩልን ብላችሁ ለጠየቃችሁን እንደገና ለመስራት ሞክረናል ይመልከቱት ፣ኢትዮጵያዊ የለውጥ አራማጅ/አክቲቪስት/ ታጋይ ወጣት በዳዉሮ ዋካ ራሱን አቃጠለ

ሞሃመድ ቡዐዚዝ የሚባል ቱኒዚያዊ ወጣት በአገሪቱ ላይ በተንሰራፋው የአመራር ብልሹነት፣ጎሰኝነት፣ሙሰኝነት፣ሥራ አጥነት፣ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት፣በአገሪቱ መሪ የአንባገንነትና መድሏዊ አስራር የተነሳ ተስፋ በመቁረጥ ራሱን ነዳጅ አርከፍክፎ በማቃጠል የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ዛሬ ለምናየው የሰሜን አፍሪካና የአረብ አገሮች ህዝባዊ ማዕበልና ፖለቲካዊ ለውጥ መነሻ በመሆን ዓይነተኛ አስተዋጸኦ አሳድሮ አልፏል።

እነሆ ሌላ ኢትዮጵያዊ የለውጥ አራማጅ/አክቲቪስት/ ታጋይ ወጣት በዳዉሮ ዋካ ተከሰተ። ወጣቱ የኔሰው ገብሬ ይባላል። ሥራው መምህር ነው። ዕድሜው ወደ ሃያዎቹ ማገባደጃ አካባቢ የሚገመት ወጣት ነው። ወጣቱ በትምህርቱ ጎበዝ፣በተማሪዎቹ ዘንድ የሚከበርና የሚወደድ፤ከፍተኛ የህዝብ ፍቅር ያለው፣ትሁትና በደልን አጥብቆ የሚጠላ፣ሰውን አክባሪ፤በሚሰሩት ህገ ወጥ ሥራዎች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከድርጊታቸው የተነሳ አጥብቆ የሚጠላ፤በየስብሰባው የሚተቻቸው ደፋር ሰው ነው። እሱና የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አብረን አንድ ት/ቤት ሰርተናል።የግል ብቃቱንም ሆነ አቋሙን በደንብ አውቃለሁ።

የህዝባዊ አመጹን ዋና ዋና መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በጥቂቱ ላውጋችሁና ወደ ወጣቱ ጀግና ታሪክ እመልሳችኋለሁ።

የዳዉሮ ዋካ ህዝብ የዴሞክራሲ፤ የፍትህ፤ የመልካም አስተዳደር፣የልማት፣እንዲሁም የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና የወረዳ የአስተዳደር እርከን እንዲፈቀድለት ጥያቄ በማንሳት ከፍተኛ ህዝባዊ አምፅ እያካሄደ መንግስትን በማስጨነቅ ላይ ነው።እንቅስቃሴዉን መንግሥት ለማቆም ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም መልኩን እየቀየረና ወደ ለሎቹም ወረዳዎች እየተዛመተ ካድሬዎቹን አስጨንቋቸዋል። ህዝቡ የተማረረና በመንግሥት ላይ ተስፋ የቆረጠ መሆኑን በአደባባይ እየነገራቸው ነው።

ሥርዓቱ ከፈጠረው ህዝብን ሆን ብሎ ያለማረጋጋቱ በተጨማሪ አንዳንድ የወረዳና ከዚያ በላይ በሆነ እርከን ተሹመው የራሳቸዉን ጥቅም ከማየት ወዲያ ህሊና ያልታደላቸው ሆድ አደሮች የህዝቡን

