“ሴክስ ቱሪዝም” ያውም እስከ ሰዶማዊነት ድረስ?

(ኤፍሬም እሸቴ)

በዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ በሚደረግ እና ሰዶማዊነትንና ሰዶማውያንን “ለመከላከል” ቀድሞ በተጠራ የ”International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA” ቅድመ ጉባኤ ምክንያት ሚዲያዎች እና ጦማሪዎች ሐሳባቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ” የተባለው በአገራችን የሚገኙ ዋና ዋና ቤተ እምነቶች በጋራ የሚሳተፉበት ጥምረትም ተቃውሞውን ገልጿል። ይሁን እንጂ የICASAን ጉባኤ በዋነኝነት የሚያዘጋጀው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉባኤው ጋዜጣዊ መግለጫውን ከሚሰጥበት ሥፍራ ሚኒስትሩን በመላክ መግለጫ እንዳይሰጥ አድርጓል። በወቅቱ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ፎቶግራፎችም በፖሊሶች እንደ ተደመሰሱ ሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች የጡመራ መድረኮች ዘግበዋል።
ወደ ዝርዝሩ ከመግባታችን በፊት ነገሩ ምን እንደሆነ በአጭሩ እናቅርበው። ነገሩ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሲሆን 16ው “ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የአባላዘር በሽታዎች ጉባኤ በአፍሪካ” (16th International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA) ይባላል። አለመግባባቱን የፈጠረው ግን ይህ ጉባኤ አይደለም። አለመግባባቱን የፈጠረው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሊደረግ የታሰበው “የአፍሪካ ግብረ ሰዶማውያን የቅድመ ኮንፈረንስ ማነቃቂያ ስብሰባ” ነው። ይህንን የግብረ ሰዶማውያን ጉባኤ በመቃወም መግለጫ ለመስጠት የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ቢሰበሰቡም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በቦታው ተገኝተው ከልክለዋል። ጥያቄው ከዚህ ይጀምራል።
1. አዲስ አበባ አፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ለቁጥር የሚታክቱ ስብሰባዎች የሚደረጉባት ከተማ እንደሆነች የታወቀ ነው። (ከዜናው 90% ስብሰባ የሚዘግበው ምስክሩ ኢቲቪ ነው።) ስለዚህ ከተማዪቱ ብዙ ስብሰባ ባዘጋጀች ቁጥር ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጥሩ ገቢ እንደሚያገኙ እና አገርም ሕዝብም እንደሚጠቀም እናውቃለን። ስለዚህ በተቻለ መጠን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በናይሮቢ እና በሌሎች ተቀናቃኝ ከተሞች ከሚደረጉ ይልቅ በአዲስ አበባ ቢደረጉ ተጠቃሚዎች ስለምንሆን ጤና ጥበቃ ጉባኤውን ለማድረግ መጣሩ ተገቢ ነው። ነገር ግን ይህ ጥረቱ የሕዝብን ሃይማኖታዊ መሠረተ እምነት እስከመጣስ ድረስ መሆን የለበትም።
2. ግብረ ሰዶማዊነትን ክርስትናም ሆነ እስልምና አጥብቆ ይቃወመዋል። በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሰዶማዊነት ኃጢአት ነው። ይህ ሃይማኖት ነው። ቤተ እምነቶቹ ደግሞ ምእመኖቻቸው ከግብረ ሰዶማዊነት እንዲጠበቁ ማስተማር ግዴታቸው ነው። ግብረ ሰዶማዊነትን ለማስፋፋት እና ሰዶማውያንን ለማበረታታት ጤና ጥበቃ ጉባኤ እንዲደረግ መድረኩን እንዳመቻቸው እና እንደተጋው ሁሉ እነዚህ ቤተ እምነቶችም ሰዶማዊነት ኃጢአት መሆኑን አጥበቀው መናገራቸውን መከልከል አይገባም። ይህ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው። መንግሥት በቀጥታ በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞችንም መብት በመጣስ ያነሷቸው ፎቶግራፎች በፖሊሶች እንዲደመሰሱ መደረጋቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦልናል። እንዴት ነው ነገሩ?
3. ጤና ጥበቃ ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መደረጉ ለአገር ኢኮኖሚ ይጠቅማል ብሎ ከሆነ በሌላ አማርኛ “ሴክስ ቱሪዝም”ን እያስፋፋ ነው ማለት ነው። ከአገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላዩ ወጣት እና ሥራ አጥ በሆነባት አገር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ለሴክስ ቱሪዝም እንዲጎርፉባትና አገሪቱ ካለባት ቅጥ ያጣ ችግር በላይ እንዲህ ዓይነቱ የባህል ወረራ እንዲካሄድባት መንግሥታዊ ማበረታቻ መስጠት ስሕተት ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው። በሌላው ዓለም ቢሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ለማቋረጥ ከመሔድ ይልቅ ከሕዝብ ሊያገኙት የሚገባቸውን እምነት ስላጎደሉ ሥልጣናቸውን ወደ መልቀቅ ይሄዱ ነበር።  አገሩ ኢትዮጵያ ስለሆነ አንድ ሚኒስትር የሃይማኖት መሪዎች ያዘጋጁትን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማስተጓጎል ቻለ።
4. ድርጊቱ ኢትዮጵያውያን እንዲሸማቀቁ፣ እንዲያፍሩ፣ ራሳቸውን እንዲጠሉ የታሰበበት ያስመስለዋል። መንግሥት እርሱ ከፈቀደው ሐሳብ ውጪ ያሉ ሐሳቦችን ሁሉ በመጨፍለቅ እስከ ሃይማኖታችን ድረስ መድረሱ አስደንጋጭ ነው። ሰዶማዊነት ኃጢአት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን ይህንን ነው። ጤና ጥበቃ የጣሰው ይህንን መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ነው።
5. ከዚህ አንጻር ሕዝቡ በሃይማኖቱ የማይቀበለውን ነገር መቃወሙ ተገቢ ስለሆነ መንግሥት የራሱን አስተሳሰብ ለመጫን መሞከር የለበትም። ሕዝቡ ስብሰባው እንዲሰረዝ ለማድረግ አቅሙ ባይኖረውም እንኳን እንደማይቀበለው ለመናገር መታገድ የለበትም። ከውጪ አገር የሚመጡ የተወሰኑ የጤና ጥበቃ እንግዶችን ለማስደሰት በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ሕዝብ እምነት መዳጥ አይገባውም። ነውር ነው። ነውር ነው። በጣም ነውር ነው። አደራ ይህንንም “ፖለቲካ ነው” እንዳትሉን እነ እንቶኔ።
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close