“የእኔ ኮሚኒቲ የእግር ኳስ ኮሚኒቲ ነው” አቶ ጌታቸው ተስፋዬ/ESFNA ፕሬዚዳንት/

gech article 1 with picture (excusive interviwe with Hiber radio reporter Netsanet Solomon )

“የእኔ ኮሚኒቲ የእግር ኳስ ኮሚኒቲ ነው”

አቶ ጌታቸው ተስፋዬ/ESFNA ፕሬዚዳንት/

/በነፃነት ሰለሞን/

  • ጥይት ቤት
  • አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
  • MIT
  • ኒዩክለር ኢነርጂ
  • ኪልማንጃሮ ተራራ

በምን? እንዴት? በማን እና የት ተገናኙ?

ወቅቱ ኢትዮጵያውያን መንግስታቸውን ለመተካት የሚጣደፉበት ግዜ ነበር። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1965-1966 ዓመተ ምህረት። ተማሪው፣ ገበሬው፣ የመንግስት ሰራተኛው ሁሉ ለውጥ የፈለገበት፤ ሁሉም በያለበት “ይሄ አገዛዝ በቃን!” እያለ የጮኸበት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዋነኞቹ የለውጡ አራማጆች እንደሆኑ ይጠቀሳል። በዘመኑ ከነበሩ ወጣቶች ሁሉ ሰላማዊ ሰልፍ ያልወጣ፣ የተቃውሞ ድምጹን ያላሰማ፣ የትምህርት ክፍለ ግዜውን በጥብጦና አስበጥብጦ ጩኸቱን ያላስተጋባ አልነበረም ማለት ይቻላል።

ትምህርት ቤት ተረብሾ ወደ መንገድ ሰልፍ ሲወጣ ሁሉም ሲፅፍ ያደረውን መፈክር ያወጣል። ጉሮሮውን ለጩኸት ይስላል። ግጥምና የተቃውሞ መፈክሮቹን ያሰማል።

በዚህ የተቃውሞ እሳት በተቀጣጠለበት የኢትዮጵያ አብዮት አንድ ወጣት ብዙም ተሳታፊ እንዳልነበረ ይነገራል። ለዛውም የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪ! በዕውነት ለማመን የሚከብድ ይመስላል።

ይህ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሳይንስ ፋክልቲ ተማሪ፣ ተማሪዎች ለጩኸትና ግርግር ሲበባሰቡ፤ የአንዱን የተቃውሞ ንግግር ለመስማት ሲጠራሩ፣  አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ሲዶልቱ እሱ ብዙም በአካባቢው አይታይም።

ይህ ሰው ጥናቱን ለብቻው እያስኬደ ነው? ለፈተና እየተዘጋጀ ነው? ወይስ ላቦራቶሪ ተቀምጦ እየተመራመረ? ኧረ እሱ ምን ተዳው? በዚህ ግርግር ለብቻው ፈተና አይቀመጥ የምን ጥናት ነው? ለውጡ እንደሁ አይቀሬ ነው።

እናም ከዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ እሱን ምን ነጠለው?

ኳስ! ኳስ!! ኳስ!!! የኳስ ፍቅር!!!! የእግር ኳስ ፍቅር!!!!!  ለእሱ ህይወት… ኑሮ… ሰላም… ፍቅር… እግር ኳስና የኳስ ፍቅር ብቻ! ያኔም አሁንም! ይህ ሰው ማነው?

የአንጋፋው የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ።

ጌታቸው ተስፋዬ ተወልዶ ያደገው ከአራት ኪሎ ዝቅ ብሎ በዓታ ለማሪያም ገዳም  ወይም ጥይት ቤት በመባል የሚታወቀው አካባቢ ነው። የቄስ ትምህርት ቤት ተምሮ… ዳዊት ደግሞ ነው ያደገው።

የባዕታ ለማርያም ገዳም አገልጋይ የነበሩት ወላጅ አባቱ ዳዊት ከመድገምም በላይ እንዲዘልቅ ነበር ፍላጎታቸው። እንደው ዓለማዊው ትምህርት ቀርቶ ፈጣሪውን አገልጋይ ወንድ ልጅ ማግኘት? በትንሹ ድቁና፤ ከዛ በላይ ምንም አይፈልጉም ነበር።

የጌታቸው ታላላቅ እህቶች ግን ከአባታቸው የተለየ ሀሳብ ነበራቸው። ዘመናዊ ትምህርት ቤትም እንዲሄድ አባባን ሞገቷቸው። እናም ዳግማዊ ምንሊክ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄደ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ተፈሪ መኮንን ቀጠለ።