ጥያቄ የሚያፍኑበት ምክንያት ምንድር ነው? እስቲ የሚመስለኝንና የማውቀዉን አንድ ሁለት ልበላችሁ።

1. በነባር የወረዳ ርዕሰ ከተማ ዋና ዋና መንገዶችን የተከተሉ ለንግድ ሥራ አመቺ የሆኑ ሥፍራዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ቀድመው ተይዘዉባቸዋል። እነርሱ በለስ ቀንቷቸው ወደ ሥልጣን ሳይመጡ ቀደም ሲል ነባሩ ህዝብ ይዞታል ሥፍራዉን።ይህ ደግሞ ባለዘመነኞቹ የራሳቸዉን የግል ገቢ ማግኛ ሥራ እንዳሻቸው ለመሥራትና አዳዲስ ግንባታዎችን ለማካሄድ አልተመቻቸዉም።ስለዚህ ነባር የወረዳ ዋና ከተማዎችን ወደ ሌላ ሥፍራ ማዛወርና ወረዳዉን ወደ ሚመቻቸው ማንሳትን እንደ ብቸኛ መፍትሄ መርጠው ነው ሲሰሩ የቆዩት። ይሄ በሁሉም የዳዉሮ ወረዳዎች ተመሳሳይነት ያለው ችግር ነው። በተለይ የዋካ ከተማ በዚህ ምክንያት ለልማት አልተመቸችንም በሚል የዉሸት ዘፈን እያዜሙ ባለሥልጣኖቹ ራሳቸዉን የማልማት ህቡዕ ፖሊሲ ለማሳካት ሲሉ የወረዳ ከተማነትዋን ነስተው፤ ማህበራዊ ተቋማትን ከአብዛኛው ህዝብ ነጥቀዉበት፤ ከላይ እስከ ታች አንድ ሆነው በጥቅም ተሳስረው አሳሩን ያሳዩታል።

2. አዲስ በመሠረቷቸው የወረዳ ከተሞች አመቺ ነው ብለው የገመቱትን የመኖርያና የንግድ ሥፍራ በተለያየ መንገድና የቤተዘመድ ሥም ተቆጣጥረዉታል፤ የግንባታ ቦታ በሥልጣናቸው ወስደው ጥቂት የማይባል የመኖርያ ቤት ሰርተዋል፣የንግድ ድርጅት አቋቁመዋል።በማከራየት ገቢያቸዉን አሳድገዋል።በተለይ ዋካ ከተማን የወረዳ ነፃነትዋን ነፍገው ወደ ሌላ ቦታ ርዕሰ ከተማውን ያዛወሩ የዞንና የወረዳ ባለሥልጣናት ዋና ተጠቃሽ ናቸው።ፍትህ ቢኖር ዳኝነቱ አድካሚ አልነበረም።ህዝቡን እያደሙና እየበደሉ፤ በሃዘኑና በእንባው እነርሱ ሃብት በማከማቸት እየበለፀጉ ይገኛሉ። የአሁኑ ህዝባዊ አምፅም በእነርሱ ሥራና የእነርሱን የሥልጣን ዕድሜ ለማሳጠር ይመስላል።ዉሎ ያድራል እንጂ ለዛሬው የህዝብ እንባ ነገ ዋጋ ይከፍሉበታል።

3. አዲስ የከተሙዋቸው መንደሮች /የወረዳ ከተሞች/ የተቋቋሙበት ሥፍራ ውሳኔዉን ያስተላለፉ ግላሰቦች ለቤተሰቦቻችውና ለትውልድ ቀዬአቸው ይቀርባል ብለው ወዳሰቡበት ሥፍራ መሆኑ የበለጠ አሳዛኝ ነው። የወረዳ ዋና ከተማ ወደ ትውልድ መንደር ማቅረብ የሚል ሃሳብ እንደመስፈርት ማገልገሉ ይገርማል። በአንድ ወቅት በግምገማ ላይ ትክክልም ይሁን ስህተት ይህን የመወሰን ጉልበት 3

ባለኝ ጊዜ በቀላሉ በማንም የማይታረም፤ በግሌ የምደሰትበትን ሥራ ሰርቻለሁ ብሎ መልስ የሰጠ አስተዳዳሪ እንዳለ መስማቴ ትዝ ይለኛል። ይህንን አንድ

