“በእነ እስክንድር ነጋ ችሎት የተሰየሙት ዳኛ የእውቀት ችግር የለባቸውም”

ከፍተኛ የህግ ባለሙያ
እውቁ የነጻ ፕሬስ አባል፡ ጋዜጠኛ እና ጸሃፊ እስክንድር ነጋ እና የአንድነት ፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ሃያ አራት ጋዜጠኞች ፡የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች በኢህአዴግ መራሹ ፍርድ ቤት ከአስር ወራት በላይ መመላለስ በሁዋሏ ሰሞኑን “ፋተኛ ናችሁ” የሚል ውሳኔ ማሰተላለፉ ይታወቃል፡፡ ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው የህግ አንቀጽ በቅርቡ ረቅቆ የጸደቀው የጸረ አሸባሪነት እና የተሻሻለው የፕሬስ ህግ መሆኑን የተገነዘቡ በረካታ እለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በውሳኔው በእጅጉ ያዘኑ እና የአገሪቱ የዲሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት አያያያዝ በብርቱ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ለገዤው የኢህዴግ መንግስት ባለስልጣናት ወሳኔው እንዲያስቀይሩ ተማጽኖአቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የሁኔታውን ወቅታዊነት እና አስሳቢነት በተመለከት በምድረ አሜሪካ ከላስ ቭጋስ ከተማ የሚሰራጨው የህብር ራዲዮ በአዲስ አበባ የሚኖሩ እና በህግ እና ተዛማጅ ስራዎች የሚተዳደሩ አንድ ታዋቂ የህግ ባለሙያ አነጋግሯል፡፡ እኝህ ባለሙያ በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ካላው ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ጋር በተያያዝ በዜጎች ላይ የሚደረጉትን ማስፈራራት ፡ ወከባዋች እና እስራትን ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት ሰማቸው እንዳይጠቀስ በቅድሚያ ጠይቀዋል፡፡ የዝግጅት ክፍሉም ጥያቄያችውን በማክበር “አቶ አወቀ” በሚል የብእር ስም በመጠቀም የራዲዮው የምእራብ አውሮፓ ልዩ ዘጋቢ ታምሩ ገዳ ቃለምልልሱን አንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንሎት ፡፡
ጥያቄ፡- እርሶ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰለነበሩት ሆነ አሁን ስላሉት በጣት ስለሚቆጠሩት የፕሬስ ውጤቶች ምን ያህል ቅርበትነት አሎት?
አቶ አወቀ ፡- “በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ከስራዩ ጋር ተዛማጅንት ባላቸው መለኩ ከምርጫ 97 አ.ም በፊት ሆነ በሁዋላ እብዛኞቹን የነጻ ፕሬስ ውጤቶችን እከታተል ነበር፡፡ “
ጥያቄ፡- ታዲያ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተከታታይ ጽሁፎችን የማንበቡ እድል ነበሮት ?
አቶ አወቀ፡-“ምርጫውን ተከትሎ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ታስረው፡ ገሚሶቹ ደርጅቶቻቸው በመንግስት ሃይሎች ከተዘጉባቸው እና ከተሰደዱ በሁዋላ በተለያዩ ድህረ ገጾች እማካኝነት የሚወጡት ጽሁፎችን እከታተላለሁ ፡፡ከእነርሱ መካከል የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተለያዩ ወቅታዊ ጸሁፎችን አነብ ነበር፡፡”
ጥያቄ፡- ታዲያ ለእሰክንድር ጽሁፎች እንግዳ ካልሆኑ እውን ገዤው መንግስት እንደሚለው የእስክንድር ጽሁፎች ይህንን ያህል የመንግስት የስልጣን ህልውናን የሚፈታተኑ : ህዝብ በህዝብ ላይ ወይም ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ ነበሩ?
