ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ዓመታት ውስጥ 154 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደረሰብኝ አለ


•    ለ4‚500 ሰዓታት አገልግሎት ከመስጠት ተስተጓጉሏል

Reporter:ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በኦፕቲካል ፋይበር ላይ በደረሰ ስርቆትና መበጣጠስ ጋር በተያያዘ፣ ማግኘት የሚገባውን ገቢ በማጣቱና ለጥገና ወጪ በማውጣቱ የ154 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት በትናንትናው ዕለት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ የደረሰበትን ኪሳራ ያስታወቀው በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና ከውበት፣ ፅዳትና መናፈሻ ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት የጋራ ስምምነት ላይ ነው፡፡

ስድስቱ መሥርያ ቤቶች በጋራ ተባብረውና ተጋግዘው ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባባያ ሰነድ ከመፈረማቸው በፊት እየደረሰባቸው ያለውን ችግር በተነጋገሩበት ወቅት፣ የኢትዮ ቴለኮም የሕዝብ ግንኙነትና የሕግ ኤክስፐርት በጋራ እንደገለጹት፣ በድርጅቱ ላይ የሚደርሰው ችግር ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በተለይ በኦፕቲካል ፋይበር ላይ በስርቆት፣ በውኃ መስመር ዝርጋታ ቁፋሮ ወቅት፣ ሕንፃዎች ሲገነቡና በመሳሰሉት በሚደርሰው መበጣጠስ 41 ሚሊዮን ብር አጥቷል፡፡
ኦፕቲካል ፋይበር በመበጣጠሱ ምክንያት ለ4‚500 ሰዓታት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ በእነዚህ ሰዓታት ውስጥ ማግኘት የሚገባውን 53 ሚሊዮን ብር አጥቷል፡፡ ፋይበር ኦፕቲክሱን ለማስቀጠል 60 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና በድምሩ 154 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ተወካዮቹ አስታውቀዋል፡፡

በኦፕቲካል ፋይበር ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ እያተካሄደ መሆኑን የገለጹት ተወካዮቹ፣ የሚሰርቀው አካል ለገበያ ቢያቀርበው ምንም ጥቅም እንደሌለው፣ ለድርጅቱ ግን ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ ተዘርግቶ የነበረው ኮፐር (መዳብ) የሚይዘው ከአንድ ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ደንበኞችን ሲሆን፣ አንድ ኦፕቲካል ፋይበር ግን 10 ሺሕ ደንበኞችን እንደሚይዝ በንፅፅር አስረድተዋል፡፡ አንድ ኦፕቲካል ፋይበር ሲቆረጥ የኢንተርኔት፣ የሞባይልና የዳታ አገልግሎቶች እንደሚቋረጡ ተወካዮቹ ገልጸው፣ መልሶ ሲጠገን ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ ክስረት የጥበቃ መላላትና የሚሰረቁ ግለሰቦች ግንዛቤ ማጣት መሆኑን ጠቁመው፣ ወደፊት መግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሟቸው ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ችግሩ ሊቀረፍ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ወንጀል ሲፈጽሙ የተገኙትንም በወንጀል ሕጉና በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ጠበቅ ያለ ቅጣት እንዲጣልባቸው መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በበኩሉ በተወካዮቹ በኩል የደረሰበትን ድርጊት እንደገለጸው፣ ከኃይል ስርቆት ጋር በተያያዘ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ስምንት ሚሊዮን ብር ገቢ ቀርቶበት ነበር፡፡

ከኢንዱስትሪ፣ ከመኖርያ ቤትና በልዩ ታሪፍ ከሚሠሩ የደረሰበትን የኃይል ስርቆት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ያጣውን ገቢ በማወቁ፣ በሕግ እንዲከፍሉ ማስደረጉን ተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከ800 ሺሕ በላይ ደንበኞች እንዳሉት የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎችና ማስተላለፊያ ገመዶች እንደሚሰረቁበት ተናግረዋል፡፡ ጥበቃ የሚደረገው በድርጅቱ ሠራተኞችና በፖሊስ ቢሆንም፣ በቂ አለመሆኑንና ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተወካዮቹ አሳስበዋል፡፡ ሌሎቹም መሥርያ ቤቶች የደረሰባቸውን ችግር ዘርዝረው በመነጋገር ለወደፊቱ በጋራ ለመሥራትና ለመጠበቅ የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡   

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close