ቀናነት የጎደለው ካድሬ የወሰነውን ሺባ ውሳኔ ህዝብን ይቅርታ ህዝቡን ጠይቆ እንደማረም ያስነቡታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የየወረዳው ህዝብ በዚህ ህገወጥ ዉሳኔ የተነሳ ያጣዉን ነገር ትንሽ ላመላክታችሁ።

1. የመንግስት መስሪያ ቤት በሙሉ ወረዳዉን ተከትሎ በየጊዜው ከቦታ ወደ ቦታ በመፈራረቁ ለህዝቡ የተሰራው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለ ጥቅም እንዲወድሙ እየተደረገ ነው።አንድ ሥፍራ የተሰራውና የተገነባው ተቋም ባለሳምንቱ ካድሬ ከተማዉን አንስቶት ወዳሻው በወሰደ ቁጥር ተጠቃሚ የለምና ይወድማል።የግለሰቦችን ቤት፣ ንብረት አላልኩም፤ልብ በሉ። እሱን አታንሱት። በተለይ የመንግስት ሰራተኛውማ ሲያፈርስ፣ሲገነባ ዕድሜዉን ቅርሱን አውድሞ ይኖራል።ምን ያድርግ! መ/ር የኔሰው በዋናነት ይህ አሰራር ትክክል አይደለም በሚል አጥብቆ ሲቃወም ነበር።

2. የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከህዝቡ ሸሽተው ህዝብ በሌለበት ባዶ ሥፍራ ላይ ይገነባሉ።ለ31 ቀበሌ ህዝብ አማካይ ቦታ ላይ ሆኖ እያገለገለ ያለን ከተማ አንስተዉበት ህዝቡ ሲጨነቅ በማንአለብኝነት ሁለት ቀበሌ ለማይሞላ ህዝብ ሆስፒታል ይገነቡለታል። ለምን የሚል ህግ፤ ተው የሚል ሥርዓት የለም።ህዝቡ በሌለበት የህክምናና ሌሎች ተቋማት በከፍተኛ ወጪ እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑ ያሳዝናል።ህዝቡ የሚሰራው ተቋም ለእኛ ነው ወይስ ለጦጣና ለዝንጀሮ? የሚል ጥያቄ ያነሳል።

አንድ አርሶ አደር አንድ ቀን በስብሰባ ላይ ይህን ጥያቄ  ጠየቀ። ይሄ ሆስፒታል የተሰራው ለማነው? የሚል።መልስ ይሰጠን አለ።ብዙ ተጠቃሚ በሌለበት ማለቱ ነው። ባለሥልጣኑም በቂ መልስ መስጠት ባለመቻሉ ይመስላል ዝም አለው።ሌላው አርሶ አደር እንዲሁ እጁን አወጣና የትም ቢሰራስ ምን አለበት፤ልማት ነው የሚፈለገው፤ ምን አገባህ፤ ይለዋል ጓደኛዉን የመጀመሪያዉን ጠያቂ፤ አልጨረሰምና ቀጠለ ጥያቄዉን።አመራሮቻችን በቂ ህክምና እንዳይኖራቸው

ትፈልጋለህ እንዴ? ሲል ሃሳቡን አራዘመው። የመጀመሪያው ጠያቂ እንደገና አይ ወንድሜ እነርሱኮ አዋሳና አዲስ አበባ ሄደው ይታከማሉ፣የእኛ ነው እንጂ ችግሩ አለውና መለሰለት። አከታተለና ታክመን እንዳንድን የህክምናዉን ስፍራ

