በእግር ኳሱ ሶማሊያን በማሸነፋችን እንመጻደቅ? ከሔኖክ ዓለማየሁ


 የአዲስ አበባ ስታዲየም የመሮጫ ትራኩን ለአትሌቶቹ መለማመጃነት አስቀርቶ መሃል ሜዳውን በቆሎ ቢዘራበት በኢትዮጵያ  ረሃብ ከተጠቃው ሕዝብ የተወሰነውን ሕዝብ ማጥገብ ይቻል ነበር” በማለት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ውጤት ማጣት የተናደደ ኢትዮጵያ አስተያየት መስጠቱን የሰሙት ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በግብጽ 5ለ0 በተሸነፈችበት ወቅት  “ቀኑን ሙሉ ነው እንዴ የተጫወቱት?” ሲሉ ቀልደዋል እየተባለ በሰፊው ይፈተል ነበር።
ቅዳሜ ኖቬምበር 12 ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ማጣሪያ ለመጫወት  ኢትዮጵያ ከሱማሊያ ጋር ትጫወታለች የሚለው ዜና ቀልቤን ገዝቶታል። እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኖርዌይ አስመጣሁ ብሎ የቀጠረውን አሰልጣኝ አባሮ በምትካቸው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ቢሾምም ሶማሊያን ዘንድሮ እንኳ ያሸንፍ ይሆን ብዬ ነው ውጤቱን የጠበቅኩት። እርግጥ ነው ጅቡቲ ላይ 0ለ0 የተለያየው ብሄራዊ ቡድናችን አዲስ አበባ ላይ 5ለ0 አሸንፏል። በብራዚል አስተናጋጅነት የሚደረገው የዓለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ ታልፋለች የሚለው ህልሜ የጨለመው ሱማሊያን አሸንፋ
ከደቡብ አፍሪካ ጋር መደልደሏ ነው። ይሄ የኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችሁም ህመም ነው።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለምን አያድግም? ለምን ቁል ቁል ወደ ኋላ ይወርዳል? የሚለውን ለመዳሰስ ስዳክር ለእግር ኳ ሳችን ውድቀት
የሆኑትን የራሴን ምክንያቶች እንዲህ ዳሰስኳቸት፦
የውጭ አሰልጣኞችን መናቅ
ከ10 ዓመታት በፊት (በ1993 በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ኢትዮጵያ በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ጋርዚያቶ
አማካኝነት ጥሩ እግር ኳስ እየተጫወተች መልካም መስመር ላይ ደርሳ ነበር። እኚህ አሰልጣኝ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
“የአፍሪካው ብራዚል” እስኪባል ድረስ አርጀንቲና ላይ ተደርጎ የነበረው የዓለም ወጣቶች እግር ኳስ ውድድር ላይ ምርጥ ጨዋታ እንዲያሳይ አድርገውትም ነበር። እኚህ አሰልጣኝ ብሄራዊ ቡድናችንን ለዓለም ወጣቶች ዋንጫ ውድድር ቢያበቁትም፤
የሃገሪቱን ብሄራዊ ቡድን ይዘው ምንም ውጤት ሊያመጡ ባልቻሉ ሃገር በቀል አሰልጣኞች ይተቹ ገቡ።
በተለይም የቀድሞው የቡና አሰልጣኝ ስዩም አባተን ጨምሮ “አዋቂ” ነን በሚሉ አሰልጣኞች
“የጋርዚያቶ አጨዋወት አጭር ቅብብል የበዛበት ነው፤ አሰልጣኙ ተጫዋቾቻችንን የእግር ኳስ ጥበብን ሳይሆን የጉልበት ሥራ እያስተማራቸው ነው” እየተባሉ ይተቹ ገቡ።
