በሚኒሶታ ለኢሳት ቴሌቭዥን የተሳካ የገቢ ማሰባሰብ ተደረገ

ከሮቤል ሔኖክ

(ዘ-ሐበሻ)፦ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንን በገንዘብ ለማጠናከር በሚል ዋና ዓላማ በሚኒሶታ የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ።
አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነን፣ አባ ወልደተንሳኤን እና አባ ገብረማርያምን፣ እንደዚሁም ተወዳጁን ድምጻዊ ተሾመ አሰግድን የክብር እንግዶች በማድረግ የተዘጋጀው ይኸው የራት ምሽት ላይ መድረኩን በሚመራው በጋዜጠኛ ሔኖክ ዓለማየሁ ነበር የተከፈተው። በኢትዮጵያ ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን ራሱን አቃጥሎ ላጠፋው መምህር የኔሰው ገብሬ፣ በጋምቤላ ሰሞኑን ለተገደሉት ከ19 በላይ ነጹሐን ዜጎች፣ በቅርቡ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ደጃፍ ጸጉሯን እየተነጨች በአደባባይ የሚያድናት ወገን አጥታ ስትጎተት የነበረችውና ራሷን አጠፋች ተብሎ ዜናዋን ለሰማነው ለእህታችን ዓለም ደቻሳ፣ እንደዚሁም በቅርቡ በሚኒሶታ ከዚህ ዓለም በዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ሁልጊዜም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ጋዜጠኞች እንዳይጎሳቆሉ፣ መልካም አስተዳደር በሃገራችን እንዲሰፍን ሲታገል ለነበረው ለአቶ ብርሃኔ ወርቁ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት እንዲደረግ በጠየቀው መሰረት ለነዚህ ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ የአንድ ደቂቃ ጸሎት ፕሮግራም ተደርጎ የገቢ ማሰባሰቡ ምሽት ተከፈተ።

ከዚያም የቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ገብረሚካኤል ተሰማ ይህን ዝግጅት በጸሎትና በንግግር እንዲከፍቱት ተደርጎ መድረኩ ወደሳቸው ሄደ።
አባ ገብረሚካኤል “የሃይማኖት መሪዎች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የለባቸውም” ተብሎ በአንዳንድ የእምነት ተከታዮች ለሚጠይቁ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እየጠሩና የክርስትና እምነት የሃይማኖት መሪዎች ከተበደሉት እና ከተገፉት ሕዝብ ጋር ቁሙ ይላል ብለዋል። “ሕዝብ ከመሬቱ ሲፈናቀል፤ የዋልድባ ገዳም ሲታረስ የሃይማኖት መሪዎች ዝም ብሎ ማየት ምንድን ነው?” ሲሉ የጠየቁት አባ ገብረሚካኤል “ይልቁንም በዚህ ጭንቅ ሰዓት ከመሬቱ ከተባረረው፣ በሃገሩ ላይ ስደተኛ ለሆነው፣ ለተቸገረው፣ ስለሰው ልጅ መብት ጻፍክ ተብሎ ከታሰረው፣ ከታረዘው ጋር አብሮ መቆም ያስፈልጋል” ሲሉ ለሃይማኖት አባቶች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ስለሚዲያ አስፈላጊነት ሲናገሩም ሚዲያ ለአንድ ሃገር ያለው ጠቀሜታን አስቀምጠው “ሰይጣን እንኳ አፍ ኖሮት ለምን ሁሌ ተንኮል እንደሚሰራ ተጠይቆ ቢያስረዳ በአንድ ሚዲያ ውስጥ መከልከል የለበትም” በማለት አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሚዲያ አፈና በምሳሌ አስቀምጠው በአዳራሹ ውስጥ የተገኘውን በመቶዎች የሚቆጠር ሕዝብ አስደምመውታል።
ከሳቸው በመቀጠል ታዋቂው የወንጌል ሰው አባ ወልደትንሣኤ ወደ መድረኩ ተጋብዘው በአዳራሹ ውስጥ ያለውን ሰው የሚያነቃቃ ንግግር አድርገዋል። በተለይም “ኢሳት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልክ እንደሲኤን ኤን እና አልጀዚራ ተሰሚነት እንዲኖረው ቁልፉ ያለው በኛ በሕዝቡ እጅ ነው” በማለት ይህን የመጀመሪያውን የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ እንዲያበረታታና እንዲደግፍ ለሕዝቡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አባ ወልደትንሣኤ የወቅቱን የሃገራችንን ሁኔታ ከኢሳት ጋር እያያዙ የተናገሩበት ቪዲዮ በቅርቡ በዩቱዪብ እና በኢሳት ቲቪ ላይ ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአባ ወልደትንሣኤ ንግግር በኋላ ለእንግዳው ታማኝ በየነ “ታማኝ የታለ?” የሚለውና ለክብሩ በደረጀ ደገፋው የተዘፈነው ዘፈን በአዳራሹ ተከፈተ። ወዲያውም ታማኝ በክብር ታጅቦ ወደ አዳራሹ ሲገባ ሕዝቡ ከመቀመጫው በመነሳት በክብርና በሆታ ተቀብሎታል።