በሌለንበት ገንብታችሁ ለራሳችሁ ወሰዳችሁት። ምናለ እንደዚሁ ሞትንም እንደከተማው አንስታችሁ ብታመጡና ብትወስዱት፤መቼም አልታደልንምና ሞተን የምንቀበርበትን ቤተ ክርስቲያናችንን አንስታችሁብን አስከሬን እዚህ ድረስ አምጥታችሁ ነው የምትቀብሩት እንዳትሉን ነው የምንፈራው ብሎ ማለቱን ሰምቻለሁ። እውነት እኮ ነው። ለምን ህዝብን አላግባብ ትበድላለህ የሚል የበላይ ያጣ ህዝብ…ያሳዝናል። ቢቸግረው ሞትንም እባካችሁ ውሰዱት አለ አርሶ አደሩ።

3. የተመሰረተው የወረዳ ከተማ በፍጹም ህዝቡን አያማክልም።እንዳጋጣሚ ሆኖ በሁሉም ወረዳዎች ማለት ይቻላል። ህዝቡ ያለው ደጋ ከሆነ የወረዳ ከተማዉን ብድግ አድርገው ወደ ቆላ ወስደዉታል። ምሳሌ ዋካንና የሎማ ባሌ ከተማን ቶጫን መጥቀስ ይቻላል።

4. የመጠጥ ዉሃ ለከተማ ምስረታ ትልቅ መስፈርት ነው። ከተማ ሲመሰረት ውሃ ወዳለበት አቅራቢያ ነው ወይስ ውሃ ወደሌለበት? በዳዉሮ ተጨባጭ ሁኔታ ስናየው ተቃራኒው ነው የሆነው።ዋካ በመጠጥ ዉሃ የታደለ ነው።የቧንቧ አገልግሎት ሳይኖራት ንጹህ የምንጭ ዉሃ በተፈጥሮ የታደለች ከተማ ናት ዋካ።አዲስ የተከተመው የተርጫ ከተማ ደግሞ በመጠጥ ዉሃ እጥረት ነዋሪው ፍዳዉን ያይበታል። ባለጊዜዎቹ በመንግሥት መኪና ከዋካ ንጹህ ዉሃ እያመላለሱ ይጠቀማሉ።በጠራራ ፀሃይ፣ ቀን ህዝቡ እያየ ውሃ ይጋዛል በመኪና፤ ሌላው የመንግስት ሠራተኛ በዉሃ ጥም፣በዉሃ እጥረት ይሰቃያል። ለመጠጥ ነው ልብ በሉ ገላ ለመታጠብ አላልኩም። ለሎችም ወረዳዎችም ችግሩ ተመሳሳይ ነው።

5. ለማንኛዉም ጉዳይና አቤቱታ የሚመላለሰው ህዝብ ከሌለው ላይ ከትራንስፖርት ወጪ ጀምሮ ያወጣል። ምሳው አዳሩን ገምቱ። ገቢው በአብዛኛው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለባለሥልጣናቱ ነው የሚገባው።

እንግዲህ ፍልሚያው በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ ነጋዴዎችና በደሃው፤አልበዘበዝም በሚል ህዝብም ጭምር መሆኑን አስተዉሉ። የወረዳ ማእከል