አቶ አወቀ ፡- “በጭራሽ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ እና የጽሁፎቹን መንፈስ በቅንነት ለተመለከተው ለመንግስት ተብዩው ሆነ ለሰርአቱ አፈቀላጤዎች የማነቃቂያ ደውሎች አና አሰተማሪዎች እንጂ በተቃራኒው ወይም በአፍራሽነት የሚታዩ አልነበሩም ፡፡ጽሁፎቹን ባትወዳቸው እንኳን በሰለጠነው አለም ሁልጊዜ እንደሚደረገው ለጽሁፎቹ ተቃራኒ ወይም የመንግስትን አቋም የሚያንጸባርቁ ምላሾችን መሰጠት ይቻላል፡፡ ለእነደዚህ አይነቱ ምላሾች የመንግስት ሰዎች የሚቦዝኑ አይመሰለኝም ፡፡ ወይም ጽሁፎቹን አንብበህ ታዲያ ምንድነው ይደርግ የሚለው ?( so what?) በማለት ጽሁፉቹን በነጻ አመለካከት ደረጃ ፈርጀህ የመታልፋቸው እንጂ አንደዚህ እስኪ የዋጣልን ምን ታመጣለህ ብለህ ጥርስ የምትነክስባቸው አየመስሉኝም፡፡”
ጥያቄ፡- የእስክንድር ጽሁፎች ሆኑ አሰተያየቶቹ የመንግስትን ህልውና አያናጉም ካሉኝ ገዤው መንግሰት የህንን ሁሉ ወራት እና የህዝብ ገንዘብ እያባከነ ለምን በእነ እሰክንድር ላይ የቅጣት በትሩን ለመሰንዘር የፈለገ ይምሰሎታል?
አቶ አወቀ ፡- “እስከ ዛሬ ድረስ ለፕሬሱ እና ለፍርድ ቤቶች ካለኝ ቀረቤታ አኳያ በህትመት ሆነ በኤሌክትሮኔክስ መልክ የሚሰራጩ የፕሬስ ውጤቶች ህዝቡን ቀስቅሰው በመንግስት ላይ አመጻ ያስነሱበት ወይም ህዝቡ እርስ በርሱ ደም እንዲቃባ ምክንያት የሆኑበት አጋጣሚን አላስታውስም፡፡እነ እስክነድርን በተመለከት በአጠቃላይ የተጠቀሱባቸው የህግ እንቀጾችን ስመለከታቸው ከበድ ያለ የቅጣት ብይን የሚያሰበይኑባቸው በመሆናቸው በተከሳሾቹ ላያ የስነልቦና እና የሞራል ኪሳራ ለመፍጠር፡ተከሳሾቹን ለማሸማቀቅ እና ከዛሬ ነገ ምን እንሆን ይሆን በሚል ስጋት ተጠምደው ሁለተኛ ፊታቸውን ወደ ቆሙለት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና የዲሞክራሲ መብት ተጠቃሚዎች እንዳይሆኑ ለማድርግ የተወጠነ የፓለቲካ እቅድ ይመስለኛል፡፡”
የህሊና እስረኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ፎቶ ፋይል)
ጥያቄ፡-የህዝቡን አመለካከት እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አወቀ ፡- “ሁኔታው በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ የፍርሃት ድባብ ያጠላ የመስላል፡፡ ሁሉም ሰው ምን እየተደረገ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃናት እና ባለሰልጣናቱ ውሸታሞች እንደሆኑ ህዝቡ ያውቃል፡፡እንዴ ፍርድ ቤቱ በተከሳቹ ላይ የፍርድ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት በመንግስት መገናኛ ብዙሃናት አማካኝነት በተከሳሾቹ ላይ የተከፈቱት የተለያዩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ምን አይነት መልእክትን ለማሰተላለፍ እንደተፈለገ እና የፍርድ ቤቱ ውሳኔም ቢሆን ምን እንደሚሆን ቀድሞውንም ማወቅ አይከብድም ፡፡ ሌላው ቀረቶ ምን አልባት አንተም