Ethiopia under wikiliks file list ኢትዮጵያ በዊኪሊክስ ፋይሎች

ethiopia under wikiliks file list to read  click here pdf format

ኢትዮጵያ በዊኪሊክስ ፋይሎች

በአቢይ አፈወርቅ |

(አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካን ኢምባሲ ተጠናቅረው ወደ ስቴት ዲፓርትመንት ከተላኩ ምስጢራዊ ሪፖርቶች መሀል የኢትዮጵያን ውስጣዊ ጉዳዮች የሚፈትሹ በርካታ መልእክቶች ውኪሊክስ በተባለው ድረገጽ አማካኝነት ለአደባባይ በቅተዋል።ሪፓርቶቹ ሰፊና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንደመሆናቸው በዚህ ርዕስ ስር አንኳር ነቁጦችን በመንቀስ በተከታታይ ምጥን ፍተሻዎች ለማቅረብ ይሞከራል።)

መንደርደሪያ

ህወሐት- በኋላም ኢሕአዴግ በበረሀው የትግል ወቅት የሶሻሊዝም ፍልስፍና ተከታይ መሆኑን በይፋ ሲያውጅ የቆየ ድርጅት ነው። እያንዳንዱም ታጋይ አብዮታዊ መሆኑን ነበር የሚያምነው። አቶ መለስም በተለይ በአርአያነት የሚጠሩት ታጋይ፤ የአልባንያውን ኤንቨር ሆዣን ነበር። ይህ እምነት ግን ለማታገያነቱ ቢረዳም እንኳን አራት ኪሎ ለመግባት ግን ፈታኝ ቅኝት ሆነ። የአለም ፖለቲካ ተቀይሮ የምእራቡ አለም በተለይም የዩ.ኤስ አሜሪካ ቡራኬ ለድል ለመብቃቱም ሆነ ስልጣን ላይ ለመደላደሉ ወሳኝ ሆኖ ተገኘ። ይሄኔ ነበር በኢህአዴግ አካባቢ አዲስ የፍልስፍና ጎዳና ይጠረግ የጀመረው።

የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን የመሰሉ ስር ነቀል የፖሊሲ ለውጦች ማድረጉ ቢያስፈራቸውም እንኳን የተወሰኑ በሮችን ከፈት አድርጎ በምዕራቡ የፖለቲካ ዜማ መደነሱ ግን ግድ ነበር፤ በዚህም ዲሞክራሲና ነጻ ገበያ አዳዲሶቹ መዝሙሮች ሆኑ።

በተግባር ሲፈተኑ ዲሞክራሲውም ሆነ የገበያው ነጻነት ሁሌም ጥያቄ ውስጥ እንደወደቁ ነበር። ያም ሆኖ ግን የምእራቡ አለም ባንጻራዊ እይታ እንደ በጎ ጅማሮ ተቀበላቸው። ኢህአዴግን እየደጋገፉ እንዲረጋጋ ብቻ ሳይሆን እንዲፈረጥምም ከፍተኛ እገዛ አድርገውለታል።

አቶ መለስም ስለዲሞክራትነታቸው ሲደሰኩሩ አመታት አስቆጠሩ። በገቢር ግን ኃያልነት እየተሰማቸው በመጣ ቁጥር ገርበብ አድርገዋት የነበረችውን የዲሞክራሲ ጭላንጭል ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት ፈለጉ። በተለይም ከ2005 ዓ.ም ወዲህ የወሰዷቸው እርምጃዎች ለምእራባዊያኑም ሳይቀር አይናቸውን በጨው አጥበው “ዲሞክራት ነኝ” የማይሉበት ደረጃ አደረሳቸው።… ከዚህ በኋላ መወሻሸቱን አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም ወይም መሸዋወድ የማይቻልበት ደረጃ መድረሳቸው ገብቷቸዋል። በዚህም ለአሜሪካው አምባሳደር በግልጽ “ዲሚክራሲያችሁን አልፈልግም” እስከማለት ደረሱ።

