የሚኒሶታ ኢትዮጵያውያን የወያኔን ሕልም አከሸፉ፤ ቦንድ የገዛ የለም

 በዲያስፖራ ረቂቅ ሰነድ ለመወያየትና ቦንድ ለመሸጥ በሚል በሚኒያፖሊስ የተጠራው የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎች ስብሰባ ካለ ውጤት ተበተነ። ሁሌም በሃገሩ ጉዳይ ወደ ኋላ የማይለው ጀግናው የሚኒሶታ ነዋሪ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ይህንን የመለስ ዜናዊ የ እቃቃ ጨዋታ ቀልድን ቦይኮት በማድረጉ ከአንድ ሺህ ሰው በላይ እንዲይዝ የተዘጋጀው ስብሰባ 40 ሰው የማይሞላ ሰው አስተናግዷል።
የዲያስፖራውን ረቂቅ ሰነድ ለማወያየትና ቦንድ ለመሸጥ ከዋሽንግተን ዲሲ በከፍተኛ ወጪ የመጡት አምባሳደር ግርማ ብሩ የሶማሊኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ አስተጓሚዎችን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው ነበር ስብሰባውን የጀመሩት። በስብሰባው ላይ ከታደሙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ “አጀንዳ እናስይዝና በሃገር ጉዳይ እንወያይ” ሲላቸው አቶ ግርማ “እኛ የያዝነው አጀንዳ ስላለ በርሱ ላይ ነው የምንወያየው” በማለት የኢትዮጵያውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዲያስፖራው የተዘጋጀውን ቪድዮ እንዲታይ ሆነ።
በቪዲዮው ላይ የሚታየው ዲያስⶒራው ወደ ሃገር ቤት ገብቶ እንዲሰራ የሚጠይቅ ሲሆን የተለያዩ ፖሊሲዎች እንደረቀቁም ተገልጸዋል። የአሜሪካ ዜግነት ያለው ኢትዮጵያዊ ሃገር ቤት ገብቶ ቢዝነስ ለመስራት የሚያስብ ከሆነ በሩ ክፍት ነው ያሉት አቶ ግርማ “ጥምር ዜግነት አንሰጥም። (አሜሪካዊ የሆነ ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያ ገብቶ ሌላ ዜግነት አይሰጠውም) ሆኖም ግን በአምስት መቶ ዶላር ወረቀት ገዝቶ መስራት ይችላል። ያ ወረቀትም ወደ ሃገር ቤት ካለቪዛ እንዲመላለስ ያስችለዋል” ብለዋል።
እንደሚታወቀው ወያኔዎች ወደ ሃገራችሁ ገብታችሁ ስሩ ቢሉም፤ ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመስራት ጠቅልለው የገቡ ሰዎች ንብረታቸውን እየተው፤ እየከሰሩና እየሸጡ ወደ መጡበት እየተመለሱ መሆኑን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም። እነዚህ ከኢትዮጵያ የሚመለሱ ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያ አላሰራ ያላቸውን ሁኔታ ሲገልጹ “ስርዓቱ ዘረኛ በመሆኑ አያሰራንም፤ ለአንድ ዘር እንዲጠቅም ተደርጎ ነው ህጉ የተሰራው፤ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ለቻይና እና ህንድ እንደዚሁም አረብ ህጉ ያደላል” ይላሉ።
በስብሰባው ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ወደ ሃገር ቤት መኪና ስለማስገባት፣ ስለላፕቶፕ ኮምፒውተር ማስገባትና እነዚህን ተከትሎ ከመለስ መንግስት ስለሚጣልባቸው ታክስ አንስተው የጠየቁ ሲሆን “ይህ የዲያስፖራ ረቂቅና የኢትዮጵያ ሕግ ይለያያል። ስለዚህ ይህንን ጥያቄ መመለስ አንችልም” ያሉት አቶ ግርማ ወደፊት ረቂቁ ሕግ ሆኖ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል።
