የሕዝብ ፍቅር በዳላስ ሲያሸንፍ!

የሕዝብ ፍቅር በዳላስ ሲያሸንፍ!

                                                                                                                             ግርማ ደገፋ ገዳ (ዳላስ)│girmariver@gmail.com│

29ኛው የኢትዮጵያውያን ዓመታዊው የስፖርትና የባሕል ዝግጅት በዳላስ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሮ በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። የዓመቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሽፈራው በተገኙበት ዓመታዊ ዝግጅቱን የከፈቱት፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፓርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ናቸው። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔም ተገኝተዋል። በመክፈቻው ላይ፣ የዳላስ መረዳጃ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ብርሃኑ፣ የዳላስ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ለዝግጅቱ ስኬት ያደረገውን እገዛ በማውሳት አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል። የኢትዮጵያ ቀን በተከበረበት እለትም ታዋቂዎቹ ድምጻውያን መሃሙድ አህሙድና ጸሓዬ ዮሃንስ፣ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ፣ ስሜት ቀስቃሽና አስደሳች ልዩ ልዩ ዘፈኖችን ለታዳሚው አቅርበዋል። በዚህ ዓመታዊ ዝግጅት ላይ በርካታ ቡድኖች የእግር ኳስ ግጥሚያ ያደረጉ ሲሆን አሸናፊውም የሜሪላንድ ቡድን ሆኖ በአልፍሬድ ጄ. ሉስ ስታዲዮም ሲካሄድ የነበረው ዝግጅት ከዋንጫ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ተጠናቋል።

የአንድ ባለሀብት መጫወቻ ላለመሆን ቁርጠኝነቱን ባሳየው  አመራር አባላት የሚመራው የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን፣ (Ethiopian Sports Federation in North America) ከምስረታው ጀምሮ የተሳካም ይሁን ያልተሳካ የረጅም ዓመታት ጉዞን የተጓዘው በኢትዮጵያውን ተሳትፎ እንጂ በባለሃብቶች የገንዘብ ቁልል ምክንያት አለመሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጽ እንደነበር ይታወሳል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ደግሞ፣ ከውስጥ ሆነው ለግል ቁሳዊና ፖለቲካዊ  ጥቅማቸው ብለው ማኅበሩን ወዲያና ወዲህ እየወዘወዙ መላቅጡን ሲያሳዩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች፣ ጊዜው ደረሶ ከፌዴረሽኑ መገለላቸው ብቻ ሳይሆን በነሱ ምክንያት ሊያጣ የነበረውን ፌዴሬሽናዊ ነጻነቱን ተከላክሎ ድል በተቀዳጀ ማግሥት 29ኛውን ዓመታዊ ውድድር ለመደገስ  መቻሉ ነው።

የተገለሉት ያቋቋሙት All Ethiopian Sports Association-ZERO ተብሎ የሚጠራው ተለጣፊው ማኅበር፣ አስቀድሞ እንደተመኘው መጥፎ ምኞት ሳይሆን፣ በዳላስ የመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን በመገኘታቸው መክፈቻው ልዩና ድንቅ ሆኖ አልፏል። በተለይ ደግሞ የዲሲው ‘ኢትዮ-ስታር’ ቡድን አባላት፤

“ዲሲ ምን አለ? ዲሲ ምን አለ?

ፌዴሬሽኑን አንሰጥም አለ!” በሚል አስደሳች ዜማ ለፌዴሬሽኑ ሕልውና ያደረጉትን ትግል አንጸባርቀዋል። ተመልካቹም አድናቆቱን በጭብጨባና በጩኸት ገልጾላቸዋል።

ይህ ዝግጅት ብዙ አድናቂዎችን ከብዙ አቅጣጫ እያጎረፈ የሚያገናኝ መድረክ እንደመሆኑ መጠን፣ እድምተኞች፤ በጣም ጠበቅ ያለ የናፍቆት ሰላምታ ሲለዋወጡ ማየት የተለመደ ነው። እኔም አንድ ጓደኛዬን አገኘሁት። ዲሲ ላይ በሚካሄደው ድግስ ላይ ይሳተፋል ሲባል ነበር የሰማሁት። ግን ለምን መጣ?