የሚገርመው ነገር አቶ መለስ ስልጣኑን ሁሉ ጠቅልለው እልፍኛቸው ባስገቡ ቁጥር ከመረጋጋት ጋር ያለመረጋጋት ነው የዋጣቸው። የደህንነት መዋቅራቸው በመላው ሀገሪቱ ስሩን በተከለና አግአዚን መሰል ተወርዋሪ ልዩ ጦራቸው እያበጠ በመጣ ቁጥር ከእፎይታ ይልቅ ስጋት ነው ያናወጣቸው። ይህም የሆነው የህዝቡ የመብት ጥያቄ እየፋመና የምሬቱ ልክ እየናረ መምጣቱን በመረዳታቸው ይመስላል።

ይህንና ተዛማች ጉዳዮችን በተመለከተ ምጥን ፍተሻ እናደርጋለን። በክፍል አንድ እይታችን የምናተኩረው ጁላይ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባው የአሜሪካን ኢምባሲ ወደ ስቴት ዲፓርትመንት በተላለፈው ምስጢር የነበረ መልእክት ላይ ይሆናል። የአምባሳደሩን የግል አስተያየት በንኡስ ርእሱ መደምደሚያ ላይ ያገኙታል።

ዲሞክራሲ

“ዲሞክራሲያችሁን አንፈልግም” መለስ ዜናዊ

ፕሬዝዳንት ኦባማ በአፍሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ጋና ላይ ያደረጉትን ንግግር ጠንካራ መልእክት ያለው ነበር። የአፍሪካ መሪዎች ስለ እድገት ለማውራት በቅድሚያ መልካም አመራርና ዲሞክራሲን ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው ጠንከር አድርገው አስጠንቅቀዋል።

ይሄው የፕ/ቱ ንግግር በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር በሆኑት በዶናልድ ያማማቶ እና በአቶ መለስ ውይይት መሀል ተነስቶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በወቅቱ እያወጧቸው ከነበሩት ዲሞክራሲን የሚያጨናግፉ ህጎችና ሊወስዱ ካሰቧቸው አምባገነናዊ እርምጃዎች አንጻር “እስማማለሁ” የሚል ሽንገላ ለማቅረብ አልደፈሩም። ይልቅስ ስህተት ነው በሚል ዓይናቸውን ጨፍነው አጣጣሉት።

“አፍሪካ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጓታል” ከሚለው የፕ/ት ኦባማ አባባል ጋር እስማማለሁ” አሉ አቶ መለስ “ይሁንና ‘የእድገት መሰረቱ መልካም አመራርና ዲሞክራሲ ነው’ የሚለውን ሀሳባቸውን ግን አልቀበለውም። እንዲያውም ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለእድገት አስፈላጊ ወይንም በቂ ስለመሆኑ በታሪክ አንድም አስረጅ የለም።” ሲሉ ተከራከሩ።

አምባሳደር ያማሞቶ ከአቶ መለስ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ውይይታቸው ወቅት ዲሞክራሲንና ልማትን በተመለከተ ጠ/ሚሩ ከምእራባዊያን ጋር ያላቸውን መሰረታዊ ልዩነት ቃል በቃል አምነውልኛል ባይ ናቸው።

ይህ የአቶ መለስ ግልጽ አባባል ደግሞ በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ ላለፉት ሁለት አመታት ያህል “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስትራቴጂ በዩ.ኤስም ሆነ በመላው ምእራብ አለም ከሚታወቀው ዲሞክራሲ ጋር ከመሰረቱ የማይገጥም ነው” እያለ ስቴት ዲፓርትመንት ሲያስተላልፍ ከነበረው ሪፖርቱ ጋር የሚገጥም ሆኖ ተገኝቷል።

“ላለፉት ሁለት አመታት ስናቀርብ የነበረውን ሙግት ትክክለኛነት አረጋግጦልኛል” ይላሉ አምባሳደሩ።

‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ የተሰኘው ፍልስፍና ምንም እንኳን ዲሞክራሲ የሚል ቃል ቢገኝበትም በተግባር ግን ዲሞክራሲ አልባ መሆኑን የአምባሳደር ያማሞቶ ሪፖርት ያረጋግጣል።