ጌታቸው በትምህርት ቤት የዕረፍት ሰዓትም ሆነ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ እንዲሁም በዕረፍት ቀኑ እግር ኳስ ምትክ የሌለው መዝናኛው ነበር። ከህፃናት እኩያ ጓደኞቹ ጋር ሌላ የተጫወተውን ጨዋታ በቅጡ አያስታውሰውም። “ነጋ ጠባ ኳስ ነው” ሲል ነው ያን ዘመን የሚያስታውሰው።

ሮተሪ ክለብ ውስጥ የጥይት ናዳ ክለብ፤ ከፍ ሲልም ሸዋ ሊግ፤ ቀጥሎም የአራት ኪሎ ዩንቨርስቲ የእግር ኳስ ክለብ በልጅነት የተሳተፈባቸው የሃገር ቤት ክለቦቹ ናቸው። ክለቦቹ ውጤታማ እንደነበሩም ያስታውሳል።

በኋላም ዳኘው ለሚባለው ክለብ ለታዳጊ ቡድን ለተወሰነ ግዜ ተጫውቷል። ነገር ግን በትምህርቱም የዋዛ አልነበረም።

ብዙ ግዜውን ለኳስ አሳልፎ የሚሰጠው ጌታቸው የማትሪክ ፈተናን በከፍተኛ ማዕረግ አልፎ ነበር ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የገባው።

ጥያቄ፦ ለመሆኑ የዩኒቨርስቲ ቆይታህ ምን ይመስላል?

መልስ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ፋክልቲ ተማሪ ነበርኩ። ለ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ የእግር ኳስ ቡድን እጫወት ነበር። የሚገርመው ነገር ከቡድኑ እኔ ብቻ ነበርኩ የአዲስ አበባ ልጅ። የቡድኑ አባላት በብዛት ከኤርትራ እና ከትግራይ የመጡ ልጆች ነበሩ። የነበረን ፍቅርና መከባበር በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም።

በአጋጣሚ አንድ ሴሚስተር እንደተጫወትን የየካቲቱ አብዮት ተቀሰቀሰ። ሁል ግዜ ረብሻ፣ ቀን በቀን ግርግር ነበር። ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል…የትምህርታችን ነገር ጥያቄ ውስጥ ነበር።

ጥያቄ፦ ወደ አሜሪካ በዛ ወቅት እንደመጣህ ይነገራል። በምን አጋጣሚ ነው የመጣኸው?

መልስ፦ አሜሪካን የመጣሁት በግርግሩ ሰአት ነው። እኔ ስመጣ ጃንሆይ ስልጣን ላይ ነበሩ። እህቶቼ እዚህ ስለነበሩ ስኮላር ሽፕ ሞክረውልኝ ለትምህርት ነው የመጣሁት። መጥቼም ሀዋርድ ዩንቨርስቲ /ዋሽንግተን ዲሲ/ ነው የገባሁት። ሜካኒካል ኢንጅነሪነግ ነው ያጠናሁት።

<ሶከር ስኪል> የሚል ኮርስ ወስጄ ነበር። ያንን ኮርስ የሰጠኝ መምህር የሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ነበር። መምህሩ ወደ “ቡድኑ መምጣት አለብህ” አለኝና ሄድኩ። ልምምድ ጀመርኩ።

የሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረ አምደ ሚካኤል የሚባል  ኢትዮጵያዊ ነበር። ብዙዎቹ የቡድኑ አባላት በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾ ነበሩ። ሀዋርድም በ1974 የኮሌጅ ሻምፒዮን ሆኖ ነበር። እኔ ግን አልቀጠልኩም ነበር።

*    *     *

የጌታቸው ቤተሰቦች ልጁ ጎበዝ ተማሪ እንደሆነ ያውቃሉ። የሚያመጣቸው ውጤቶች መሬት ጠብ የሚሉ አልነበሩም። ይሄ ከኳስ ጋር የወደቀው ፍቅር ግን እንቅልፍ ነስቷቸዋል። የውጭ ሀገር ትምህርቱን እንደ ትልቅ መፍትሄ ነበር የወሰዱት። እነሱ ጎበዙ ተማሪ የበለጠ ጎበዝ፣ እጅግ በጣም ጎበዝ እንዲሆን ነው ፍላጎታቸው።

ታዲያ በሰው ሀገር ይፈጽማል ብለው ያልገመቱትን ነገር ሰሙ።  ማመን የሚከብድ ነገር ነበር ለእነሱ! በውጭ ሀገር ትምህርት ላይ እ…ግ…ር…ኳ…ስ?!

