ፍርሃት አዶ ከበሬ


 ከአስቻለው ከበደ
ደርግ ወደ ስልጣን መውጫው ጊዜ ላይ ድሮ ልጅ ሳለሁ አንድ የማይረሳ ትዝታ አለኝ፡፡የጥምቀት በዓል ለማክበር ሄጄ አንድ ነገር ተመለከትኩ፡፡አንዲት እናት የትግሬ ሽሩባ የተቆነደሉ በእጃቸው ረዘም ያለ ዘንግ ይዘው ከታቦቱ ፊት ጥቂት ሰዎች አጅበዋቸው ይሄዳሉ፡፡በእጃቸው የያዙትን ዘንግ እንደ ጦር ይሰብቁታል፡፡ ዐይናቸው እንደ ፈጠጥ ከተኮሳተረው ግንባራቸው ስር ይጉረጠረጣል፡፡ሴትየዋ እንደ እድሜ እኩዮቻቸው እናቶች ሳይሆን እንደ ወጣት ትከሻቸውን እያንቀጠቀጡ ይዘላሉ፡፡ በግዜው ባለገባኘ ቋንቋ ጎርነን ባለ ድምጽ ያነበንባሉ፡፡ በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች “ትግሬው አበበ፣ ትግሬው አበበ…” እያሉ ያጅቧቸዋል፡፡

አብሮኝ የነበረውን ሰው “እማማ ምን እያደረጉ ነው ?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡”አዶ ከበሬ ናቸው” ብሎ መለሰልኝ፡፡እያደኩ ስመጣ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች መንፈሱ ሲያድርባቸው ሽቶ የሚጠጡ፣እሳት የሚጎረሱ መሆናቸውን እሰማ ጀመር፡፡

በሚከተለው ርዕዮት የማሌሊት-ህውሃት ወንድም የሆነው ደርግ እንዲህ አይነቱን ነገር በባህል አብዮት ጅራፍ ገርፎ ሊያጠፋው ትንሽ ሲቀረው እራሱ እንደ ጠፋ የአዶ ከበሬ ተከታዬች ሲተርኩ ሰምቼአለሁ፡፡

የደርጉ ጅራፍ ከተነሳ ከአንድ ኮሚኒዝም የተወለዱ ደርግ፣ኢህአፓ፣መኢሶን፣ማሌሊት-ህውሃት ቀይሽብር፣ነጭ ሽብር…በሚባሉ ጅራፎች እንዴት እንደተጫረሱ ሁል ጊዜ የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ሳስበው መለማመኛዋ ፋፋ ቆሎ፣የእጣን ሽታና ቡና የሆነው ፣ደርግ ሊያጠፋት ከነበረችው አዶ ከበሬ እና በከተማና በገጠር፣ በአይምባና አሲምባ ተራሮች ላይ የወንድማማቾችን ደም ካፋሰሰው የኮሚኒዝም ዛር በጭካኔ የትኛው ይበልጥ ነበር ስል እራሴን እጠይቃለሁ፡፡

“ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቀደም!” የሚለው ቅዱስ መፈክርን “ያ ምንደኛ የኢህአፓ ቅጥረኛ በቀይ ሽብር ተመትቶ ሲተኛ፣ እሰይ እሰይ ደስ ማለቱ፣እሰይ እሰይ ደስ ማለቱ…” በሚለው እሰከ መቀየር ድረስ ምነው ትውልዱን ጭካኔ ሞላው?

መቼም ይህንን አብዮታዊ መፈክር ደርግ እንጂ ሌላው አልዘመረውም ማለት አይቻልም፡፡ምክነያቱም በብሔርም ሆነ በህብረ ብሔር ስም ተደራጅተው የተጋደሉ ሁሉ በሚያሽካካው ክላሼንኮብ ጥይት ዘምረውታልና፡፡

የታሪካችን መጥፎ ገጽታ የሆነው መገዳደላችን እንስሳዊ ባህሪያችንን አጉልቶ ያሳየ መሆኑን ሳስብ በእንስሳቱ አለም ያለው መጠፋፋት ለምን እንደሆነ አሰላስልና አይ የእኛ አብዮታዊ እንስሶች ያስብለኛል፡፡