“የዲሲን ድግስ ለማን አደራ ሰጠህ?” አልኩት።

“ሺት! ገንዘቡን ነው የፈለኩት!”

“ለምን?”

“ዳላስ ልመጣበት ነዋ!”

“አራዳ ሆንክ ማለት ነው?”

“ትቀልዳለህ? ካዲላክ ነው የተከራየሁበት። ውድ፣ ውድ ጋዞሊን እየቀዳሁበት!”

“እነእከሌስ?” አልኩት። የነሱንም ጉድ ሰምቼ ነበር።

“ድርሻቸውን ነክሰዋል። ይመጣሉ….” እንዳለኝ ስልኩ አቃጨለና “ሃሎ!” ማለት ጀመረ። “የት ደረሳችሁ? …..አትለኝም!” አለና ወደ እኔ ዞር ብሎ “ዋ! የሚገርም ነው! አላልኩህም! ….ኦክላሆማ ደርሰዋል። ይሄን በግላጭ የተገኘ የሼሁን ገንዘብ እንጨረግደዋለን!” ካለኝ በኋላ፣ ወደ ምግብ አስተናጋጇ ዞር ብሎ፣ “ለጋሽ ግርማና ልጆቹ 3 ኃይለኛ የዳላስ ጥብስ!” አላት።

ሳቄ መጣ።

“በየትኛው ገንዘብ ልትጋብዘን ነው?”

“ምን አዲስ ትሆናለህ? በዚህ ወቅት አሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለት ዓይነት ገንዘብ ነው ያለው። የአሜሪካ ዶላርና እነአቶ ሰብስቤ የሚጫወቱበት የሼሁ ዶላር! የፈለከውን ምረጥ” አለኝና ዞር ሲል ‘ቾምቤ’ የሚባል ጓደኛውን አየው። በፍጹም ማመን አልቻለም።

“እንዴ! ቾምቤ! አንተም ዳላስ መጣህ?”

“አዎ! ከመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ወደዚህ ከነፍኩኝ። ተመልከት! የገዙልንን ማሊያ እንኳ አላወልኩም” አለው በማሊያው ላይ የደረበውን ስስ ከነቴራ በአንገቱ በኩል እየሳበ። “ሸወድናቸው!”

“ምን ነካህ? ነውርም አይደል እንዴ!”

“ጥቁር ካባ ለብሶ ስቴዲየም የሚያክል መቃብር ውስጥ የሚንጎራደድ በቁሙ የሞተ ሬሳ የሆንኩኝ መሰለኝ” አለው።

“ገለልተኛው ጋሽ አብነት ኮረንቲ ጨበጠ በለኛ!”

“የግልገል ጊቤን?”

“የሕዳሴውንም ጨምሮ” ካለው በኋላ “መቼም ጓደኛዬ ነህ። አንድ ነገር ብልህ አትቀየመኝም!”

“ለምን እቀየምሃለሁ? ለማ ተብሎ?”

“እንግዲያውስ የለበስከው ማሊያ ደም ደም ይሸታል! አንተን አይሸትህም?”

አወለቀውና “በስመአብ” እያለ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጨመረውና  “አሁንስ?” አለ ቾምቤ።

“አሁን’ማ ሕዝብ ሕዝብ! …..ግን እንደዚያ አይደለም ይህንን የጋሽ አብነትን ማሊያ የምንቀብረው። አቀባበሩን ማሳመር አለብን። …..አውጣው!”

ቾምቤ የተባለውን አደረገ። እኔም ‘ምን ጉድ ሊከተል ነው?’ ብዬ በጉጉት ጠበኩኝ።

ስልክ ደወለና በዛ ያሉ ወጣቶች ያሉበትን ቡድን አስመጣና “ሰብስቤን ያያችሁ? ማለት ጀመሩ።

“ሰብስቤን ያያችሁ?

ገደል ገባላችሁ!

እያያን ያላችሁ

የት ሊያደርሳችሁ?

ጋሽ አብነት

ሆ!

ጋሽ አብነት

ሆ!