ከዚህ በፊት የሰሙት ታሪክ አለ። የአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ልጅ የዩኒቨርስቲውን እግር ኳስ ቡድን ተቀላቅሎ ትምህረቱን ጉድ ሆኗል! ጌቾስ ምን ማስተማመኛ አለው?

ይሄኔ አብረውት ያሉ ታላላቅ እህቶቹ ወደ አባባ መልዕክት ይልካሉ። የመጨረሻ እርምጃም እንዲወስዱ አባታቸውን ጠየቋቸው። ይህን ያህል ርቀት ላይ ያለን ወጣት በምን መቅጣት የቻላቸዋል? እናም አባባ “ልጄ ይሄን ኳስ ከዚህ በኋላ መለስ ብለህ ታይና ውጉዝ ከመአርዮስ!” አለቀ!

ጥያቄ፦ እንደው የአባባ ውግዘት ባይመጣስ ከዩኒቨርስቲ ትምህረት ጋ ኳስ ጨዋታ ይዘለቅ ነበር?

መልስ፦ በርግጥ የዩንቨርስቲ ተማሪ ሆኖ እግር ኳስ መጫወት ከባድ ይሆን ነበር። ስለዚህ የኮሌጁን ትቼ ለዋሽንግተን ዲሲ ብሪቲሽ ኢንባሲ ቡድን መጫወት ጀመርኩ።

ጥያቄ፦ በሃዋርድ ቆይታህ ትምህርትና ውጥጤትህስ እንዴት ነበር?

መልስ፦ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። /SUMMA CUM LAUDE- 1ST IN CLASS ነው የጨረሰው/። ጥሩ ውጤት ስለነበረኝም ነው ለሁለተኛ ዲግሪ ስኮላር ሽፕ ያገኘሁት። /MASSACHUSETTS INSTITUTE OF TECHNOLOGY/ M.I.T.  ገብቼም ከ5 ነጥብ 4.8 አምጥቼ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ማስተርሴን ያዘኩ።

ጥያቄ፦ ከዛስ ወደ ስራ ዓለም?

መልስ፦ዶክትሬቴን መቀጠል ነበር የኔ ሀሳብ፤ በ1979 MIDDLE TOWEN PELSENVENIA TMI /THREE MILE ISLAND/ የሚባል የኒኩለር ኤሌትሪክ ማመንጫ አደጋ ነበር። በዚህ ምክንያት የአሜሪካ መንግስት የኒክለር ምርምር ዘርፏን በዲግሪ ምሩቃን ለመተካት መንቀሳቀስ የጀመረችበት ወቅት ነበር። በወቅቱ የዘርፉ ምሁራን በየዩኒቨርስቲው እየሄዱ በሳይንስ እና ሂሳብ የላቀ ውጤት ያመጡ የማዕረግ ተማሪዎችን ይመለምሉ ነበር። እኔም ጥሩ ውጤት ስለነበረኝ ተመረጥኩ።

እኔ በወቅቱ ለዶክትሬት ትምህርት ዕጩ ነበርኩ። ሆኖም የስራ እድሉን ሳገኝ ለአማካሪ መምህሬ ነገርኩት። ‘ጥሩ ዕድል ነው፣ አንድ አመት ሰርተህ መመለስ ተችላለህ፣ ስኮላርህ ይጠብቅሃል’ አለኝ። …እኔ ግን በስራው አለም ቀልጨ ቀረሁ።

ጥያቄ፦ በአሁኑ ሰዓት የት እየሰራህ ነው?

መልስ፦ ለአሜሪካ መንግስት የሲቪል ኒኩለር ኢነርጂ ዘርፍ NUCLEAR REGULATORY COMMISSION /NRC/ ነው የምሰራው።

* *  *

ጥያቄ፤- እንግዲህ አሁን ዛሬ አንተ በፕሬዚዳንትነት የምትመራው ፌዴሬሽን ወደ ተጠነሰሰበት 1980ዎቹ ደርሰናል። ስለዛ ግዜ ምን ታስታውሳለህ?