አንድ ጊዜ ደቡብ ኢትዮጵያ ማጎ ፓርክ አካባቢ አንድ ነገር አስተዋልኩና የስነ ምህዳር ባለሞያ የነበረውን ሰው አጠር ያለ ጥያቄ ጠየቅኩት”ዝሆን፣ጎሽም ሆነ እባብ ስጋ በል እንስሳት አይደሉም፡፡ተዲያ ለምንድን ነው ሰውን የሚያጠቁት?” መልሱ እንዲህ የሚል ነበር “ማንኛውም እንስሳ የደህንነት ርቀት ልክ (Flight distance) አለው፡፡ ይህ ማለት በዚያ ርቀት ላይ ሰው እነደማያጠቃው ያውቃል፡፡ ከዚያ ርቀት ልክ ወዲህ ከሰው ጋር ቢገናኝ ግን ፣ሳቀድመኝ ልቅደመው በሚል ተፈጥሮዊ ደመ ነፍስ ሰውዬውን ቀድሞ ያጠቃል፡፡የርቀት መጠኑም ከእንስሳ እንስሳ ይለያያል፡፡”

ከ62 – 68 ዓ.ም የነበረው የኢትዮጵ ሙህራንና ወታደር የለውጥ ትግል ሊገነቡት ያሰቡት ቤት
በኤርትራ ሀገርነት ጥያቄና በብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ንፋሶች አስራሰባት ዓመት ሲንገላታ ከርሞ ደርግ ቤቱን ለኢሐደግ አስረከበ፡፡እነዚህ ነፋሳት ሀገር በቀል ብቻ ነበሩ ወይብለን ከጠየቅን በውሰጣቸው ከጣልያን፣እንግሊዝና ቱርክ የመጡ ተወሃሲያን ስለምናገንባቸው ተረፈ ቀኝ ግዛትም ናቸው ብለን መደምደም እንችላለን፡፡

ምንም እንኳ ለለውጥ ያንጓበበው ወጣት የፊውዳሉ ስርዓት መገርሰስ አንድ ረምጃ ወደፊት ነው ብሎ
ቢያምንም እውነታው ግን ወለፈንዴ ሆነ፡፡እርስ በራሱ በአንጃ በግራንጃ ስም ተከፋፍሎ ተራረደ፡፡
ውጤቱም አምባገነን ወታደራዊ መንግስት ፈጠረ፡፡

እዚህ ላይ ቀኝ ገዢዎች ካሰመሩት የፍርሃት መስመር በተጨማሪ የቀለም ሽብሮች የራሳቸውን ግብአት ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ኢሕአደግ ስልጣን ሲይዝ “ሴይጣን በኢትዮጵያ ታሰረ ! መልካም ዘመን መጣ ! ችግራችንን የሚፈታ ህገመንግስት እነሆ ” ላሉ ወገኖች በምድሪቱ የጦርነት ነጋሪት ሳይጎሽም ሶስት አመት ማለፍ አልተቻለም ፡፡ ከዚያ ምኑ ቅጡ ፓርላማው የእንቧይ ካብ ሆነ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ቁስልም አመርቅዞ ነቀርሳ ሆነ፡፡ሁሉም የየራሱን የፍርሃት መስመር አደመቀ፡፡

ኢህአዴግ ሃያ አንድ አመት ኢትዮጵያን ካስተዳደረ ቧኃላ “ፈርቶ አደር” የተባለ አንድ ትልቅ የሕብረተሰብ ክፍል ሀገሪቷን እያጥለቀለቀ ይገኛል፡፡ገዢው ፓርቲም ትውለዱን ከፍርሃት ቅንብቡ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ ፍረሃቱን ፣አንድ ለአምስት፣ ሲያደራጅለት ነው የሚታየው፡፡

ምርጫ 97 የታሰርንበትን የፍረሃት ሰንሰለት ይበጣጥስልናል ብለን ስንጠብቅ፣ሁለት ያለ ሰፈራቸው የተገናኙ ውሾች ወዲያና ወዲህ ሆነው በነከስኩህ ሞክረኝ አይነት ጥርሳቸውን አግጠው እንደሚጯጯሁ አደረገን፡፡ ይህን ተከትሎ አለም አቀፋዊ የፍርሃት ቅይድ ገዚው ፓርቲ ላይ ኤች አር፣ጄኖሳይድ… በሚል ስሞች ተሰሩበት፡፡

ይህን ነብሰ በላ የፍርሃት ቅይድ ደበበ ሰይፉ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” በሚለው የግጥም መጽሃፉ በ
“ፍርሃት አዶ ከበሬ” ግጥሙ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

ፍረሃት አዶ ከበሬ
ፍረሃት አዶ ከበሬ
አይ እናት አይምሬ
የቁም መቃብሬ
የቅዠት ሀገሬ፡፡
ከስጋ ከነፍሴ ከደሜ ቆንጥሬ
ከአጥንቴ ሰንጥሬ፤
ምስህን ሰጥቼ ላመልህ ገብሬ፤