ቢሆን ታዝበህ ከሆነ የአገዛዙ ባለስልጣናት እስከአሁን ድረስ ሊዘጉት ወይም ሊያስተጓጉሉት ያልቻሉት እና በርካታ ወጣቶችን የሚያሳትፈው የወዳጆች መገናኛ ድህረ ገጽ የሆነው ፌስ ቡክ (Face Book) ላይ አገዛዙን የሚተቹ ጽሁፎች ሲወጡ ብዙ ሰዎች ጽሁፉን በተመለከተ የራሳቸው የሆነ የድጋፍ ይሁን የተቃውሞ አሰተያየትን ከመሰጠት ቢቻላቸው ጽሁፉን አንብበው ካጣጣሙ በሁዋላ ዝምታን አሊያም ጽሁፉን ወድጄዋለሁ( I like it ) የምትለውን ሳጥን መንካት ብቻ ይመረጣሉ ፡፡ጽሁፉ ፖለቲካዊ ይዘት ከሌለው ደግሞ የተላያዩ የአሰተያየት አይነቶችን ሲያዥጎደጉዱ ታያለህ ፡፡ይህ ሁሉ እንግዲህ የሚያሳየው ከባድ የፍርሃት ደመና በህዝቡ ላይ ማንጃበቡን እንጂ የፌስ ቡክ አላማን እና ሚናውን ያለማወቅ አይመሰለኝም፡፡ የሚገርምህ ነገር የመንግስት ሰራተኞች ሳይቀሩ ወደ ቢሯቸው ከመግባታቸው ቀድመው አርብ ጠዋት ገበያ ላይ የሚውለውን ፍትህ የተባለውን ነጻ ጋዜጣን ለመግዛት ሲሻሙ ታያለህ ፡፡ ነገር ግን ሁሉም በጽሁፉ ዙሪያ በእረፍት ሰአታቸው ከመወያየት ስሜታቸውን በጉያቸው ውስጥ ደብቀው ከስራ መልስ ወደቤታቸው ሲሄዱ የምታየው ፡፡ “
ጥያቄ፡-ፍርድ ቤቱ በእነ እስክንድር ጉዳይ ላይ ምን ያህል አመት ይፈረድባቸዋል ብለው የገምታሉ?
አቶ አወቀ ፡- ” በእኔ አመለካከት ቁምነገሩ ስንት አመት ይፈርድባቸዋል ወይም ምን ያደረጋቸዋል የሚለው ጉዳይ ሳይሆን ከመጀመሪያው አንስቶ ተከሳሾቹ መከሰሳቸው ተገቢ ነበር? ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ መመለስ ነበረበት ፡፡ይህንን ምላሽ ስናገኝ ፍርዱ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከባድ አይሆንም፡፡”
ጥያቄ፡-በህገ መንገስቱ መሰረት ፍ/ ቤቶች ከፖለቲካ ተጸእኖ ነጻ እንደሆኑ ነው የሚነገረው ፡፡ታዲያ የእነ እስክነድር ነጋን ጉዳይን የተመለከተው ችሎት ነጻ ነበር ማለት አይቻልም?
አቶ አወቀ ፡- “ወዳጄ እንዴት እንደዚያ ብልህ ታስባለህ? “
ጥያቄ፡-እሺ ታዲያ ዳኞቹ የልምድ (የብቃት) ችግር አለባቸው እያሉኝ ነው?
አቶ አወቀ፡-“ችግሩ የልምድ እና የእውቀት ማነስ አይመስለኝም ፡፡ ዋናው ተጠሪነትህ ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄ መምለሱ ላይ ነው፡፡ተጠሪነትህ ለእይምሮህ ነው? ፡ለህጉ? ለገዤው መንግስት? ወይስ ለህገመንግስቱ?… ወዘተ?. ለምሳሌ ለህገመንግስቱ ተገዤ ካልሆንክ በመጀመሪያው ዙር ትመታለህ ወይም ከችሎት ወንበር ላይ አትቀምጠም፡፡ ለምሳሌ ያህል የእነ እሰክንድር ነጋ የክስ ፋይልን ከሚመለከቱት ከሶስቱ ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ዳኛ ሁሴን ይመር የእውቀት ችግር ያለበት ሰው እንዳልሆነ