እርግጥ ነው ብሄራዊ ቡድናችን ከሚተችባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የተጫዋቾቻችን ቅጥነትና ሃይል ማጣት ነው። ከሌላ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ሲጫወቱ የኛዎቹ በአካል ብቃት አነስ ብለው መታየታቸው የገባቸው ጋርዚያቶ ጉልበት እንዲያዳብሩ ያንን የአሰለጣጠን ዘዴ መከተላቸው አግባብ ነው የሚሉ የስፖርት ተንታኞች በሰፊው በወቅቱ ተደምጠው ነበር። ጋርዚያቶ በኢትዮጵያውያን አሰልጣኞችና የፌዴሬሽኑ ባለስልጣናት ጥርስ ውስጥ በመግባታቸው የተነሳ አርጀንቲና ላይ ለዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ወጣት ብሄራዊ ቡድናችንን ለተሳታፊነት ማብቃታቸው ከግምት ውስጥ ሳይገባ “ተንኮል” ሊባል በሚችል መልኩ እንዲሰናበቱ ተደረገ።  እሳቸው ከተሰናበቱ በኋላ የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን ለሃገራችንን
ከዓመታት በኋላ ጋርዚያቶ ያዘጋጀውን ቡድን አስራት ሃይሌ ይዞ ቢያመጣውም፤ አስራት ከዚያ በኋላ ጠንካራ ቡድን ሊሰራ አለመቻሉ ጋርዚያቶ
ምን ያህል ውጤታማ አሰልጣኝ እንደነበር እንዳንዘነጋው አድርጎናልል።
ጋርዚያቶ የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን በአካል ብቃት እንዲጠናከር በማድረግ ተጋፍጦና በተሻለ ሞራል እንዲጫወት በማዘጋጀት እንዲሁም 
ከዘመናዊ እግር ኳስ አጨዋወት ጋር በማስተዋወቅ ረገድ ያሳዩት ፍንጭ በአገሪቱየስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ አድናቆት ቢያተርፉም
ከስራቸው ሲሰናበቱ “የተወሰኑ ሰዎች አላሰራ” አሉኝ ከማለት በቀር የተናገሩት ነገር የለም። ሆኖም ግን በወቅቱ ከነበሩት
የፌዴሬሽኑ መሪ ጸሓዬ ገብረ እግዚአብሄር ጋር ሊግባቡ እንዳልቻሉ አንዳንድ ጋዜጦች ሲጽፉ እንደነበር አስታውሳለሁ።
ከጋርዚያቶ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጀርመናዊ አሰልጣኝ ቀጥሮ ነበር። ጆሃን ፊገ ይባሉ ነበር።
እኚህ አሰልጣኝ በ1995 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን
በወር 9 ሺህ ዶላርእየተከፈላቸው ለማሰልጠን ሕጋዊ የሆነ ኢንተርናሽናል ውል  ፈጽመው ነበር።
ውሉን ሲፈጽሙ ታዲያ ከብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት በተጨማሪ ሊሠሩ የገቡባቸው ግዴታዎች ነበሩ። ከነዚህም መሃል 
የኢትዮጵያ ታዳጊብ/ቡድንን በአማካሪነት ማገልገል የሚለው አንዱ ነው። አሰልጣኝ ጆቫን ፊገ በገቡት የውል ግዴታ መሠረት ከታዳጊ ቡድኑ ጋር ለመሥራት የቡድኑ ልምምድ ሜዳ ድረስ ተጉዘው ለቡድኑ የተመረጡትን ተጨዋቾችከተመለከቱ በኋላ ለመሥራት ፍቃደኛ አለመሆናቸ ውን 
ለፌዴፌሽኑ ኃላፊዎች  ያወጡት ጉድ ሃገርን አስገርሞ ነበር።
የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን  በወቅቱ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ 
ከ30 በላይ ተጫዋቾችን በመምረጥ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ጉልላት ፍርዴ አማካኝነት ዝግጅቱን ጀምሯል።
ለታዳጊ ቡድኑ ተጨዋቾቹ የተመረጡት ከክለብ ዋና፣ ወጣትና ፕሮጀክት ሰልጣኞች ዕድሜያቸው ይመጥናል ተብሎ የታመነባቸው ናቸው።
 ይሁንና ጀርመናዊው አሰልጣኝ ለታዳጊ ቡድኑ የተመረጡት ተጨዋቾች አብዛኞቹከ17 ዓመት በላይ እንጂ በታች 
አይደሉም በሚል “እኔ የፊፋ ኢንስትራክተር ነኝ፤ ፊፋ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የዕድሜ ማጭበርበርን አጥብቆ ይቃወማል፣ ያወግዛል።
 እኔም ይሄን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆንግዴታ አለብኝ።