“በፍልስፍናው አመራርና ልማት የህዝቡ ነው ቢባልም እንኳን ከህዝቡና በህዝቡ ግን ከቶ አይደለም። ይልቅስ በኢትዮጵያ በተግባር የሚታየውና ጠ/ሚኒስትሩም ያረጋገጡት አሰራራቸው ከላይ ወደታች ብቻ የሚወርድ መሆኑን ነው።

“ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌላው ቀርቶ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ በመንግስት እና በገዥው ፓርቲ የሚታዘዙ፤ አለያም የሚፈቀዱ ብቻ ናቸው።” የሚሉት ያማማቶ ይህ ሂደት አገሪቱን መረጋጋት የሚያሳጣና የአሜሪካንን ጥቅምም የሚጎዳ ስለመሆኑ ዘርዝረዋል።

አቶ መለስ በዲሞክራሲ ጎዳና እንዲራመዱ የሚደረግባቸው ጫና እንዳበሳጫቸውም ከሪፖርቱ ውስጥ ማጤን ይቻላል።

“እኛ ከናንተ የተለየ ጎዳና መምረጣችንን ልታውቁልን አትፈልጉም። ዲሞክራሲን ላያችን ላይ ልትጭኑብን አይገባም” ይላሉ።

“የተፈጠርነው እኩል ነው። ስለዚህ እንደ እኩል እዩን። ከሱዳንና ከሰሜን ኮርያ ጋር በአንድ ላይ አትመድቡን። ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በአንድ ጎራ የተመደበችው ተገቢ ባልሆነ ሚዛን ነው። ይሁንና ይንንኑ መስፈሪያ ብትጠቀሙ እኮ ከእኛ በላይ ዝቅ ባለ ደረጃ የሚገኙ ብዙ ሀገሮች አሉ። ኮንግረሳችሁ ግን አላተኮረባቸውም።” ብለው አምባሳደሩን ተማጥነዋል።

በራሳቸው ፓርላማ የለመዱት አዛዥ ናዛዥነት በአሜሪካም እንዲሰራ በመመኘት አይነት ዳግም እንዲህ አሉ አቶ መለስ፦

“በኮንግረሳችሁ ውስጥ አንዳንዶች እንደማይወዱን እናውቃለን። ያን ደግሞ አስተዳደራችሁ ሊመክትልን አይሞክርም። ለእኛ የማይስማሙን አቋሞች ኮንግረሳችሁ ውስጥ የሚያልፉት እኮ አስተዳደሩ ስለማይገፋቸው ነው።”

አፋኞቹ ሕጎችና ዲሞክራሲ

ብትወዱትም ባትወዱትም ህጉ አይለወጥም” መለስ ዜናዊ

አምባሳደር ያማማቶ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሳለፈቻቸውን የሲቪል ማህበረሰብን፣ የፕሬስን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የጸረ ሽብርተኛነትንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን ጨምሮ ነጻነትን የሚገድቡ ህጎችን በተመለከተ አጥብቀው ጠይቀዋል።

ይህንኑ ጉዳይ የአቶ መለስ አማካሪ ሆኑት አቶ ብርሃኑ አዴሎም ከአምባሳደሩ ጋር ተነጋግረውበት ነበር።

“አሜሪካ በቅርቡ ያወጣናቸውን ህጎች በተመለከተ ነጻነትን አፋኝ ናቸው በሚል የምታሳድረውን ጫና መቀነስ ይኖርባታል። ምክንያቱም ህጎቹ እንዴት እንደሚተገበሩ ገና የሚታዩ ናቸውና” ነበር ያሉት።

ይሁንና ህጎቹ እንዴት እንደሚተገበሩ ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ መለስ ወዲያውኑ አማካሪያቸውን ተቃወሙት።

“መለስ ግን ወዲያውኑ አማካሪያቸውን በመጻረር” ይላሉ አምባሳደሩ በሪፖርታቸው “አተገባበሩ እንዴትም ይሁን እንዴት ያ ግን የህጎቹን ይዘት አይቀይረውም” አሉኝ።

