መድረክ ምርጫ ቦርድን በአድሎአዊ አሠራር ወነጀለ

REPORTER:ምርጫ ቦርድ የገለልተኛነት መርሁን ጥሶ፣ ኢሕአዴግ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት በመፍጠር የሚያከናውነው ተግባር አስፈጻሚ ሆኖ እንደሚያገለግል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ገለጸ፡፡

መድረክ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ምርጫ ቦርድ በየዓመቱ ከመንግሥት አሥር ሚሊዮን ብር እያስፈቀደና መልሶ ለኢሕአዴግ፣ ለአጋሮቹና ለታማኝ ‹‹ተቃዋሚዎቹ›› ጠቅልሎ እያስከረበ፣ በኢፍትሐዊና አድሎአዊ አሠራሩ ለሚቀርብበት ቅሬታ ‹‹አዋጁ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም›› በማለት የሚሰጠው ምክንያት ተቀባይነት የለውም፡፡

Medrek, MT

ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት የሚሰጥን ድጋፍ በማስመለከት የተደነገገው አዋጅ፣ ‹‹ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጥ የመንግሥት ድጋፍ በፍትሐዊነትና ያለአድልኦ መፈጸም አለበት›› በማለት የጠቆመው መድረክ፣ አዋጁ ሁሉም ፓርቲዎች ለዕለት ተዕለት ሥራቸው ማከናወኛ ከመንግሥት በፍትሐዊነት ድጐማ እንዲደረግላቸው ቢደነግግም፣ ቦርዱ አሁንም አድሎአዊ አሠራር እየፈጸመ መሆኑን አመልክቷል፡፡

መግለጫው እንደሚለው፣ ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ቦርዱ ለ2004 ዓ.ም. ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተግባር ማከናወኛ ከመንግሥት ካስፈቀደው አሥር ሚሊዮን ብር ውስጥ ለመድረክ በአንድ መቀመጫ ተሰልቶ 3,598.41 ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በሚገኘው የመድረክ ሒሳብ ገቢ መደረጉን የገለጸው ምርጫ ቦርድ፣ ከላይ የተጠቀሰው ገንዘብ በኦዲተር የተረጋገጠ የፋይናንስ ድጋፍ አጠቃቀም እንዲቀርብለት መጠየቁ ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ንሳው›› የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡

አምና ለተለያዩ ተግባሮች ማከናወኛ በሚል ያለፍላጐቱ በባንክ ሒሳብ ቁጥሩ በምርጫ ቦርድ ገቢ የተደገለትን 3,598.41 ብር፣ ክፍፍሉ ኢፍትሐዊና አድሎአዊ ሆኖ በማግኘቱ ለመላኪያ ተጨማሪ ወጪ አውጥቶ ለቦርዱ ተመላሽ ማድረጉን ያስታወሰው መድረክ፣ ባለፈው ዓመት የተከሰተው ነገር እየታወቀ ለ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመትም ያው 3,598.41 ብር ለመድረክ ገቢ መደረጉ፣ ድርጅቱ ገቢ ከተደረገለት ከሦስት እጥፍ በላይ ወጪ አውጥቶ ያውም ኦዲተር ቀጥሮ የተረጋገጠ የፋይናንስ ሒሳብ ሪፖርት እንዲያቀርብ መጠየቁ ይበልጥ የሚያስተዛዝብ ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ፣ እንደ መንግሥትና እንደ ነጋዴ ሆኖ የአገሪቱን ሀብት በብቸኝነት ጠቅልሎ መያዙ አልበቃ ብሎት፣ በዲሞክራታይዜሽን ስም ከለጋሽ አገሮች ወይም ከመንግሥት ካዝና በፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ስም የሚመጣውን ገንዘብ ጠቅልሎ እንዲወስድ መደረጉ፣ ኢሕአዴግንም ሆነ ቦርዱን በኢትዮጵያ ሕዝብና በታሪክ ፊት የሚያስጠይቅ ድርጊት እንደሆነ ሙሉ እምነት አለን፤›› ሲል በመግለጫው ያስታወቀው መድረክ፣ አምና እንዳደረገው ሁሉ ዘንድሮም ያለፍላጐቱ በባንክ ሒሳብ ቁጥሩ ገቢ የተደረገውን 3,598.41 ብር ተመላሽ ያደረገበትን አንድ ገጽ ሰነድ ለምርጫ ቦርድ የላከ መሆኑን፣ ለወደፊትም ቢሆን የድጋፍ ገንዘብ ክፍፍል አፈጻጸሙ ከአድሎአዊነት እስካልፀዳ ድረስ ያለፍላጐቱ በባንክ ሒሳብ ቁጥሩ ገቢ የማድረጉ ድርጊት እንዲቆም ጠይቋል፡፡

አያይዞም፣ ‹‹ይህ ሳይሆን ቢቀር፣ ገንዘቡን ለመመለስ ወይም ገቢ ከተደረገልን ገንዘብ እጥፍ በላይ ወጪ አውጥተን ኦዲተር ሾመን የአጠቃቀም ሪፖርት ለማቅረብ የማንገደድ መሆኑን እናስታውቃለን፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close