ጥያቄ እንግዲህ በባለሥልጣኞች ጥቅም ዙሪያ የታጠረ ነው።ለዚህ ነው ሆን ብለው የሚያወሳስቡት።ይህ ነው ከሞላ ጎደል ህዝቡን ለአመፅ የዳረገው። ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ስላሉ ሌላ ጊዜ በሌላ አጋጣሚ ብቅ እላለሁ። አሁን ወደ ዳዉሮው ሞሃመድ ቡዐዚዝ ልመልሳችሁ።የኔሰው ገብሬ። ከላይ በጠቀስኩትና በሌሎች ምክንያቶች የህዝብ ተወካዮች የሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ይመረጡና ከወረዳ ጀምረው ፣ዞንም አመልክተው፣ ክልልም ጎራ ብለው አመልክተው ለነገሩ መፍትሄ እንዳላገኙ በተረዱ ጊዜ አቤቱታቸዉን  ወደ አቶ መለስ ዜናዊ ይዘው አቀረቡ። ልብ በሉ፤ባለፈው አንድ ወር ወዲህ የሆነ ነገር ነው የማወራችሁ። ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ጉዳዩ ታይቶ በክልሉ አስተዳደር በኩል ምላሽ በቶሎ እንደሚሰጣቸው ትነግሯቸው ወደ ዋካ ይመለሳሉ። ዋካ በደረሱ በሶስተኛው ቀን ለአቤቱታ መጥተው ከተመለሱት ያገር ሽማግሌዎችና የህዝብ ተወካዮች መካከል ሶስቱን ፖሊስ ይይዛቸዋል። የያዛቸውም ቦታ ደግሞ አንድ ታዋቂ የሆኑ የዋካ ከተማ ነዋሪ አርፈው ኑሮ ከዋካ ቅ/ማርያም ቤ/ክ/ የቀብር ሥፍራ እያቃበሩ ሳለ ነው ፖሊስ የያዛቸው። እሱን ተከትሎ ነው ጉድ የፈላባቸው። ከቀብሩ መልስ አንድ ሰው ሳይቀር ለቀስተኞቹ እንኳ አልቀሩ በሙሉ ህዝቡ ተሰልፎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተጉዞ የፖሊስ ጣቢያዉን ይከብና ይቆጣጠረዋል። ለ31 ቀበሌ ህዝብ ተወካዮችህ ታስረውልሃል የሚል መልእክት በአስቸኳይ ተላለፈ።ህዝቡ ወደ ዋካ ተመመ። ፖሊስ ጣቢያዉን ቀድሞ የከበበው ህዝብ ሌሊቱን በሙሉ ጣቢያዉን ከቦት አደረ። ምኑ ቅጡ! ተጨማሪ ሃይል ይላካል። ህዝቡን የበለጠ ነገሩ አስቆጣው። አመራር ተብዬዎች ከወረዳና ከዞን መጡ።ህዝቡ መኪናቸዉን በድንጋይ አመድ አድርጎ አባረራቸው።የሮጠዉም ሮጦ፤ አንዳንዱም በህዝቡ እግር ላይ ወድቆ ለምኖ ህይወቱን አተረፈ።

ከየቀበሌው የተመመው ህዝብ የመሰብሰቢያ አደባባይ /ሜዳ/ በአቅራቢያው ስለነበር ተሰብስቦ መፈክር እያስተጋባ ብሶቱን ገለጸ።መልካም አስተዳደር አጥተናል፤ዴሞክራሲና ፍትህ የለም፤የወረዳ መዋቅራችን በአስቸኳይ ይመለስልን፤ሙሰኞች ይውደሙ፤ለውጥ ያስፈልገናል! የሚሉ መፈክሮች ተስተጋቡ። ሁኔታው ከቁጥጥር ወጣ። ከፌደራል አድማ በታኝ ፖሊስ በብዛት ተጭኖ በማግስቱ ሌሊት ገባ። በብዙ ድካምና በጉልበት ህዝቡ ወደ ቤቱ እንዲገባ፤ ጥያቄያቸው መፍትሄ እንደሚያገኝ ተነግሮ ሁኔታዉን ለማቀዝቀዝ

ተሞክሯል። ችግሩ እንዳለ ነው አሁንም። ትዝ ያለኝ ጣሂር አደባባይ ላይ የተካሄደዉ የህዝብ አመጽ።አልበተን ያለ የህዝብ ቁጣ።የዋካ ህዝብ በሌሎች ወገኖቹ ቢታገዝ ኑሮ ጥሩ ነበር።

የኔሰው ገብሬም ይህንን አመጽ ተቀልቅለህ የመንሥትን ባለሥልጣኖች አውግዘሃል፤መፈክር አስተጋብተሃል፤አደራጅተሃል ተብሎ ነው ከሌሎች በርካታ ወጣት ጓደኞቹና ከሀገር ሽማግለዎች ጋር የታሰረውና ከሳምንታት በኋል የተፈታው።በርካታ ጓደኞቹ እስካሁን እስር ላይ ናቸው።

