“ኢህአፓ የፈፀመውን ሰማህ?”

አሳዛኝ ዜና
(ከተስፋዬ ገብረአብ)

ይህን አሳዛኝ ዜና የሰማሁት፣ ጥር 17፣ 2012 ተስያት ላይ ነበር።
አንድ ጓደኛዬ በስልክ እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፣

“ኢህአፓ የፈፀመውን ሰማህ?”
“አልሰማሁም። ምን ፈፀመ?”

ባጭሩ ነገረኝ።

በዝምታ ካዳመጥኩት በሁዋላ፣ እቤት እንደደረስኩ እንደምደውልለት ነግሬው ስልኩን ዘጋሁ። ሆኖም ወደ ቤት አልገባሁም። ቢራ ሳልቀምስ 7 ቀናት አልፎኝ ስለነበር 7ኛው መንገድ ላይ ወደሚገኘው ግሮሰሪ ሄድኩ። “እሾክን በእሾክ”፣ “ኢህፓን በመኢሶን”፣ ‘ብርድን በበረዶ”፣ እንዲሉ ቀዝቃዛ ቢራ አዘዝኩ።

… ኢህአፓን በጣም እወደዋለሁ።
በርግጥ ኢህአፓ ገናና በነበረበት በዚያ ዘመን ገና ልጅ ነበርኩ። ደብረዘይት ላይ ፅጋብ በርሄ የተባለ የኢህአፓ አባል በሁለት ጥይት ተመቶ መገደሉ ግን ትዝ ይለኛል። ጀርባው ላይ፣ “ቀይ ሽብር ይፋፋም!” የሚል ቀይ መፈክር ተለጥፎበት መዘጋጃ ቤቱ ደጃፍ ላይ ዘረሩት። ተኩሶ የገደለው ፈለቀ የተባለ “አብዮተኛ” ነበር። የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ከትምህርት ቤት እንደተለቀቅን፣ ከሰፈር ልጆች ጋር ተሰባስበን ሬሳ ልናይ ሄድን።
የቃጅማው ያለህ!!