ያው ነህ አንተ ገና
ልጓምህ አይላላ፡፡
ትጋለበኛለህ በእሾህ በቆንጥር ላይ
ጨለማ እንደ ግራር በቅሎበት በሚታይ
አንዲት ዘሀ – ጮራ
በማትደፍርበት
እውነት – ፍቅር – ውበት
በተቀበሩበት፡፡

ታዲያ ሲጋለቡ የፈራ ፈረስ ቦኃላ እግሮቹ ቆሞ ማሽካካቱ አይቀርምና ሰውኛው ፉከራም ፍርሃትን ለማባረር ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

ምንም እንኳን ሁሉም የኢህአዴግ አመራሮች አንድት አይነት ናቸው ማለት ባይቻልም፣መፍቅሬ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ከነዚህ ወገን ያልሆነው የቀድሞው የኢህአዴግ ደህንነት ሓላፊ የነበረው አቶ ብሰራት አማረ “ፍኖተ ገድል” በሚለው መጽሃፉ የፎከራት ፉከራ የደበበ አዶ ከበሬ አይነቷን እነደሆነች የገጥሙን ስንኞች መጽሐፉ ውስጥ ያለውን መንፈስ አጋላጭ ኛቸው ፡፡

ብሰራት በፍኖተ ገድል ሲፎክር እነ አቦይ እንቶኔ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደዱ፣ እንዲያ በል፤ ሃሃ… እያሉ ይቀበሉት እንደ ነበር ከመጽሓፉ መግቢያ ጀምሮ እሰከ መጽሓፉ ምርቃት ድረስ ሽፋን ተሰጥቶት ተመልክተናል፡፡

የመጽሓፉ ፍልስፍና ሲታይ በናዚዝም ተጀምሮ ፣ በጥንት ግሪካውን አሳዛኝ የአማልክት ታሪክ የተደመደመ ነው፡፡መጽሓፉ ሊያሳይ የሚሞክረው፤በአክሱም ዘመነ የነበረው ሆነ አሁን ህውሃት የያዘው ባህል ከኢትዮጵያ ባህሎች ሁሉ የላቀ መሆኑን፣ አማራዎች በተለይም የሸዋዎቹ ከዚህ ባህል ጋር እነደማይተዋወቁ ፣ በዝርያም ቢሆን ከአክሱም መቁጠር እነደማይቸሉ መነሻቸው የት እንደሆነ
የማይታወቅ ድብልቅልቅ ህዘቦች /Low breed ?/ መሆናቸው፣ናዚዎች አይሁዶችን የክፋት ሁሉ ምንጭ እነደሚያደርጉ በፕሮቶኮል ኦፍ ጺዮን እነደሚነበበው በበሽታ አምጪ ተወሃሲያን የአውሮፓን ህዝብ ሊፈጁ ነው ተብሎ ከአንደኛው አለም ጦርነት ቦሓላ ፐሮፓጋንዳ እንደተነዛባቸው ሁሉ፣ሸዋ የክፋት ሁሉ ምንጭ እነደሆነነና ንጉስ ምኒሊክና ሰራዊቱ የትግራይን ከብት ለመጨረስ ከጣሊያን ጋር በመተባበር የበሽታ አምጪ ተውሃሲንን በትግራይ እንዳሰራጩ ነው፡፡

ስለ ትግራይ ህዝብ ጀግንነት ሲያወጋን ከአፄ ዬሃንስ ዘመን ጀምሮ በደርግ ጊዜም እነደታየው የትግራይ አንድ ወታደር ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለመጣው አስር ወታደር በቂ ነው ይለናል፡፡አቶ ብስራት እዚህ ላይ ይጠየቁና ” ይህ ጥምርታ ለሻቢያስ ይሰራል ወይ? ” በባደሜ ጦርነት ጊዜ የትግራይ ሕዝብ፣ ነፍሱን ይማረውና በእያሱ በርሄ በኩል ለወንድሙ ለኢትዮጵያ ህዝብ “አማራ አሎ በሎ፣ኦሮሞ አሎ በሎ፣አፋር አሎ በሎ…” ብሎ ያደረገውን ጥሪና የደም ግብር መልስ ፍኖተ ገድል አፈር ያስግጠዋል፡፡ግን ለምን ደራሲው የኢትዮጵያ የታሪክና የሃይማኖት መነሻ የሆነችውን ትግራይ ከሌላው ህዝብ መነጠል ፈለገ ? የውም በዚህን ጊዜ፡፡ በሽዋ (አማራ፣ጉራጌ፣ኦሮሞ…) ጥላቻን የሚያነሳሳ ታሪክስ መጻፍ ማንን ይጠቅማል ?