መልስ፤- በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ መምጣት ጀመሩ ።  ዲሲ አካባቢ እየተሰባሰብን እንጫወት ነበር። ቦስተን ትምህርት ቤት ስሄድም እንደዛው። ከቦስተን ዲሲ እየተመላለስን ግጥሚያ ማድረግ ጀምረን ነበር።

በኋላ ሂዩስተን ቴክሳስ የነዳጅ ዘይት ምርት ብዙ ስራ ሲፈጥር ወደዛ የሄዱ ኢትዮጵያውን በ1984 ሂዩስተን፤ ዳላስ፤ አትላንታና ዋሽንግተን ዲሲ ሆነው የመጀመሪያውን ውድድር አደረጉ። ከ29 ዓመት በፊት!

በቀጣዩ አመት እኔም ከቦስተን ቡድን ጋ ፌደሬሽኑን ተቀላቀልኩ።/1985-1987/

ጌታቸው ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋ በመሆን የኢትዮ ሜሪላንድ ቡድን/1988-1989/፣ የኒዮርክ አባይ ቡድን /1990/፣ የቅዱስ ሚካኤል ሜሪላንድ ቡድን/2001 እስከ አሁን/  ከመስራች እስከ ተጫዋችነትኟ ቡድን መሪነት፤ የአሰልጣኝነት ኮርስ በመውሰድም በአሰልጣኝነትና በፌዴሬሽኑም የቦርድ አባልነት አገልግሏል።

ጥያቄ፦ የESFNA ፕሬዚዳንት ሆነህ መቼ ተመረጥክ?

መልስ፦ በኦክቶበር 2011። የመጀመሪያ ዓመቴ ነው። የመጀመሪያ ቶርናመንት ለማዘጋጀት እየሰራን ነው።

ጥያቄ፦ የዳላስ ዝግጅት ምን ደርሷል?

ጌታቸው፡- ዝግጅቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ሆቴሎችን አመቻችተናል። ለእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው። አርቲስቶችን እያነጋገርን ነው። የ”ኢትዮጵያ ቀን” ዝግጅትም ደማቅ እንዲሆን  አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማሟላት እየጣርን ነው።

የመጀመሪያዬ ስለሆነም፣ የገንዘብ አቅሙ የሚያወላዳ ባልሆነበት ሰዓት የምንችለውን ሁሉ እየጣርን ነው። የቦርድ አባላት በአጠቃላይ ገንዘባችንን ግዜያችንን መስዕዋት በማድረግ ህዝባችንን ለማስደሰት በጣም ደስ ብሎን እየተሯሯጥን ነው። በጥሩ ዝግጅት እንደምንገናኝም ተስፋ አለኝ።  በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን ከያላችሁበት ወደ ዳላስ እንድትመጡ በፌዴሬሽኑ ስም በአክብሮት እጋብዛለሁ።

ጥያቄ፦ ጌታቸው ፖለቲከኛ ነው ለሚሉ ምንድነው መልስህ?

መልስ፦ እኔ ከሀገር ስወጣ ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነበር። እዚህም ከመጣሁ በኋላም በ1970ዎቹ ትልቅ የፖለቲካ ነውጥ ነበር። ደርግ፣ ኢህአፓ፣ መኢሶን…የሰሜን አሜሪካ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሌሎችም ነበሩ።

“መጀመሪያ ትግል…ከዛ ትምህርት” በሚባልበት በዛ የትግል ዘመን፤ በርካታ ተማሪዎች ትምህረታቸውን አቋርጦ ወደ ትግል በተቀላቀለበት ዘመን ፤ እኔ ትምህርቴን ሳላቋርጥ ጨርሻለሁ። ለተከፈለው መስዋትና ለነበረው መነሳሳት ትልቅ አክብሮት አለኝ። አሁንም ለሀገራቸው መልካም በመመኘት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ለሚለፉ አድናቆት አለኝ።  እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሃገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል፤ ይቆረቁረኛል። ሃገሬን ስለምወድ ያልረገጥኩት ገዳም ያልደረስኩበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም። ባይገርምሽ ራስ ዳሽንን በእግሬ ወጥቻለሁ።

ለኢትዮጵያ ኮሚኒቲና ቤተ ክርስቲያናት ለሌሎችም ልቤ ለፈቀደው በጎ ለመሰለኝ ጉዳዮች በሙሉ ከጉልበት እስከ ገንዘብ እርዳታ አደርጋለሁ። በዋናነት ግን የኔ ፍቅርና ግዜ ለእግር ኳስ ነው የሚውለው። ኳስ ደግሞ ፖለቲካ አያስፈልገውም። የፌዴሬሽኑም የ29 ዓመት ፅናት እዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። ነፃ የሆነ፣ ሁሉን በነፃነትና በእኩል የሚያገለግል፣ ከየትኛውም የፖለቲካ አቋም የፀዳ ፌዴሬሽን መሆን አለበት። የኔም እምነት ይሄ ነው።

ጥያቄ፦ ታዲያ የትዳር? የልጆችስ ነገር? ሁሉ በኳስ ነው የተተካው?