ማሊያዎ

ትራሽ ሆኖልዎ!” የሚል ቆንጆ ዘፈን እየዘፈኑ፣ ከዲሲ ለመከራ የመጣውን የነአቶ አብነት ማሊያን እንደ መርዛማ እባብ “አትንካው በእጅህ!” እየተባባሉ በእንጨት አንስተው መከራውን አሳዩት። ከዚያም ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ቀበሩት። “ለሚቀጥለው ዓመት እንዳይነሳ!” እያሉም ጠቀጠቁት። የማሊያው ሕይወት በዚያ መልኩ ተጠናቀቀ። ምስኪን ማሊያ!

*****

…..የኢትዮጵያን አብዛኛዎቹን ስመጥር እግር ኳስ ተጫዎቾችንና ቡድኖችን ለማወቅ እድል የሚሰጥ ከተማ ነው ያደኩት። መንግሥቱ ወርቁ የብሔራዊ ቡድናችን አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት፣ ቡድኑ የሚሰለጥነው አዳማ ራስ ሆቴል ተቀምጦ ወንጂ ነበር። ተጨዋቾቹ ሲለማመዱ በቅርብ ርቀት ላይ ሆነን ማየት ብቻ ሳይሆን፣ የመጨባበጥና ለደቂቃም ቢሆን የመነጋገር እድል ነበረን። ቱታቸውን፣ ቁምጣቸውን፣ ማሊያቸውንና ታኬታቸውን ማየቱ ይማርከናል። የአዳዲስ ኳስ ብዛቱ ያሳብደናል። መንግሥቱ ወርቁ፤ ሲጮሁ፣ ሲናደዱ፣ ሲደሰቱና ሲስቁ እናያለን። በረኞቹ ላይ ትኩረት ሰጥተው፣ በኃይለኛ ምቶች ሲያስቀጠቅጧቸውና ሰማይ እያስደረሱ መሬት ላይ ሲያስከሰክሷቸው!’ እንላለን። ክረምት ላይ ከአንደኛ ዲቪዚዮን እስከ ታች ድረስ ያሉት ቡድኖች አዲስ አበባን ለቀው፣ በየሳምንቱ እሁድ ለግጥሚያ ወንጂ ስለሚመጡ፤ ከነአሰልጣኞቻቸው፣ ወጌሻቸውና አውቶቢሳቸው ጭምር ነበር የምናውቃቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ከክፍለ ሀገር ለብሔራዊ ቡድን የሚመረጡት ካልሆኑ በቀር፣ ብዙዎቹን ለክለባቸው ሲጫወቱ የማየቱ እድል ስለነበረን፤ የብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ሆነው ሲመጡ አዲሳችን አይሆኑም።

በየተወሰኑ ጊዜያቶች፣ የምድር ጦር ቡድን ጓዙን ጠቅልሎ፣ ለሁለት ወይም ለሶስት ወራት ወንጂ ከሚገኙት የድሮ የሆላንድ ቪላ ቤቶች አንዱ ይለቀቅለትና እዚያ ይከርማል። ራሺያዊ አሰልጣኙን፣ የቀላልና ከባድ ሚዛን ቦክሰኞቹን፣እናቡድኖቹን አስከትሎ፤ ይቆያል። ክብደት ማንሳት፣ አሎሎ መወርወር፣ የላውንደሪ ላስቲክ ለብሶ መሮጥ፣ መቧቀስ፣ የእንቁላል መዓት፣ የሚታረዱ ፍየሎች ጋጋታ፣ ዋዝ ጂፕና የማናውቀውን ወታደራዊ ማእረግ ሲጠራሩበት እየሰማን እንከርማለን።