ፕሮግራሙ ቀጠለ….
የመድረክ መሪው ጋዜጠኛ ሔኖክ በኢትዮጵያ ፕሬስ ዙሪያ ገለጻ ሰጥቷል። በገለጻውም ወቅት “የኢትዮጵያን የነጻ ፕሬስ ሚዲያ ታሪክ በሦስት እከፍዋለሁ። 1ኛው የድንጋጤ ዓመታት ፣ 2ኛ. የመረጋጋት ዓመታት፣ 3ኛው ደግሞ የሽብር ዓመታት። የድንጋጤ ዓመታት የምላቸው ኢሕአዴግ ነጻ ፕሬስን ከፈቀደበት እስከ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ያሉትን ዓመታት ነው:፡በዚህ ወቅት አንድ ጋዜጠኛ አንድ ጽሁፍ በጋዜጣው ላይ ካወጣ ቢሮው በፖሊስ ተከቦ በመታደን ወደ እስር ቤት የሚወረወሩበትና ኢሕአዴግ በአንድ ጋዜጣ በተጻፈበት ጽሁፍ ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ የሚያረገውን የሚያጣበት ወቅት ነበር። 2ኛው የመረጋጋት ዓመታት የሚባሉት ናቸው። እነዚህ የመረጋጋት ዓመታት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እስከ ምርጫ 97 ዓመታት ያሉት ናቸው። በነዚህ ዓመታት ጋዜጠኞች በጻፏቸው ጽሁፎች እስር ቤት ቢወረወሩም ቢያንስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመታሰር የሚጠሩት በስልክ ወይም በመጥሪያ ወረቀቶች ነበሩ። 3ኛው ዘመን ደግሞ ከምርጫ 97 ያለው የሽብር ዘመን ነው። ይህ ዘመን የጻው ፕሬስ አባላትም ኢሕአዴግም የሚሸበሩበት ነው። በሽብር ዘመን ኢትዮጵያ በስደተኛ ጋዜጠኛ ቁጥር ከዓለም አንደኛ ሆናለች። በሽብርተኛው ዘመን ጋዜጠኞች አሸባሪና ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር በተያያዘ ክስ ታስረዋል፣ በዚህ ዘመን ነጻ ጋዜጦች በአጠቃላይ ተዘግተው በአሁኑ ወቅት ደፋር የሚባል ጋዜጣ ቢኖር አንድ ነው” ሲል ንግግሩን ያስረዘመው ጋዜጠኛው ኢሳት ነጻ ሚድያ በሌለበት ሃገር ምን ያህል ተፈላጊም አስፈላጊም እንደሆነ በማስረዳት አይደለም ኢሳትን የሚያህል በርከት ያሉ የተፈተኑ ጋዜጠኞች ይቅርና አንድ ግለሰብ ብቻውን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ላሳያችሁ በሚል በቪዲዮ የተደገፈውን የጆሴፍ ኮኒ 2012 (ይህን ቪዲዮ ለማየት እዚህ ይጫኑ) ፊልም በአዳራሹ አሳይቷል። በዚህ ቪድዮም የአብዛኛው ታዳሚ መንፈስ በአምባገነኖች ተግባር ተነክቷል።
ድምጻዊ ተሾመ አሰግድ በየፕሮግራሙ ጣልቃ እየገባ ጣዕመ ዜማዎቹን እያሰማ በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበውን ሕዝብ ያዝናናው ሲሆን እሱም በበኩሉ ለኢሳት የሚገባውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ተሾመ “ኢሳት መረዳት ያለበት ተስፋ ያለው ሚዲያ ነው” በሚል የሙዚቃ መሣሪያዎቹን ክራይ ሁሉ በመቻል ይህንን ዝግጅት ካለምንም ክፍያ በማገልገል ለሌሎች ልማታዊ አርቲስቶች አረአያ የሚሆን ተግባር አከናውኗል።

ወደ እራት ምሽቱ ከመሄዱ በፊት የክብር እንግዳው ታማኝ በየነ 1 ሰዓት ከ38 ደቂቃ የፈጀ ንግግር በቪድዮ በማስደገፍ አቅርቧል። ታማኝ በየነ በሚኒሶታ ያደረገው ንግግር በኢሳት ቲቪና በዩቱዩብ ከሰሞኑ የሚወጡ ቢሆንም የዳሰሳቸውን አንዳንድ ነጥቦች እናካፍላችኋለን።
ታማኝ ንግግሩን የጀመረው የአክሊሉ ሃብተወልድን መልካም ተግባርና ለኢትዮጵያ ሐገራችን በዓለም አደባባይ የሰሩትን መልካም ተግባር አድንቆ “ይህ የኢሳት ፈንድራይዚንግን እዚህ እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት አክሊሉ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ዛሬ ልደታቸው ነበር” ብሏል። የአክሊሉ ሃብተወልድን መልካም ተግባር በቪድዮ እያስደገፈ አቅርቦ እኚህ ታላቅ ሰው በኋላ በስቅላት ሲገደሉ መንግስት ለሃገሪቱ ለፈጸሙት መልካም ተግባር እንኳ ሲል ይቅር አለማለቱን ወቅሷል።