“በህጎቹ ቃላት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሁሉ በአተገባበራቸው ላይም ችግር ይኖርባቸዋል። ህጎቹ ላይ ያለው ዋንኛው ትችት በይዘታቸው ነው። ያን ግን አንድም የሚለውጠው ነገር የለም።”

አቶ መለስ በዚህ አላበቁም። አፋኝ ህጎቻቸው ለዲሞክራሲ አራማጆች ባይመቹም እንኳን ለእኛ ግን አሪፍ ናቸው፡ ሲሉ ይከራከራሉ።

“ምዕራቡ አለም እነኝህን ህጎች ባይወድልንም እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን የተሻሉ መሰረታዊ አማራጮችን የሚሰጡ ናቸው። ከምንከተለው ከኛ ዲሚክራሲ ጋርም አይጋጩም።” ይላሉ።

አቶ መለስ በተደጋጋሚ የምእራባዊያንን ዲሞክራሲ አንፈልግም ቢሉም የሳቸውን ከዲሞክራሲ የተቃረነ ፍልስፍናም በተመሳሳይ ስም ከመጥራት ግን አልተቆተቡም። ልክ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እንደሚደርቷቸው ተለጣፊዎች ሁሉ ዲሞክራሲንም ‘የእናንተ ዲሞካራሲ’ እና ‘የእኛ ዲሞክራሲ’ እያሉ አዲስ የመዝገበ ቃላት ፍቺ የሚፈልጉ ነው የሚመስሉት።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አሜሪካና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የተከተለው ጎዳና ኢትዮጵያ ከምትከተለው የዲሞክራሲና እድገት ጎዳና የተለየ ነው። ልዩነቱም ቴክኒካል ሳይሆን መሰረታዊ መሆኑን መረዳት አለባችሁ’ ብለውኛል።” ይላሉ አምባሳደር ያማማቶ።

ይህ “የፍልስፍና ልዩነታችን መሰረታዊ ነው’ የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙግት በፖሊሲዎች ዙሪያ ላለመወያየት ከመሞከር የመነጨ መሆኑን ከሚቀጥለው አባባላቸው መገመት ይቻላል።

“በተናጥል ጉዳዩችን እየመዘዝን ልንወያይ አይገባንም። መሰረታዊ ልዩነታችን ያለው ከተከተልነው የተለያየ የዲሞክራሲ ጎዳና ላይ ነው። በምንስማማበት እንቀጥላለን። በማንስማማበትም ቢሆን የአገሪቱን ስትራቴጂካዊ ትቅም እስካልነካ ድረስ ችግር የለም። በእኛ በኩል አንዱም እርምጃችን ከአሜሪካን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ጋር የማይጣጣም ነው ብለን እናምንም።

እርዳታና ዲሞክራሲ

“ኤን.ጂ.ኦን እርሱ ብሩን ብቻ አምጡ”

አቶ መለስ አሜሪካ የዲቨሎፕመንት እርዳታዋን የምትለግሰው ተጠያቂነት ባለባቸው መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል መሆኑ ያላስደሰታቸው ሰው ናቸው። እርዳታ ለመስጠት ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንደ መስፈርት መወሰዳቸውንም ያጣጥሉታል።

“እርዳታ ለመስጠት መመዘኛ ማድረግ ያለባችሁ ኢኮኖሚውን በተመለከተ የሚካሂደውን ስራ ብቻ ነው መሆን ያለበት።” እንዳሏቸው አምባሳደር ያማማቶ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

ለእሳቸው በማይመች መልክ የተቀረጸውን የእርዳታ አሰጣጥ ሂደት ሲያጣጥሉ ዳግም እንዲህ አሉ፦

“ልማትን በተመለከተ ዋሽንግተን አዲስ አመለካከት እንዲኖራት እንፈልጋለን። ያሁኑ አያያዝ የተወሳሰበ ነው። ያም ሆኖ ግን የአሜሪካ እርዳታ ከነብዙ ስህተቶቹ የተወሰነ ጠቀሜታ ግን ሰጥቷል። የበለጠ ሊጠቅም እንደሚችል ግን እናውቃለን”