ባለፈው አርብ እለት እስር ላይ የነበሩና አመጹን አስተባብራችኋል የተባሉ ጓደኞቹ በ 29-03-04 ወደ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። ይለቀቃሉ ወይም በዋስ ይወጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ የጊዜ ቀጠሮ በሚባል የተቃዋሚ ኃይል ማንገላቻና ማፈኛ ዘዴያቸው ተጠቅመው ወጣቶችን ዳግም ወደ ወህኒ ቤት ይመልሱዋቸዋል። የኔሰው ከእስር ቀድም ሲል ተፈቶ ነበርና የዳኞችን ተውኔት አይቶ በጣም አዝኖ ከፍ/ቤት ወጥቶ ይሄዳል። የሄደውም ወደ አስተዳደር ነበር። በዚሁ ጉዳይ ግምገማ ብለው አዳራሽ ዘግተው ቁጭ ብለው አገኛቸው።

በስብሰባው ላይ የክልል፣ የዳዉሮ ዞንና የወረዳው ባለስልጣኖች ሁሉም ነበሩበትና የስብሰባዉን አዳራሽ በር በርግዶ ገብቶ ጥያቄ አቀረበላቸው። ለምን እንደታሰርኩና ለምን እንደተፈታሁ ምክንያቱን ብጠይቅ ዳኛውም አላውቅም አለ። ፖሊሱም፣ዐቃቤ ህጉም እናንተም አናውቅም እያላችሁ ታላግጣላችሁ። በጣም ያሳዝናል!  ህዝቡን እንደዚህ እንደፈለጋችሁት የምትጫወቱበት እስከ መቼ ድረስ ነው? እዚህ ነፃነት ነሳችሁን፤የበላይ አካል ተብዬ የህዝቡን ችግር ለመፍታት የማይፈልግ ሆነ። ሌላ እናንተን መታገያ ማስወገጃ መንገድ ጠፋ፤ብሎ ንግግሩን ወጣቱ ሳይጨርስ ከስብሰባ አዳራሽ እንዲወጣ ተደረገ። በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ስላጣ በሁኔታው በጣም ተናድዶ የመጨረሻ ዉሳኔ ላይ ደረሰ።

ዉሳኔውም ቀደም ሲል ህዝቡ በዋካ ከተማ ህዝባዊ አመጽ ላይ ያስተጋባዉን መፈክር እንደገና በድፍረት በማሰማት፤ፍትህና ዴሞክራሲ አጥተናል፤በአገራችን በነጻነት መኖር የማይቻል መሆኑን በማረጋገጤ ሌሎች ጓደኞቼ ተባብራችሁ ለውጥ ለማምጣት እንድትታገሉ ለአርአያነት ራሴን መስዋእት አድርጌአለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ ይዞት የነበረውን ቤንዚን በላዩ ላይ አርከፍክፎ ራሱን በእሳት አቀጣጠለው።

በአጋጣሚ በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ትሯሩጠው በመከራ ህይወቱን ለማትረፍ ሞክረዋል። አሁን ተርጫ ሆስፒታል ተኝቶ በሞትና በህይወት መካከል ይገኛል። የዳዉሮ ዋካው የነፃነት አርበኛ መምህር የኔሰው ገብሬን ቀጣይ ሂደት እንዲሁም

ስለ ዳዉሮ አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እዘግብላሽኋለሁ። ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጀምሮ ያለው የበላይ ባለሥልጣናት ህዝቡ ብቃት ባለው የዉሳኔ ሰጪ አካል እንዳይመራና ልማት አካባቢዉን በማሳጣት የሚሰሩትን ደባ በቀጣዩ መጻጽፌ አቀርባለሁ።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close