አክሊሉ ሃብተወልድ በተወለዱበት ዕለት በሚኒሶታ የተደረገው ይህ የኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ታማኝ “ኢሕአዴግን ትንሽ ልማው” በሚል ሕዝቡን በማሳቅ በተለይ በዘር ላይ ስለተመሰረተው የሕወሓት አገዛዝ በቪዲዮ ማስረጃ የተደገፈ ዘገባ በማቅረብ በአዳራሹ የተገኘውን ሕዝብ አስገርሞታል። በተለይም “የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ከእያንዳንዱ የኢሕአዴግ ሚኒስተር ስር እንደታኮ የቀመጡት ሚንስትሮች የትግራይ ተወላጆች ብቻ ናቸው” በማለት ምስላቸውን ከነሥራ ድርሻቸው በማቅረብ አሳይቷል። “የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች” በሚለው ቪድዮውም በአማካሪነት ያሉትን የትግራይ ተወላጆች በምስል አሳይቷል። የመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ያለውን የብሄር ተዋጽኦና የስልጣን ተዋረድንም በሚመለከት ባሳየው ቪድዮ ቁልፍ ቦታው በትግራይ ተወላጆች እንደተያዘ አጋልጧል። ከዚህም ውጭ በተለያዩ የሃገሪቱ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን በፎቶ ግራፍ በማሳየት መለስ ዜናዊ የገቡትን ቃልም ሕገመንግስቱንም ክደዋል ብሏል።
እነመለስ ተዋጋንለት የሚሉት የኢትዮጵያ ሕገመንግስት አንቀጽ 87፡
የመከላከያ መርሆዎች
1. የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፡፡
2. የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል፡፡
3. የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፡፡
4. የመከላከያ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ ይሆናል፡፡
5. የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነጻ በሆነ አኳኊን ያከናውናል፡፡
ቢልም፤ በግልጽ እየታየ ያለው ግን ይህ አይደለም በማለት ለሕዝቡ አስረድቷል።
ይህን የመለስ ዜናዊ መንግስት ስልጣን አከፋፈል የትግራይ ሕዝብ ሳይቀር ሊቃወምና ተው ሊለው ይገባዋል ያለው ታማኝ በየነ “መንግስቱ ሃይለማርያም ግማሽ አማራ ግማሽ ኦሮሞ ነኝ ብለዋል። ታዲያ መንግስቱ ሃይለማርያም ላጠፋው ጥፋት ግማሹን የአማራ ግማሹን የኦሮሞ ሕዝብ ሊጠየቁበት ነው ወይ?” ሲል ጠይቆ ዛሬ እነመለስ እየሰሩት ያለው ሥራና ዘረኛ አካሄድ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተነጥሎ መታየት እንዳለበት፤ የትግራይ ሕዝብም ለዚህ ተጠያቂ እንደማይሆን አስቀምጦ በጋራ እንዲህ ያለውን አካሄድ ለመቃወም አብረን እንቁም ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።
(ሙሉው ቪድዮ ተቀናብሮ እንደተጠናቀቀ እናቀርበዋለን)
“እናቴን ዓይኗን ካየሁ አስራምናምምን ዓመታት አልፈውኛል። ታዲያ አንድ ሰሞን ኢሳት ኢትዮጵያ ውስጥ መታየት ሲጀምር አሁንማ አትናፍቀኝም እቤቴ ውስጥ ሁሌ አለህ ትለኝ ነበር” በሚል ኢሳትን ለመግለጽ የሞከረው ታማኝ በመንግስት አፈና በተደጋጋሚ ኢሳት ከኢትዮጵያ አየር እንዲጠፋ የተደረገበትን ደባ ሁሉ አስረድቷል።
በሚኒሶታ በተደረገው የኢሳት የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ ሕዝቡ በኪሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ሳንቲም ሳትቀር እያራገፈ ረድቷል።
የኢሳትን ፈንድራይዚንግ ለመታደም የመጣው ሕዝብ ቁጥር በሚኒሶታ ከቅንጅት በኋላ ከተደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ በቁጥሩ ከፍተኛው ሊባል የሚችል እንደሆነ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለ-ሐበሻ ድረ ገጽ ገልጸዋል። ይህም ኢሳት “ከምርጫ 97 በኋላ ሕዝብን ያነቃቃ ክስተት ተብሎ” የሚገለጸውን እውነት ያደርገዋል ይላሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች።
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close