የሰው ሬሳ አስፓልቱ ላይ ተነጥፎአል። የኮባ ጅራፍ የመሰለ ጥቁር ደም እንደ እባብ እየተጥመለመለ ወርዶአል። አይተን ስናበቃ ወደቤታችን በረርን። እቤት እንደገባሁ ያየሁትን አልተናገርኩም። “ምን ልታደርግ ሄድክ? ሬሳ ለምን አየህ?” ተብዬ እንዳልገረፍ ስል ዝም አልኩ። አባትና እናቴ ግን ስለዚሁ ጉዳይ ያወሩ እንደነበር ትዝ ይለኛል። አባቴ ዝምተኛ ነው። በብዛት ያዳምጣል እንጂ አይናግርም። ሁሉ ነገር በሆዱ ነው። አሁንም ከነዝምታው ደብረዘይት ላይ በህይወት አለ። እናቴ ተናጋሪ ናት። የቤተሰቡም አለቃ ናት። አሁንም ደብረዘይት ላይ አለች – ማለቴ መቃብሯ። እና ያን ቀን አባትና እናቴ ስለ ኢህአፓ ሲያወሩ ነበር። በተለይም አበራ ሃይሉ እና አማረች ሃይሉ የተባሉት ወጣት ጎረቤቶቻችን ኢህአፓ መሆናቸው በሹክሽክታ ሲወራ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ከዚሁ ወሬ ጋር አያይዛ እናቴ፣ “ኢህአፓዎች ጀግኖች ናቸው” ስትል ሰምቻት ነበር። ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢህአፓና ጀግንነት አንድ አይነት ቃላት ሳይመስሉኝ አልቀሩም። እና በደመነፍስ ኢህፓዎችን እወዳቸው ነበር።
በጋዜጠኛነት የህይወት ዘመኔ በተለይም የኢህአፓን የትግልና የፓለቲካ ታሪክ ለማወቅ ብዙ ጉድጓዶችን ቆፍሬያለሁ። ከእለታት አንድ ቀን በአንድ ግብዣ ላይ ከስብሃት ነጋ ጋር ስናወጋ፣
“ኢህአፓን የመሰረተው ሳቤ ነው” አለኝ።
ኦስማን ሳልህ ሳቤን ማለቱ ነው። አቦይ ስብሃት የነገረኝ እውነት ከሆነ ሳቤ ስለመሰረተው ኢህአፓ የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ። እና በርካታ መረጃዎችን ሳጠራቅም ኖሬያለሁ። “የስደተኛው ማስታወሻ”ን ካሳተምኩ በሁዋላ መረጃዎቹን ልጠቀምባቸው አሳብ አለኝ።
እንዳልኩት ኢህአፓ ልቤ ውስጥ መልካም ስፍራ የያዘ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ኖሮአል።
ብርሃነመስቀል ረዳ እና ተስፋዬ ደበሳይ አእምሮዬ ላይ ተቀርፀው የቀሩ የመንፈስ ሃውልቶች ናቸው። “ደብተራው” በሚል የበረሃ ስም የሚታወቀውን ፀጋዬ ገብረመድህን የተባለውን ታጋይ እስርቤት ሳለ 1983 ላይ አይቼው ነበር። ከመቀሌ የህዝብ ቤተመፃህፍት አጠገብ ባለች አንዲት ክፍል ውስጥ አስረውት ነበር። “ደብተራው” ሲሉኝ፣ ያንን ስም ቀደም ብዬ ሰምቼው ስለማላውቅ ልዩ ትኩረት አላደረግሁበትም ነበር። በሁዋላ ግን ወደ አዴት እንደተወሰደ ሰማሁ። ተስፋዬ ደበሳይ ከፊሊፕስ ህንፃ ላይ ቁልቁል ራሱን ወርውሮ ህይወቱን ሲያጠፋ ምስሉ በምናብ ይታየኛል። የወያኔው ባለስልጣን ህላዌ ዮሴፍ የኢህአፓ ዘመን የህይወት ታሪኩን ሲያጫውተኝ፣ እንዴት አፌን ከፍቼ እንዳዳመጥኩት ትዝ ይለኛል። በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱት፣ ኢንጂነር ኡስማን፣ ካሳ ኩማ፣ መምህር በላይነህ ገብረማርያም በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች መስለው ይሰሙኛል። ታሪኩን፣ “ለካስ ሞትም ይቸነፋል!” በሚል ርእስ “እፎይታ” መፅሄት ላይ በተከታታይ አትሜ አውጥቼዋለሁ። ይጎርፍልን የነበረው የአንባቢ አስተያየት ከቁጥጥር ውጭ ነበር። እና ኢህአፓ በርግጥም ዝንተአለም ሊረሳ የማይችል ባለታሪክ ነበር…

በኢትዮጵያ የፖለቲካና የትግል ታሪክ ውስጥ እንደ ኢህአፓ ተወዳጅ ፓርቲ ሊመሰረት ይችላል ብሎ ማሰብ ሊቸግር ይችላል። “መንፈስ” የተባለው “ቅንጅት” እንኳ አይናችን እያየ የአየለ ጫሚሶ ጫማ ሆኖ ቀረ። እና ቅንጅት እንኳ፣ የኢህአፓን ያህል ተወዳጅ ነበር ማለት የሚቻል አይደለም። ስለመንፈስ ካወራን በርግጥ ኢህአፓ እውነተኛው የህዝብ መንፈስ ነበር።

ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና፣ ቀዝቃዛ ቢራ እየተጎነጨሁ ጓደኛዬ በስልክ የነገረኝን አሳዛኝ ዜና መልሼ መላልሼ አመነዠክሁት። አሳዛኙ ዜና እንዲህ የሚል ነበር፣

“…ኢህአፓዎች የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ስካን አድርገው በድረገፅ ለቀቁት!”