ትምህርት ቤት ስንሄድ ሊፍት ይሰጡናል። በምንም ሁኔታ በእግራችን ስንሄድ እያዩ ጥለውን አይሄዱም። አረንጓዴ ማርቸዲስ አውቶቢስ ነበራቸው። ጎማው ላይ ቆመን በመስኮት ሁሉ እየገባን አውቶቡሱን ስናጨናንቀው አይከፉም። ማክ መኪና ደግሞ ነበራቸው። እሱ ላይም እንደፈለግን ተገለባብጠን ነበር የምንወጣው። ስንገለባበጥ፣ ወይ ሙላለም እጅጉ ላይ፣ ወይም አየለ ኡርጌ ላይ፣ ወይም አስፋው ባዩ ላይ፣ ወይም አንዳቸው ላይ እንወድቃለን።  እንደ ሕጻን ልጅ ታቅፈውንወደ መሬት ልጣልህ?” እያሉ ይቀልዱብናል። በምንም ተአምርካንጋሮተብሎ የሚጠራው ረጅሙና በጣም ደጉ ዋናው የምድር ጦር በረኛ ላይ፤ አንወድቅም። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ማኩን የሚነዳው እሱ ነበር። ካንጋሮ ዋና ስሙ ወንድሙ ሲሆን፣ የሁሉም ታዳጊ ወጣት ጓደኛ ነበር። ነፍሱን ይማረው! (አስፋው ባዩንም)

የአስቴር አወቀን ዘፈን የሚወዱ ብዙ ነበሩ። መስኮታቸው ላይ ተንጠልጥለን አብረን እንሰማለን። ዓሳ ለማጥመድ ከራሺያዊው አሰልጣኝ ጋር አብረን እንሄዳለን። የቆይታቸውን ጊዜ ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ እንዲሁ ዝም ብለውን አይሄዱም። ዋናው ብሔራዊ ቡድን እንደሚያደርገው ሁሉ፤ ምድር ጦርም ከወንጂ ዋናው ቡድን ጋር የመሰነባበቻ ግጥሚያ ያደርጋል። ያን እለት የእግር ኳስ አፍቃሪው በሙሉ ተገልብጦ ወጥቶ ጨዋታውን ይመለከታል። ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱባት የመጨረሻዋ ቀን ስለምትታወቅ፣ ለስንብት እንሄዳለን። አሮጌ ኳሶቻቸውን፣ ታኬታቸውንና ማሊያቸውን ወንጂ ውስጥ ለሚገኙ የታዳጊ ወጣት ቡድኖች ሰጥተው ይሄዳሉ። እንደገና የሚመጡ ስለማይመስለን በጣም እያዘንን እንለያለን። የሚያለቅሱም ነበሩ። ዳግም የሚመለሱበት ወቅት እየራቀብን፣ ቡድኑን እየናፈቅን እንቆያለን። የወንጂ እግር ኳስ አፍቃሪ፣ ከሀገር ውስጥ ምድር ጦርን ከውጪ ደግሞ የሆላንድን ቡድን የሚደግፈው ያለምክንያት አልነበረም። …..

*****

በእንደዚያ ዓይነት አጋጣሚ ከምናውቃቸው ተጫዋቾች መካከል፣ የዛሬው የAesa-ZERO መሥራች ከሆኑት አንዱ የሆነው አቶ ሰብስቤ ይገኝበታል። ድሮ ብርሃንና ሰላም የሚባል ቡድን ነበር። ለዚያ ነበር የሚጫወተው። ብርሃንና ሰላም ያን ያህል ታዋቂ ቡድን አልነበረም። ግን ሰብስቤ ኃይለኛ ተጫዋች ነበር። ‘ቡድኑ ያለ’ሱ ሕይወት የለውም’ እያሉ የሰፈራችን ትላልቅ ልጆች ሲያወሩ እንሰማ ነበር። ሰብስቤ ከሀገር መጥፋቱን የሰማነውም በእነዚያ የሰፈራችን ትላልቅ ልጆች ግን በኛ ትናንሽ ጆሮዎች ነበር። ከዚያ በኋላ ስለሰብስቤ ተባራሪ ወሬ ብቻ ነበር የሚደርሰን። ‘በውጭ ሀገር ኮኮብ ተጫዋች ተብሎ ተሸለመ! ኢትዮጵያዊው ፔሌ ተባለ!’ ሲባል፣ ልጆች ስለነበርን ብቻ ሳይሆን በጉብዝናው የተነሳ የሰፈራችን ትላልቅ ልጆች የሚወዱት ተጫዋች ስለነበር፤ ከነሱ የምንሰማውን እያጋነንን ከማውራት በቀር ወሬው እውነት ይሁን ውሸት ግድ አልነበረንም። ‘ለየትኛው ቡድን የት ሀገር ተጫውቶ ኮከብ ወይም ጨረቃ ተባለ?’ ማን ስለዚያ ያብሰለስላል! የተሰደደባት አሜሪካ በእግር ኳስ ትታወቅ አትታወቅ አናውቅም፤  “አይገርምም!? ሰብስቤ ፔሌን ሊተካ ነው!” እያልን ጨርቅ ኳሳችንን በትናንሽ እግሮቻችን ወደ ሰማይ ከመጠለዝ በቀር።