ልመሰክርለት አችላላሁ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ዳኛ ሁሴን ወደ ችሎት ከመገባቱ በፊት እነ ዳኛ መንበረጸሃይ ታደስ ከአለም ባንክ(World Bank ) እና ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋምInternational Monetary Fund ) በተገኘው ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ ባቋቋሙት “የኢትዮጵያ ዳኞች እና አቃቢያን ህግ ማሰልጠኛ” ተብሎ ከሚጠራው ማእከል ውስጥ በመግባት ሁሉም ዳኞች በእውቀታቸው ሳይሆን ለአገዛዙ ታማኝነታቸውን በተመለከተ ተገምግመው የሚያልፉበት ስርአት በመፈጠሩ አነዚያ ሰልጣኝ የህግ ባለሙያዎች ወደ ተለያዩ ችሎቶች ሲመደቡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከፖለቲካ ርእዮት አለም ያለተናነስ ትምህርት ሰለሚሰጣቸው በችሎት ወንበር ላይ ሲቀመጡ ወደዱም ጠሉ ይህን መሰሉ ተጽእኖ አለባቸው ፡፡ እንግዲህ እንዚሁ ዳኞች ቢቻላቸው ለፓርቲው ታማኝ መሆን ካልሆነ ግን ስራቸውን ለቅቀው መውጣት አለባቸው ፡፡ ዳኛ ሁሴንም ቢሆን ይህንን የተቋሙን የአመለካከት ማጣሪያ ካለፉ ዳኞች መካከል አንዱ ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ከህገ መንግስቱ አነቀጾች ጋር በፈጹም የሚጻረረ አካሄድ ነው ፡፡ቀደም ሲል በነበረው የፍርድ ቤቶች አሰራር ተከሳሾች በየትኛው ዳኛ መዳኘት እንዳለባቸው (በተለይ የፖለቲካ ነክ ተከሳሾች) በየትኛው ዳኛ እና ችሎት መዳኘት እንዳለባቸው በመዝገብ ቤት በኩል እንደ ግዳዩ ክብደት እና ፖለቲካዊ ይዘት ተጣርቶ ነበር የሚመደበው ፡፡ለምሳሌ ያህል ጉዳዩ ጠጣር ከሆነ በእነ ዳኛ መድህን ኬሮስ ችሎት እንደሚሆን ብዙ ሰው ቀደሞ ይገምታል፡፡ግምቱም በአብዛኛው ትክክል ነበር ፡፡በሁዋላ ግን ከላይ የገለጽኩልህ ተቋም ከተከፈተ በሁዋላ ፍርድ ቤትች በሙሉ አንድ ወጥ አሰራር እንዲሰሩ በመደረጉ ( ሁሉም ለገዤው መንግስት ያደሩ በመሆናቸው) መዝገብ ቤቶች ፋይሎችን በማገላበጥ መምደቡን ትተውታል፡፡ ዳኝነት የህሊና ፍርድ መሆኑ እየታወቀ አንዳንድ ጊዜ ዳኞች እንኳን ውስኔ ከማስተላለፋቸው በፊት “መንግስት በውሳኔው ያኮርፍብን ይሆን?” የሚል ስጋት እንዳለባቸው ታዋቂው ደምጻዊ ቴዲ አፍሮ(ቴድሮስ ካሳሁን) “በሰው መግደል” ክስ ቀርቦበት ቸሎቱ ተከሳሹን ጠፋተኛ አድርጎ ከምበየኑ በፊት ዳኞቹ የመንግስትን ( የመነግስት የኮሜኒኬሽን ምክትል ሹም የሆኑት የእነ አቶ ሸመልስ ከማልን አስተያየት) የጠየቀበት ሁኔታን ስትመለከትው ፍርድ ቤቶች ምን ያህል ለስርአቱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በቀላሉ ትረዳዋለህ፡፡”
ጥያቄ፡- አሁን ታዲያ ዳኞች በጭራሽ ለህሊናቸው ሲሉ አይፈርዱም እያሉኝ ነው ያሉት?
አቶ አወቀ፡-“ምንም ጥርጥር የለውም ፡፡አንድ ማስረጃ ልጨምርልህ ፡፡ ከሰባት ወራት በፊት ፍርድ ቤቶች ተዘግተው በአዲስ አበባው የጊዮን ሆቴል ውስጥ በእነ አቶ (ጓድ) ሽመልስ ከማል አዘጋጅነት ለሶስት ሳምንታት የዘልቀ በጸረ አሸባሪነት ህጉ እና በፕሬስ አዋጁ ዙሪያ የሙያ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚል ፕሮግራም ተሰጥቶ ነበር ፡፡”
ጥያቄ፡ ታዲያ መንፈሱ “የግንዛቤ ማስጨበጫ” ከሆነ ስህተቱ እምኑ ላይ ነው?