በእርግጥ ኢህአፓ እንዲህ አደረገ?
ያ ስመ ገናና ድርጅት? የእነዚያ ጀግኖች አባት! “ጠመንጃን – በጠመንጃ! ብእርን በብእር! አሳብን በአሳብ! መፅሃፍን በመፅሃፍ! ግጥምን በቅኔ! ይመክታል” እየተባለ የተነገረለት ኢህአፓ ፎቶ ኮፒ ማሽን ታቅፎ ቀረ? እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?

ጓደኛየን ጠይቄው ነበር፣
“ለምንድነው እንደዚያ ያደረጉት?”
“ኮሎኔል መንግስቱ ገንዘብ እንዳያገኝ ነው ይባላል”
“መንግስቱ መቼ ለገንዘብ ፃፈው? መፅሃፉ እንዲነበብለት ብቻ ነው የሚፈልገው”
“ሰዎቹ ተዳክመዋል ይባላል” አለኝ።
“በስም ታውቃቸዋለህ?” ስል ጠየቅሁት።
“ለሁለት ስለተከፈሉ፣ የትኞቹ እንደሆኑ አላውቅም”

ቀደም ብዬ የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ገዝቼ አንብቤው ነበር። በመፅሃፉ ኢህአፓ ርቃኑን ቀርቶአል ማለት ይቻላል። ኮሎኔሉ ስለ ኢህአፓ የገለፀውን መረጃ የሚያስተባብል ወይም የሚተነትን ፅሁፍ ወይም መፅሃፍ ከኢህአፓ ሰዎች እየጠበቅሁ ነበር። በግልባጩ ግን መንግስቱ መቶ ሺህ የማይሞላ ብር የቸገረው ይመስል፣ የመንግስቱን መፅሃፍ ኪሳራ ላይ ለመጣል ፎቶ ኮፒ እያደረጉ በማሰራጨት ስራ መጠመዳቸውን በመስማቴ በጣም ሲያስገርመኝ አመሸ። ርግጥ ነው፣ ሰዎች ሲያረጁ አይቼ አውቃለሁ። ድርጅት ሲያረጅ በአይኔ ሳይ ግን ይህ የመጀመሪያዬ ሆነ።

በርግጥ በዚህ መሃል ብቸኛው ተጎጂ የፀሃይ አሳታሚ ባለቤት ኤልያስ ወንድሙ ይሆናል። ኤልያስ የሃገር ባለውለታ ነው። የአሳታሚነት ስራ ምን ያህል ከባድና እልህ አስጨራሽ መሆኑን የሚረዳ ሰው፣ ኤልያስ ይህን ስራ ለትርፍ ብሎ እንዳልጀመረው ይረዳለታል። ኤልያስ በኪሳራ ምክንያት ይህን ስራ ለማቋረጥ ቢገደድ፣ ተጎጂዋ ይህችው የፈረደባት መከራዋ የበዛ ሃገር ናት። ከዚያም በላይ ግን ታሪክና እውቀት ይደማሉ። ስለኢህአፓ ለዘመናት ይዤው ኖርኩት ምስል እንደ ጥላ ጥሎኝ እንዳይኮበልል ተመኘሁ። ገና በማለዳው አምበረጭቃ ተለቅልቃ፣ የጎረቤቷን ዶሮ በአሽሙር የምትሳደብ ምቀኛ ኮማሪ ምስል እየታየኝ ነበር….

አምላክ ሆይ!
የታመሙትን ፈውስ። የደከሙትን አሳርፍ። እነዚህ አባቶቻችን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተከበረ ስም ይዘዋልና ምህረትህን አትንፈጋቸው። “መዘባበቻ ከመሆን አድነን” ተብሎ እንደተፃፈው…አምላክ ሆይ!

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close