መልስ፤- ኧረ ባለትዳርና የልጆች አባት ነኝ።

*        *        *

ጌታቸው የትዳር አጋሩን ወ/ሮ ሰብለ አያሌውን የተዋወቃት በ1984 ሲሆን ትዳር የመሰረቱት በ1987 እንደነበር ያስታውሳል። በ28 ዓመታት የትዳር ህይወታቸው አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶች ልጆችን አፍርተዋል።

ሶስቱም ልጆቻቸው የአባታቸውን ያህል ባይጋነንም ለእግር ኳስ ፍቅር አላቸው።

ወንድ ልጁ በ2005  እና በ 2006 ቶርናመንት ላይ ለሜሪላንድ ቅዱስ ሚካኤል ቡድን ተጫውቷል። አባቱ ፌዴሬሽኑ ሲጀመር በተሳተፈበት ውድድር ልጁም ተወልዶ አድጎ መሳተፉ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር።

*        *        *

ጥያቄ፦ ልጅህ ሲጫወት ስትመለከት ምን ተሰማህ?

መልስ፦ እንደ አባት በጣም ደስ አለኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ደስ ብሏቸው ነበር። ከሁሉም በላይ ቶርናመንቱ የኢትዮጵያን መሰባሰቢያ፣ የጓደኛና ዘመድ መገናኛ፣ የተጠፋፋ የልጅነት ጓደኛማች ሁሉ የሚገናኝበት፤ የሀገር ፍቅርና ናፍቆት የሚገለጽበት መሆኑ ጭምር ያስደስተኛል። ሁሌም በናፍቆት የምጠብቀው ግዜ ቢኖር ይህን ወር ነው።

የቤተሰቡን እገዛ ሲገልፅ “ከአባቴ በስተቀር ሁሉም ደጋፊዎቼ ብቻ ሳይሆኑ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ናቸው” የሚለው ጌታቸው “ አባቴ 97 ዓመቱ ነው ለምን እንደምጫወት ፈጽሞ አይገባውም፤ አሁን ግን ሬዲዮ እየሰማ  ለእኔ ማገዝ ጀምሯል፤ ጓደኞቼን ሲያገኝ አንተ የየትኛው ነህ? ማለት ጀምሯል” ይላል።

ጥያቄ፦ ለፌዴሬሽኑ ህልውና ምን ራዕይ አለህ?

መልስ፦ የፌዴሬሽኑ ስራ በየቀኑ ከህዝቡ ጋ ፊት ለፊት የሚያገናኝ ስራ አይደለም። የስራው ውጤት የሚታየው በአመት አንዴ ለዚሁ ዝግጅት ነው። ፌዴሬሽናችን ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው፣ በህዝብ የሚታመን፣ ለዘመናት የሚዘልቅ፣ ለትውልድ የሚተላለፍ እንዲሆን እጥራለሁ።

ጥቂት ስለ ጌታቸው

  • ጌታቸው በትርፍ ግዜው ተራራ መውጣት /hiking/ ይወዳል። ራስ ዳሸን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ በርዝመቱ አንደኛ የሆነውን የኪሊማንጀሮ ተራራን ወጥቷል። 14 የአሜሪካን ስቴቶችን የሚያቋርጠው Appalachian Trail በመባል የሚታወቀውና 3510 k.m ርዝመት ያለውን ጉዞ ለመጨረስ ጥቂት ቀርቶታል። በዚህም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል።
  • በኢት. ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ከፍተኛ  ትኩረት የሚሰጠውን አብይ ፆም ላለፉት 30 ዓመታት አንዴም ሳያቋርጥ አክፍሏል።

ሌሎች ስለ ጌታቸው

ባለቤቴ ለእኔ ጥሩ ባል፤ ለልጆቹም ጠንካራ አባት ነው። ከስራ እና ልጆቹን ከመንከባከብ ውጪ ሌላው ህይወቱ እግር ኳስ ነው። ኳስ የህይወቱ አንድ አካል ነው!