በስብሰባው ታዳሚ ሆኖ የገባው የኦነግ አባል ነኝ ያለ አንድ ግለሰብ “በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድሜ ኦነግ ነህ ተብሎ ታስሯል። ሰው የኦነግ ደጋፊ ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ቢችል ምናለበት?” ሲል ጠይቆ አቶ ግርማ “የወንድምህን ስምና የታሰረበትን አድራሻ ከሰጠኸኝ ጉዳዩን ልከታተልልህ እችላለው” ሲሉ፤ ጠያቂው በአጠቃላይ በፖለቲካ አቋማቸው ስለሚታሰሩ ሰዎች ሲጠይቃቸው ይህንን እኛ መመለስ አንችልም ብለዋል።
የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በስብሰባው ላይ እንዲገባ የተፈቀደለት ሲሆን በስብሰባው ላይ ከገባ በኋላ ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ሲነሳ ተከልክሏል። በዚህም የተነሳ በተነሳው አለመግባባት ስብሰባው ለተወሰነ ደቂቃ ሲቋረጥ የዘ-ሐበሻ አዘጋጅ በፖሊስ ከስበባው እንዲወጣ ተደርጎ በአዘጋጆቹም “ማን እንደሆንክ፣ ለምን እንደመጣህ እናውቃለን፤ የሰጠነህ እድል ቁጭ ብለህ እንድታዳምጥ ነበር፤ እድሉን ስላልተጠቀምክበት ውጣና እንደፈለክ ጻፍ” ተብሏል።
የዘ-ሐበሻ አዘጋጅ ከስብሰባው ከተባረረ በኋላ በስፍራው የነበሩ ሶማሊያውያን ሁሉ ሳይቀሩ ወጥተው አዳራሹ ውስጥ ሃያ በማይሞላ ሰው ሰብሰባው እንደቀጠለ ስብሰባው ውስጥ የነበሩት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ተናግረዋል። ቦንድ ግዙን ብለው ፎርሙን ቢበትኑም እንዳሰቡት አንዳችም ቦንድ ሳይሸጡ ባዶ ኪሳቸውን ተመልሰዋል።
ይህንን ስብሰባ ከታደሙት የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ለዘ-ሐበሻ በሰጡት አስተያየት “ወያኔ በሚኒያፖሊስ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። በስብሰባው ላይ ባለመገኘት የሚኒሶታ ሕዝብ ላሳየው ቁርጠኝነት በጣም እናመሰግናለን።” ካሉ በኋላ “በዚህ ስብሰባ ላይ ወያኔን በይፋ የሚደግፉ ሰዎች እንኳ አልተገኙም። ይህ የሚያሳየው ራሳቸው የወያኔ ደጋፊዎች በመለስ ዜናዊ ዲስኩር መሰላቸታቸውን ነው” ብለዋል።
በሃያት ሆቴል ይደረጋል የተባለው ስብሰባ ተሰርዞ በሌላ ሆቴል እንዲደረግ መደረጉ ሕዝቡን ለማደናገርና፤ ይደርስብናል የተባለውን ተቃውሞ ለማርገብ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ወያኔዎች የሚይዙትን እና የሚጨብጡትን ስላጡ በሚኒሶታ በመደናገጣቸው የስብሰባ ቦታ በማቀያየር በአንድ ቀን ውስጥ ስብሰባ የሚደረግበትን ሆቴል መቀየራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። “ለሃያት ሆቴል የስብሰባ ቦታ ከፍለው ስብሰባውን ሲሰርዙ ለሆቴሉ ከፍለው ነው፤ እንደዚሁም ዛሬ ስብሰባው የተደረገበት ዲፖር ራይሰንሰንስ ሆቴልም ከፍለው ነው። ግን የተገኘው ሰው ከአርባ የማይበልጥና ምንም ቦንድ ያልገዛ በመሆኑ ኪሳራውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል” ያሉን አንድ አስተያየት ሰጪ “በሚኒሶታ አንድም ጊዜ ወያኔ ኮርቶ የተመለሰበትን ጊዜ አላስታውስም። ይህኛው ውርደት ግን ከምንግዜውም በላይ ነው” ብለዋል።
አምባሳደር ግርማ ብሩን የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቃለምልልስ ለማድረግ ሞክሮ አልተሳካለትም።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close