የኢትዮጵያ ሠራዊት በኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ፈጸመ

የኢትዮጵያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት ኤርትራ የነፃነት ቀኗን ስታከብር በነበረበት ዕለት፣ ባድመ በሚገኘው የኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ማድረሱ ተገለጸ፡፡ ወታደራዊ ጥቃቱ በትግራይ አካባቢ በቅርቡ በኤርትራ ጦር ታፍነው ለተወሰዱ ኢትዮጵያውያን አጸፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡

ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. የኤርትራን ድንበር ጥሶ የገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባድመ አካባቢ በሰፈረው በአንድ ብርጌድ የኤርትራ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጾአል፡፡

በጥቃቱ በርካታ የኤርትራ ወታደሮች የመቁሰልና የሞት አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን፣ እስከ ሻለቃ ማዕረግ ያላቸው በርካታ የኤርትራ ጦር አመራሮችም እጃቸውን እንደሰጡ ታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከወራት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጽመው ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር ሰሞኑን በኤርትራ ላይ የወሰደው ወታደራዊ ጥቃት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ አካባቢ ለሚፈጽሙት አፈና አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወሰደውን ዕርምጃ በማስመልከት ከኤርትራ በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡
(ምንጭ ሪፖርተር)

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close