 ይሄን ሳላደርግ ብቀር ፊፋ የዕድሜ ማጭበርበር ሲደረግ ዝም ብለሃል፤
 ደግፈሃል በሚል የኢንትራክተርነት ማዕረጌን ይነጥቀኛል። ስለዚህ ትክክለኛ ዕድሜ ያላቸው ተጫዋቾች እስካልተያዙ ድረስ አልሰራም”
በማለት በማመጻቸው፤ ፌዴሬሽኑ ያሳጣሉ ብለው ያመነባቸውን ተጨዋቾች በመቀነስ እኚህ ኢንተርናሽናል አሰልጣኝ ቡድኑን እንዲያማክሩ
ሲያግባባ ነበር። በኋላ ላይ ግን ፌዴሬሽኑ ገልበጥ ብሎ ጆሃን ፊገ የትምህርትማስረጃ እንደሌላቸውና ቅጥራቸውም ህግና ደንብን 
የጠበቀ አልነበረም በሚል እንዲባረሩ አድርጓል።
ከነርሱ በኋላ የተቀጠረው ስኮ-ጄሪያዊው (የስኮትላንድ ዜጋ ያለው ናይጄሪያዊ) አሰልጣኝም ለእንግሊዙ ደይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ
 “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የረባ ትጥቅ እንኳ የለውም፤
 ልምምድ የምንሰራበት ሜዳየከብቶች ግጦሽ ስፍራ ሲሆን ልምምድ ከመስራታችን በፊት ከብቶችን ማባረር ይኖርብናል” 
ብለዋል በሚል አገራችንን አዋርደዋል ክስ ከስራቸው እንዲባረሩ ተደርገዋል።
እንዳለመታደል ሆኖ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሾሙ ሰዎች እውነት ቢነገሩም፤ ስለ እውነት ቢሰሩም አይፈለጉም።
ጋርዚያቶ የሰሩት ታላቅ ገድል ምንም እንዳልሰሩ ሲደረግ፤ ፊገ ደግሞ የዕድሜ ማጭበርበርን አልደግፍም በማለታቸው
ጥርስ ሊነከስባቸው አይገባም ነበር። የስኮ-ጄሪያዊውም ቢሆን እውነታ አለው፤ ግን እውነትን መደበቅ ስለማንችል
ዘሎ ማባረሩ ውጤት የለውም። ብሄራዊ ቡድናችን የረባ ትጥቅ እንደሌለው የታወቀ ነው፤
ማሊያቸው ላይ እንኳ ስማቸው የሚጻፈው በጀት ሲኖር ነው። የልምምድ ማሊያ ለብቻው አላቸው ብሎ መናገርም
ድፍረት ነው።
ብሄራዊ ቡድናችን ለጨዋታ ሲዘጋጅ ማንቸስተር ዩናይትድ እንዳለው “ካርሊንግተን” የልምምድ ቦታ የለውም።
እውነትን መሸሸግ ለመጥፋት እንጂ ለመማር እንዳልጠቀመን ስኮ-ጂያዊው አስልጣኝ ከተባረሩ በኋላ እንኳ አሳይቶናል።
ምክንያት
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ጥሩ ኳስ አፍቃሪ ተመልካች እንጂ ጥሩ ተጫዋች እንደሌለው የታወቀ ነው።
ተመልካቹ ኳስ አፍቃሪ ስለሆነ
ተስፈኛ ነው። ተስፈኛ በመሆኑም ብሄራዊ ቡድኑ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ጨዋታ አለው በተባለ ቁጥር ጆሮውና ልቡ አብሮ
“ከዋሊያዎቹ” ጋር ይጓዛል።
“የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግብጽ 6 ለ0 ተሸነፈ”
“በሊቢያ ተሸነፈ”
“በሱዳን ተሸነፈ”
“በናይጄሪያ ተሸነፈ”
“በቤኒን ተሸነፈ”
“በሶማሊያ ተሸነፈ”
የሚለው ዜና አስገራሚ ባይሆንም በተሸነፉ ቁጥር የሚቀርበው ምክንያት ግን 
ነው። ሕዝቡም “አሁን ደግሞ ለሽንፈታቸው ምን ይሉን ይሆን?” ብሎ ለሽንፈቱ የሚቀርበውን ምክንያት በጉጉት ይጠብቃል።
የቡድናችን አባላትም አያሳፍሩንም በየጊዜው አዲስ ምክንያት ያቀርቡልናል።
“ግብጽ ላይ የተሸነፍነው አየሩ ከብዶን ነው”
“ሊቢያ ላይ የተሸነፍነው ትራንዚት ስናደርግ ተጉላልተን ነው”
“በሱዳን የተሸነፍነው በአውሮቡስ ረዥም ሰዓት ተጉዘን  ስታዲየም ደርሰን ስለተጫወትን ነው ነው”
“በናይጄሪያ የተሸነፍነው ጉንፋን ይዞን ነው”
“ቢኒን ላይ የተሸነፍነው ስታዲየሙ ውስጥ ስንገባ በጦር መሳሪያ ታጅበን ስለገባን ሰግተን ነው”
“በሶማሊያ የተሸነፍነው አልሸባብን ፈርተን ነው?” (ያስቃል አይደል?)
የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ በሱማሊያ 1ለ0 ተሸንፋ ነበር። በወቅቱ የነበረው  የሕዝብ ስሜት ባለፈው ቅዳሜ ከተከሰተው ስሜት
የማይተናነስ ነበር። እንደውም አንዳንድ ስሜታዊ ኢትዮጵያውያን “እንዴት ከጫት ላይ በጡሩምባ ‘ኳስ የሚጫወት’
ተብለው ተጠራርተው በመጡት ሶማሊያውያን እንሸነፋለን” እስከማለት ሁሉ ደርሰው ነበር። በሶማሊያ ምድር ጸጥታውን ፈርተው
ሊጫወቱ ያልቻሉት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ባለፈው ቅዳሜ ኖቬምበር አስራሁለት ጅቡቲ ላይ ተገናኝተው ነበር።
ጨዋታውም 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። የምስራቅ አፍሪካ አውራ መሆኑ ቀርቶ እንዴት ሶማሊያን ማሸነፍ ያቅተናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ እኔ ብዙ ነበርን። ሆኖም ትናንት ኖቬምበር 16 አላሳፈሩንም 5ለ0 አሸንፈውልናል።
ሶማሊያን በማሸነፋችን አንመጻደቅም ምክንያቱም በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ የሚያበቃ ውጤት እንኳ የለንምና። ሶማሊያን ለማሸነፍም ስምንት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ነበረብን።
እርግጥ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መውደቅ በቅድሚያ ከኢሕአዴግ ፖለቲካ ተጽዕኖ ውጭ ሊወጣ ካልቻለው
የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ባልተናነሰ፤ የሚሰራን ማናናቃችን፣ መወንጀላችን፣ ሽንፈትን አምኖ አለመቀበላችን፣ ምክንያቶቻችን፣
ሁሉ ተጠያቂ ያደርጉናል።
ታማኝ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች “ደግሞ ኢሕአዴግም ለእግር ኳሱ ውድቀት ተጠያቂ ሊሆን ነው ወይ?”ሲሉ ሊጠይቁ ይችሉ ይሆናል።
መልሱ ግን ግልጽ እና አጭር ነው፤
– መሰብሰብ በሚከለከልባት ሃገራችን ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ኳስ ሲጫወቱ  በስርዓቱ ወታደሮች “ተበተኑ” እየተባሉ መጎሳቆላቸው፤
– ኮንስትራክሽንና ቤት ሲሰራ ለሕጻናትና ወጣቶች መዝናኛና መጫወቻ ፕላን እንዲወጣ አለማድረጉ፤
ወጣቱ ለኳስ መጫወቻ የሚሆን ቦታ የለውም፤
– ለብሄራዊ ቡድን የሚመረጡት ተጫዋቾች በብቃት ሳይሆን ለኢሕአዴግ ቱባ ባለስልጣናት 
 ባላቸው ቅርበትና በሙስና መመረጣቸው፤
– የእግር ኳስ ፌድሬሽኑ እግር ኳስ በሚያውቁ ሳይሆን ፖለቲካ በሚያውቁ ሰዎች መመራቱ፤
– ለብሄራዊ ቡድኑ በቂ በጀት አለመመደቡ፤ (አንድ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ካላቸው በጀት ስለሌለ ዝግጅት ለማድረግ ሆቴል የሚገቡት ለመጫወት ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው ነው፤ እንደዚሁም የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ የሚመደበው በጀት አናሳ መሆኑ) እና ሌሎችም ሰፋፊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
በነገራችን ላይ ፊፋ በየወሩ በሚያወጣው ደረጃ መሰረት በኦክቶበር ወር 2011 ዓ.ም  በእግር ኳስ ከፊፋ 307 አባል የዓለም ሃገራት አንደኛ ስፔን ስትሆን፤ ሆላንድ፣ ጀርመን፣ ኡራጋይ እና ብራዚል እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኮትድዲቭዋር 19ኛ፣ ኢትዮጵያ 136ኛ፣ ኤርትራ 190ኛ፣ ሶማሊያ 192ኛ ናቸው።µ
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close