የግሪካውያን ሚቶሎጂ ስለ ወጣቱ ናረሲሰ እንዲህ ይላል፡፡ናርሲስ የሚባልአንድ ወጣት ቆንጆ ነበር፡፡ ኢኮ/ የገደል ማሚቱ/ የአማልክቱ ንጉስ ዜዎስ ከሌሎች ሴቶች ጋር ፍቅር ሲሰራ ሚስቱ ሄራ እነዳታውቅ በጥሩ ድምጿ ታማልላት ነበር፡፡ ሄራ ምስጢሩን ደረሰችበትና የኢኮን ድምጽ ነሳቻት፡፡ኢኮ መናገር ስለተሳናት ሰው የተናገረውን የመጨረሻ ቃል መድገም ስራዋ ሆነ፡፡በዚህ ሁኔታ ሳለች ከናረሲስ ጋር በፍቅር ወደቀች፡፡እንዴት ትንገረው ? ለአደን ወደ ጫካ በሄደበት ወቅት ጠብቃ ፍቅሯን በማቀፍ ልትገልጽለት ሞከረች፡፡ገፍቶ አባረራት፡፡ ልቧ ተሰብሮ በለቅሶ ብዘት ከስታ አካሏ ጠፍቶ የገደል ማሚቱ ሆነች፡፡ለዚህ ድረጊቱ አማልክቱ ናረሲሰን ከራሱ ምስል ጋር በፍቅር እነዲወድቅ በማድረግ ቀጡት፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስራ ፈቶ ቀኑን ሙሉ መልኩን ኩሬ ውሀ ውሰጥ ሲመለከት ይውል ጀመረ፡፡ከዚህ መጨበጫ ከሌለው ፍቅር መላቀቅ እነደማይችል ሲያውቅ እራሱን በጩቤ ወግቶ ህይወቱን አጠፋ፡፡

የአናሳነት ስሜት፣ ትምክህትና ዕብሪት የፈጠሩት ፍርሃት ደራሲውና መሰሎቹን በትለቁ የኢትዮጵያዊነት ኩሬ ውስጥ የእራሳችንን ምስል ብቻ እንይ አሰኝቷቸዋል፡፡ ይህ የ”አክሱናርሲናዚዝም” እርሾ ለዳቦ መጋገሪያነት ገና የበቃ ባይሆንም፣ የጋገረው ሪሚጦ ግን በተለያየ የኢትዮጵያ ክልል የሚኖሩ የሸዋ(አማራ፣ኦሮሞና ጉራጌ…) ህዝብ ላያ ስቃይ መሆን ከጀመረ አመታት አልፈዋል፡፡ ሪሚጦው በተጅቦነበት እሳት ከስሎ እዛው መቅረቱ አይቀሬ ነውና ፍርሃትን እያራቡ መጪውን ትውልድ በእኩይ የፖለቲካ ድር መተብተብ እኩይ ምግባር ነው፡፡

ነገሬን ለመቋጨት አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ መሪውና ተመሪው ህዝብ በፍርሃት ቅይድ ውስጥ ባለበት ሁኔታ እንዴት ሀገራዊ ርዐይና እድገት ይኖራል?

ይኸው መንገድ ይሰራል፣የባቡሩ ደግሞ ይቀጥላል፣ህንጻዎች እየቆሙ ናቸው፣ኢኮነሚው እያደገ ነው እንዳትሉኝ፡፡ ምንም እነኳን በእርዳታ፣ዕዳና ብድር ላይ የተመሰረተውን ግነባታ ይሁን ብዬ ብቀበልም የአለም ታሪክ ስለሚሞግተኝ ለሃሌሉያ የሚበቃ የምስራች አልነገራችሁኝም፡፡ የተባበሩት የሶቬይት ሪፓብሊክ፣ ዩጎዝላቪያ… መንገድና ህንጻ ገንብተው ነበሩ፣አሁን ግን የት አሉ? ሰውን እያፈረሱ ህንጻን ቢገነቡ ማን ለማን እደተንፈጠረ አለማወቅ ብቻነው የሚሆነው፡፡

ስለዚህም ሁላችን ኢትዬጵያውያን ይህ አስሮ የያዘንን የፍረሃት ቅይድ ሰበረን ለመውጣት አንድ ብለን ጉዞ እንጀምር፡፡ እንዴት? …

የሰምናወርቅ አስትያየት
በዚህ ብሎግ ላይ በውጡት ሃሳቦችና ፅሁፎች  ዙሪያ አስትያየት ካላችሁ ላኩልን። እናትመዋለን። ሰምናወርቅ ለታፈኑ ፀሐፍት መነጋገሪያ የወይይት መድረክ እንድትሆን ክፍት ናት።
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close