አይተ መለስ ዜናዊ መቀሌ ፍርድ ቤት ምስክር ሆነው ሊቀርቡ ነው

 

መለስ በምስክርነት ፍ/ቤት ሊቀርቡ ነው
*ከምስክሮቹ መካከል ሶስቱ ጄነራሎች ናቸው
*የቀድሞ የህወሓት አመራሮችም ይገኙበታል
በዘሪሁን ሙሉጌታ (የሰንደቅ ጋዜጣ ሪፖርተር)

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ አስራስምንት የሚሆኑ የአሁኑ እና የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ለምስክርነት መቐለ ከተማ ፍ/ቤት ሊጠሩ ነው። አመራሮቹ ለምስክርነት የተጠሩት የህወሓት መስራች ከነበሩት አንዱ አቶ አስገደ ገ/ ስላሴ ላይ አቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የስም ማጥፋት ክስ ተከላከሉ በመባላቸው ነው። የመቀሌ ዞን ሰሜን ወረዳ ምድብ ፍ/ቤት ግንቦት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቶ አስገደ ቀደም ሲል …በትግርኛ ቋንቋ ‘‘ጋሃዲሦስት’’ በሚል ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ በምዕራፍ 29 ከገፅ 359 ጀምሮ ባለው አንድ ምዕራፍ ላይ አንድ የቀድሞ የህወሓት የፀጥታና ደህንነት አባልን ስም ማጥፋታቸው በአቃቤ ሕግ በመረጋገጡ ክሱን እንዲከላከሉ መወሰኑን ተከትሎ አቶ አስገደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የቀድሞ 18 ህወሓት አመራሮችን ለምስክርነት ለመጥራት መገደዳቸው ታውቋል።

ለአቶ አስገደ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ከትናንት በስቲያ ክሱ ለቀረበለት ፍ/ቤት ምስክሮቹ ታዘው መቅረብ እንዲችሉ ከሳሽ አቶ አስገደ ማዘዣ መጠየቃቸው የተገለፀ ሲሆን የፍርድ ቤቱ ዳኛ ወ/ሮ መብሪሂት አድሽ በውጪ ሀገር ያሉትን ጨምሮ ለሁሉም ምስክሮች የመጓጓዣ አበል እንዲሰጡ ለከሳሽ ጥያቄ በማቅረባቸው ከሳሽም ከጠበቃዬ ጋር ልማከር በማለታቸው ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ለዛሬ ግንቦት 29 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

አቶ አስገደ በመከላከያ ምስክርነት ከጠሩዋቸው የመከላከያ ማስረጃዎች መካከል አቶ መለስ ዜናዊ፣ አምባሳደር ሙሉጌታ አለምሰገድ (ነዋሪነታቸው በጣሊያን) አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ መኮንን (የአባታቸው ስም ለጊዜው ያልታወቀ)፣ አቶ ወልደስላሴ አብርሃ (በትግራይ የሚገኙ)፣ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣ አቶ ፍሬው ተስፋሚካኤል (በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኙ)፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ አባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስዬ አብርሃ (በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ)፣ አቶ ስዩም መስፍን (ቻይና በአምባሳደርነት የሚያገለግሉ)፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ኪሮስ አቡዬ፣ አቶ አክሊሉ ኪዳነማርያም (በአድማስ ኮሌጅ አዲስ አበባ የሚገኙ) እና ሦስት የመከላከያ ጄኔራሎች ይገኙበታል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ (አቶ አስገደ) መከላከያ ምስክሮቹን የማጓጓዣ እና አበል ይችሉ እንደሆነ ጠይቋቸው አቶ አስገደም ከጠበቃቸው ጋር ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃሉ። የተጠቀሱት ምስክሮች በመንግስት ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ያሉ ባለስልጣናትን በመከላከያ ምስክርነት በመጥራት በሀገሪቱ የችሎት ታሪክ ቀዳሚ ከመሆናቸውም በላይ ግለሰቡ መብታቸውን ለማስከበርና የሕግ የበላይነት መኖሩን አለመኖሩን የሚያሳይ ሊሆን እንደሚችል እየተጠቀሰ ነው። የተጠቀሱት ምስክሮች ለአቶ አስገደ ክስ መከላከያ ሆነው እንዲያስረዱ የሚፈለገው በ17 አመቱ ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል የተፈፀመ ታሪካዊ ሂደቶች እንዲያስረዱ በሚል ሲሆን ምስክሮቹ ደግሞ የትግሉን ታሪካዊ አመጣጥ ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው ነው ተብሏል።

አቶ አስገደ በዚህ ክስ ሶስት ጊዜ ታስረው በዋስ የተፈቱ ሲሆን በአንድ ወቅት ክሱ በይርጋ ተዘግቷል ተብለው ነፃ ከወጡ በኋላ እንደገና አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቁ ክሱ ከተንቀሳቀሰ በኋላ ተከላከሉ የሚል ብይን ፍ/ቤቱ አስተላልፏል።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close