ዛሬ ልጆቻችን አድገውልናል። ሁሉም ዩኒቨርስቲ ደረጃ ደርሰውልናል። ባህላቸውን እና ቋንቋቸውን አከባሪዎች ናቸው።

በስራው ባህሪ ወደ ተለያዩ ሀገራት ይሄዳል። ግዜውን ሰውቶ ፌዴሬሽኑን የሚጠቅም ስራ እንደሚሰራ አልጠራጠርም። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ተስፋ ጥለውበታል። ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚያገኙኝ ሰዎች “ጌታቸው ፌዴሬሽኑ ካለበት ችግር ሊያላቅቀው የሚችል ሰው ነው። በዚህ ሰአት በመመረጡ ደስ ብሎናል” ይሉኛል። የማያውቁኝ ሰዎች ሳይቀር ነው እግዚያብሔር ይርዳው የሚሉኝ።

ጌታቸው ስለ እውነት የሚኖር ሰው ነው። ውሸታምና ሌባ አይወድም። ያመነበትን ከማድረግም ወደ ኋላ የሚል ሰው አይደለም። በይሉኝታ እና ሰው ምን ይለኛል በሚል ስጋትም አያፈገፍግም።  እውነት ከሆነ ስለ እውነት የሚመጣውን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ ነው። በዚህም የእውነት አምላክ እንደሚረዳው አምናለሁ። ልዑል እግዚያብሄር ሁላችንንም እንዲረዳንም የዘወትር ፀሎቴ ነው።

ባለቤቱ ወ/ሮ ሰብለ አያሌው /Dunkirk – Maryland/

*        *        *

ጌታቸው የ30 ዓመት ጓደኛዬ ነው። ቦስተን ማስተርሱን ሲማር ጀምሮ ነው የማውቀው። እኔና እሱን ኳስ ነው ያገናኘን። ሁለታችንም አብረን እንጫወት ነበር።

የኳስ ፍቅሩን በተመለከተ ስፖርት በጣም ይወዳል፣ ከሀገር ቤት ከልጅነቱ ጀምሮ ነው ኳስ ይጫወት የነበረው። ለእግር ኳስ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ችሎታም ያለው ልጅ ነው።

በባህሪው ግልፅ፣ የሚመስለውንና ያመነበትን ነገር ፊት ለፊት የሚናገር እውነተኛ ሰው ነው። በሰው ጉዳይ በፍፁም ጣልቃ አይገባም። የሚሰራውን ስራም በጥራትና በትክክል እንጂ ሰራሁ ለማለት ያህል ብቻ አይገባበትም። በጣም ጠንካራ የስራ ሰው ነው።

አሁን ፌዴሬሽኑ ላይ የተጣለበትን ሀላፊነትም በብቃት እንደሚወጣው አምናለሁ። ከባድ ሰዓት ላይ ነው የተመረጠው፤ ይህን ከባድ ሰዓት ግን ከጌታቸው በላይ የሚወጣው ሰው አለ በዬ አላምንም። በጣም እድለኞች ነን በምርጫው ሰዓት ሃላፊነቱን እሺ ብሎ መቀበሉ።

ለቤተሰቡም ለሃገሩም ከፍተኛ ፍቅርና ከበሬታ ያለው፣ ልጆቹንም ጥሩ ጥሩ ቦታ ያደረሰ ሰው ነው።

መሰለ ክፍሌ /Boston – Massachusetts/

*   *   *

እንደ ወንድም ደግ እና ተቆርቋሪ፤ ቤተሰብ አክባሪ፤ ለቤተሰቡ ከፍተኛ ፍቅር ያለው ሰው ነው። ጎበዝ ተማሪ፣ ጠንካራ ሰራተኛም ነው። ለቤተሰቡና ለጓደኞቹ ተንከባካቢ፣ ለችግር ፈጥኖ ደራሽም ነው።

አንድ ነገር መስራት ከፈለገ ምንም ነገር አያግደውም። የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ ይወጣዋል። ሁሉን ነገር በጥራትና በብቃት ለመወጣት የማያደርገው ጥረት የለም። ከልቡ ስለሚሰራም ሁል ግዜም ይሳካለታል።

ፌዴሬሽኑን በተመለከተ ሁኔታው ከባድ ደረጃ ላይ እንዳለ ይታወቃል። ሆኖም ሀላፊነቱን ከእግዚአብሔር ጋር በርግጠኛነት ይወጣል። እግዜር ይርዳው።

ታናሽ ወንድም አንተነህ /ሂሊ/ /Silver Spring – Maryland/

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close