የመለስ አገዛዝ ባለስልጣናት በኤርትራ ላይ ተደረገ በተባሉት ጥቃቶች ዙሪያ እርስ በርሱ እየተቃረኑ ነዉ !

ሰሞኑን በሰፊዉ እየተወራ ያለ ክስተት ቢኖር የመለስ አገዛዝ በኤርትራ ላይ ፈጸምኩት የሚለዉ ጥቃት ነዉ። ተደረጉ በተባሉ ጥቃቶች ዙሪያ ግን የአገዛዙ ባለስልጣናት እርስ በርስ እየተቃረኑ እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ከአራት ቀናት በፊት የመለስ አገዛዝ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል፣ በአፋር አካባቢ 18 ኪሎሜትር የኤርትራ ድንበር ዘልቆ በመግባት፣ በኤርትራ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ፣ መናገራቸዉ ይታወሳል። አቶ ሽመልስ ከማል ተፈጸመ ስላሉት ጥቃት፣ ምንም አይነት መረጃ ያልቀረበ ሲሆን ፣ በገለልተኛ ኃይላትም የቀረበ ማናቸዉም አይነት ማረጋገጫ እስከ አሁን አልቀረበም።

የኤርትራ መንግስትም፣ የመለስ አገዛዝ ያቀረበዉን ሪፖርት በመጥቀስ «ተጠቃዉ» ብሎ ክስ ለተባበሩት መንግስታት ያቀረበ ቢሆንም፣ በቦታዉ በመገኘት የውትድርና ጥቃት መሰንዘሩ የሚያሳይ ማናቸዉም አይነት የቪዲዮ መረጃዎችን አላሳየም።

በአፋሩ አካባቢ ያለው ሁኔታ በዚህ እንዳለ ፣ የኢሕአዴግ መንግስት ባለስልጣናትን በመጥቀስ ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሁለተኛ ጊዜ ቅዳሜ ማርች 17 ቀን ጥቃት መፈጸሟን ሮይተርስ ዘግቧል። ነገር ግን የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣን አቶ ጌታቸዉ ረዳ፣ የሮይተርስን ዘገባ በመቃረን በባድመ በኩል ተደረገ የተባለዉ ጥቃት «ዉሸት» እንደሆነ መናገራቸዉን ብሉምበር ኒዉስ ያትታል።

ከመለስ አገዛዝ ለሜዲያዉ የሚሰጡ የተቃረኑ መግለጫዎችን በተመለከተ አስተያየት የሰጡን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ የፖለቲካ ተንታኝ፣ አንዱ ባለስልጣን ሌላዉን የሚቃረን ከሆነ፣ ነገሩ ዉሸትና ሸፍጥ ያለበት ፣ አቶ መለስና አት ኢሳያስ የሚጫወቱት ድራማ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

«የኢትዮጵያ ሕዝብ አዋቂ ነዉ። ሽመልስ ከማልን እየላኩ እነ መለስ የሚነዙትን ቀልድ አያዳምጥም» ያሉን እኝሁ ተንታኝ፣ የመለስ አገዛዝ «አለ» የሚለዉን የጦርነት ወሬ የሚያወራበት ሁለት ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። «የመጀመሪያዉ ምክንያት» ይላሉ እኝህ ተንታኝ … «በመጀመሪያ በሻእቢያ ላይ ትልቅ ችግር ካላቸዉና ኢሳያስን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል ከሚሉ፣ የሕወሃት ነባር አባላት ዘንድ ዉስጥ ዉስጡን እየተነሱ ያሉ ተቃዉሞዎችን ለማዳፋን፣ የሻእቢያ ደጋፊ ሳይሆኑ በሻእቢያ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ማሳየት አለባቸዉ» በማለት የመጀመሪያዉን ምክንያት ያስረዳሉ።

«ከኢሳያስ ጋር ለመደራደር ፣ ባድመንም ለመስጠት ከወዲሁ የወሰኑ ይመስላል። ለዚህም እንዲረዳቸው ፣ አንድ ሰበብ መፈለግ አለባቸዉ። ጦርነት አደረግን ብለዉ ሲያወሩ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሌለ ጦርነት እንዲቆም ፣ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ማድረጉ አይቀረም። የዚያን ጊዜ አቶ መለስ ካልተስማማን፣ ባድመን ካልሰጠን እርዳታ አናገኝም። እቀባ ይደረግበናል» የሚል ፕሮፖጋንዳ ይጀምራሉ» ሲሉም ሁለተኛዉም ምክንያት የሚሉትን ይዘርዝራሉ።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close