አቶ አወቀ፡-“ችግሩ ሴሚናር መስጠቱ ላይ ሳይሆን ስሚናሩን የሚሰጡት እነማን ናቸው? ተጠሪነታቸውስ ለማን ነው? ከሚለው የህግ ጥያቄ ላይ ማየት ይቻላል፡፡ እነ አቶ ሸመልስ እኮ የፖለቲካ ሹመኞች እና ለአገዛዙ እድሜ መራዘም ቀን ተለሊት የሜሯሯጡ ሰዎች ናቸው ፡፡ እዚህ ላይ አንሱ ለዳኞቹ ይህንን መሰሉን ስልጠና ሲሰጡ “ከዚህ በሁዋላ የምትሰሩት በዚህ መልኩ ነው” ማለታቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ህጉን የመተርጎም ሙሉ ስልጣን የፍርድ ቤቶች መሆኑ እየታወቀ የመንግስት ባለስልጣናት እና አፈቀልጤዎች ዳኞቹን በስበብ አስባቡ ሰብስበው “የእኛ መንፈስ ይህ በመሆኑ እናንተም ወደ ችሎት ስትመለሱ እንዲህ ብላችሁ ተርጉሙልን…ወዘተ” በማለት በፍትህ ስርእቱ ላይ ምን አይነት ጫና እና ግፍ እየፈጸሙ መሆናቸውን ጥንቅቀን ማወቅ ያለብን የመስለኛል፡፡በአጭሩ እነዚህ ዳኞች ከአዳራሹ ሲወጡ እንደ ኮምፒውተር ወይም ሮቦት ሶፍት ዌር (Soft ware programmed) ሆነው ነው የሚወጡት ፡፡ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በፍትህ ስርአቱ ላይ እሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው በእለት ተእለት ውሳኔዎች ላይ ማየት ይቻላል፡፡”
ጥያቄ ፡- አብዛኞቹ ፍርድ ቤቶች በአሁኑ ወቅት የክስ ፋይሎችን በፍጥነት ውሳኔ እንደሚሰጡ በስፋት ይነገራል….
አቶ አወቀ ፡- “እዚህ ላይ ሰለ የትኞቹ ጉዳዮች እንደምናውራ ጥንቅቀን ማወቅ አለብን ፡፡የፍታብሄር ጉዳይ ነው? ወይስ የደረቅ ወንጀል? የእጅ ከፈንጅ? አሊያም የፖለቲካ…? ወዘተ ጉዳይ እያልን መከፋፈል እንችላለን ፡፡ ፍጥነት ስንል ደግሞ ውጤቱ እምኑ ላይ ነው? የሚለውን ማየት አለብን (speeds at the expense of quality)፡፡ በአንድ ወቅት ከእንግሊዝ አገር የህግ ባለሙያዎች በፍርድ ሂደት(Arbitration) ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ስብሰባውን ይመሩት የነበሩት ፕ/ቱ አቶ ውብሸት ሺፈራው ነበሩ ፡፡ ነጮቹም “ፋይሎችን በስንት ጊዜያት እንደሚጠናቀቁ” ለአቶ ውብሸት ጥያቄ ቢጤ ወረወሩላቸው፡፡ ዳኛ አቶ ውብሸትም “በስድስት ወራት ውስጥ እናጠናቅቃለን” አሉ ፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የነበሩት ተሳታፊዎች በሙሉ ሳቅ በሳቅ ሆኑ፡፡ ፈረንጆቹም የአቶ ውብሸት ምላሽን ተከትሎ በታሳታፊዎቹ ላይ ይነበብ የነበረው ከቁጥጥር ውጭ የሆነው ሳቅ ምስጢር ገብቷቸው አነርሱም በመገረም ተሳሳቁ ፡፡ ነጮቹ የመልሶቹ ይዘት ሰለገባችው ከዚያ በሁዋላ ጥያቄ አላነሱም ፡፡”
ጥያቄ ፡- አነ እስክንድር ነጋ “ጠፋተኛ ናችሁ” ከተባሉ በሁዋላ ውሳኔውን በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ካለ ብሎ ችሎቱ መጠየቅ ሲገባው ችሎቱ ለእነሩሱ (ለተከሳሾቹ ) ይህንን መብታቸውን መንፈጉን ከህግ አኳያ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አወቀ ፡-“የፍ/ ቤቱን ምስል ከላይ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር እኮ ፡፡በአገሪቱ ከ1960ዎቹ እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲስራበት የነበረው እና አለማቀፋዊ ይዘት ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 148 እና 149 በአጭሩ ብገልጽልህ አቃቤ ህግ ሆነ ተከሳሾች ወይም የተከሳቹ ጠበቆች ውሳኔውን በተመለከት አስተያየት የመስጠት እኩል መብት እንዳላቸው፡በተለይ ተከሳሾች ከሁለት በላይ ከሆኑ ሰብሳቢው ዳኛ ማንኛው ተከሳሽ ቀደሞ መናገር እንዳለበት በመምረጥ የመጨረሻውን አስተያየት ተከሳሹ ወይም ጠበቃው እንደሚያደረጉ በህጉ ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጦ ሳለ አቃቤ ህግ ይህንን መብት ተሰጥቶት አነ እሰክንድር ነጋ በስተመጨረሻ የህጉ ሰለባ እና ተጠቂዎች እንደሚሆኑ እየታወቀ፡ፍርድ ቤቱ “ጥፋተኛ ናቸው” ባላቸው የክስ ፋይል ከትንሹ ቅጣት አንስቶ እስከ ከፍተኛው የፍርድ ጣሪያ ሊፍረድባቸው አንደሚችል አየታወቀ “አሰተያየት አተሰጡም” ማለቱ ፊውዳል እና በዝባዥ በተባለው በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን ንጉሱን ሊገለብጡ ከወንድማቸው ከግርማሜ ጋር በ1953 አ/ም “አሲረዋል” ተብለው የስቅላት ቅጣት የተበየነባቸው መንግስቱ ነዋይ እንኳን በስተመጨረሻ አስተያየታቸውን እንዳይሰጡ አልተክለክሉም፡፡ በቅርቡም ቢሆን ጨካኝ እና ሰው በላ የተባለው የደርግም መንግስት ቢሆን “ስልጣኑን የተቀናቀኑትን” ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናቱን በግንቦት 1980 አ/ም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሳቢያ ወታደራዊ ችሎት የሞት ቅጣት ሲያስተላልፍባቸው (ውሳኔው እና እርምጃው ትክክል ይሁን እይሁን) ተከሳሾቹ ህጉ በሰጣቸው መብት ላይ ከመናገር አልነፈጋቸውም ነበር ፡፡ታዲያ ዛሬ ህጉን እንተረጉማለን የሚሉ ወገኖች( ዳኞች ) መጽሃፉ ላይ ያለውን የህግ አንቀጽ እንኳን እንብበው ለመፍረድ ሲሳናቸው ስታይ የዚህች ያልታደለች አገር የፍትህ ስርአት ወዴት እያመራ እንደሆነ መገመት አያዳግትም ፡፡”
ጥያቄ፡-እርሶ ታዲያ አሁን ካለው ሁኔታ ሆነ ቀደም ሲል ከተፈጸሙት የህግ ጥሰቶች በመነሳት ከህግ ጋር ተዛማጅነት ያለውን ሙያዎትን እጣፈንታ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አወቀ፡-“በአገሪቱ ውስጥ ሆነ በውጭ አገር በሚገኙ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በህግ ሙያ ተመርቀህ አገሬን እና ህዝቤን በሙያዩ አገለግላለው ፡ ቤተሰቤንም በነጻነት አስተዳድራለሁ ማለቱ ዘበት እንደሆነ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ እኔም ብሆን በህግ ትምህርት ላይ ያሳለፍኩት እድሜዩን ወደ ሁዋላ መለስ ብዮ ስመለከተው የባከነ የህይወት ዘመን ሆኖ ይታየኛል ፡፡ ልጆቼን እና ወዳጆቼንም ቢሆን በህግ ነክ ጉዳዩች ዙሩያ ለመማር ከፈለጉ በመጀመሪያ ደረጃ ለግላቸው እውቀት ማጎልበት ካልሆነ በቀር በሙያው ዘርፍ ያለማንም አካል ጣልቃ ገበነት እና አስገዳጅነት (በነጻነት) ለመስራት የሚለውን ሙያዊ ምክር አልሰጣቸውም፡፡ ” ጥያቄ፡- ሰለ ሰጡኝ ሰፊ ምሁራዊ እና ሙያዊ አስተያየት ከልብ አመሰግንለሁ ፡፡
አቶ አወቀ ፡- “እኔም እድሉን ሰለትሰጠኝ አመሰግናለሁ ፡፡ “
ለተጨማሪ ጥያቄዎች እና መረጃዎች ጽሃፊውን በtamgeda@gmail.com ያገኛሉ
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close