አምባሳደር ያማማቶ ኢትዮጵያ የተለያዩ የዩ.ኤስ.ኤ አሜሪካ የእርዳታ ፕሮግራሞች ትኩረት መሆኗን እንደምትቀጥል አረጋግጠው ይሁንና ከምግብ ርዳታ ባሻገርም መንቀሳቀስ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

(ይህንን አስተያየት የእርዳታ ድርጅቶች ስራቸውን ማካሄድ የሚችሉት በዲሞክራሲም ሆነ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ጉዳዮች ዙሪያ እስካልተንቀሳቀሱ ድረስ ብቻ ነው ከሚለው ከኢሕአዴግ አስገራሚ ህግ ጋር አዛምዶ ማሰቡ ተገቢ ይመስላል።)

በዚህ ጁላይ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተላልፎ ከ2አመት ከአንድ ወር በኋላ ኦገስት 30 ቀን 2011 ዓ.ም በዊኪሊክስ አማካኝነት ይፋ የተለቀቀው ሪፖርት ላይ አምባሳደር ያማማቶ የግል አስተያየቶቻቸውንና ግምገማቸውን አካተውበታል። በጥቅሉ ሲታይም አምባሳደሩ የኢህአዴግን ከዲሞክራሲ ያፈነገጠ ጎዳና እየተቹ መንግስታቸው በአቶ መለስ አስተዳደር ላይ ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር መወትወታቸው ነው የሚታየው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ልትረጋጋ እንደማትችልና ይህም የአሜሪካንን የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ጠንከር አድርገው አሳስበዋል።

“ከአሁን ቀደም እንደጠቀስነው ሁሉ” ይላሉ ያማማቶ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተባለውንና ዲሞክራሲ አልቦ የሆነውን የገዥው ፓርቲን ሁሉን አቀፍ ተቆጣጣሪነት በተመለከተ ከዚህ በፊት ያስተላለፏቸውን ሪፖርቶች እያስታወሱ “ይህ ሂደት ከመሰረቱ በአገሪቱ መረጋጋትን የሚሸረሽር በዚህም አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ጥቅም የሚጎዳ ነው።”

“ምንም እንኳን የአመራር ስልቱን ኢትዮጵያ ላይ መጫን እንደማይገባን ብናምንም ያለንን የጥቅም ልዩነት መረዳትና ግንኙነታችንን አስፍተን በዚህች ባልተረጋጋች ሀገር ላይ ያለንን ጥቅም ከአደጋ መጠበቅ አለብን።”

አቶ መለስ የምእራቡን ዲሞክራሲ ያጣጣሉበትና መሰረታዊ ልዩነታቸውን ያመኑበትን ጉዳይ በተመለከተም በሁለቱ ሀገሮች መሀል ውጥረት መኖሩንና የግንኙነታቸውን ይዘት እንደሚያሳይም ጠቁመው መጭው ውይይት ማተኮር ስላለበት ርእሰ ጉዳዮች አስተያየታቸውን አስተላልፈዋል።

ቀጣዩ ከፍተኛ የሁለትዮሽ ውይይት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ ምን አይነት ቅርጽና ይዘት ሊኖረው እንደሚገባ፤ በሀገሪቱ ስላለው ፖለቲካ መረጋጋትና ነጻነት፤በተለይ ደግሞ መንግስት ከ2005 ዓ.ም ወዲህ ያወጣቸውን ህጎች በተመለከተ መሆን እንዳለበት የአጀንዳ ሀሳብ ፈንጥቀዋል።

“የአሜሪካ መሪዎች ኢትዮጵያ እነዚህን ህጎች ለምን እንደፈለገች፣ ከጀርባው ያለውን ፍልስፍና እንዲሁም ከጠንካራ ተቋማት የራቁ ወይስ በዚያ ላይ የተገነቡ ስለመሆናቸው ሊመረምሩ ይገባል። ህጎቹ በጥቅሉ ሲወሰዱ የፖለቲካ ነጻነትን የሚያሳጡ ከሆነ ይህ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው” ሲሉም አምባሳደር ያማማቶ መንግስታቸውን አሳስበዋል።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close