እኔም ተራዬ ደርሶ ፈረንጅ ሀገር መጣሁና በስንተኛው ዓመት ላይ እንደሆነ በማላስታውሰው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፓርት ፌዴሬሽን ዝግጅት ወቅት፣ ስማቸው በጥሩ ሁኔታ ከማይጠቀሱት አንዱ አቶ ሰብስቤ መሆኑን ሰማሁ። ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነብኝ። እዚያም እዚህም የሱን ስም እያነሱ የትም ሲለጥፉት በጣም አዘንኩኝ። አንድ፣ ቨርጂኒያ ውስጥ ኳስ የሚጫወት ሰው፣ “ብረትምጣድ ላይ የተሰጣ የመንደር አሻሮ እየዘገነ ያደገ ነው! ከሱ ምን ይጠበቃል?!” ብሎ ተማሮ ሲያወራ፣ በአባባሉ ደስ ባይለኝም በተደረገው ድርጊት ማዘኔ አልቀረም። ምክንያቱም፣ እነዚህ የወንጂ እግር ኳስ አፍቃሪ ድሮ በወጣትነታቸው የሚያውቋቸውና በኳስ አጨዋወት ስልታቸው የሚያደንቋቸው ሰፖርተኞች፣ ዛሬ ትላልቅ ሰዎች ናቸው። ልጆች ወልደው ጎረምሳ አድርገዋል። ‘አንተ’ ሳይሆን ‘አንቱ’ የሚባሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ግን ለምን የኢትዮጵያውያንን ድርጅት ማጅራት አንቀው አሳፋሪ ድርጊት እንደሚሰሩ አይገባኝም።

“እኛ ለምነን ያመጣነው ገንዘብ ነው። ምንስ ብናደርገው ሌላው ኢትዮጵያዊ ምን ያገባዋል!? ይላሉ” ነበር የሚባለው። እንዴ! ታዲያ የአመራር አባል ሲኮን’ኮ ለቅንጦት ወይም የኢትዮጵያውያንን ማጅራት ዓለም ለሚያውቃቸው ባለሀብቶች እያስያዙ በስሙ የሚመጣውን ገንዘብ ለመጨርገድ አይደለም። ኢትዮጵያውያንን ለመንግሥት ፖለቲካ አሳልፎ በመስጠት መጫወቻ ማድረግ አግባብ መች ሆነ። የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን የተቋቋመው፤ ከውድድሩ በፊት፣ መሃልና በኋላ ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ድርሻ ለመውሰድ መች ሆነ? ‘ድርጅቱ፣ ፖለቲካን ከሚያራምዱ ተቋማት ሥውር እጆች መጽዳት አለበት!’ ሲባል፣ ከኢሕአዴግም ጭምር ነው። ኢሕአዴግ በባለሀብቶች፣ ባለሀብቶች በነአቶ ሰብስቤ በኩል ማኅበሩን እንደፈለጉ የሚጫወቱበት ቶይ  ሲያደርጉት እንዴት አርፎ መቀመጥ ይቻላል? ለነአቶ ሰብስቤ ቡድኖች፣ ESFNA ባንክ ሊሆን ይችላል። የሕዝቡ ደረት ላይ የለጠፋት የማይታይ ኤቲኤም ቢኖርስ? ለፍቶ ያገኘውን ገንዘብና በመከራ የተፈቀደለትን የእረፍት ጊዜ፣ ዴቢትና ክሬዲት ካርዳቸው አድርገው ቆጥረውትስ እንደሆን ማን ያውቃል? በውጭ ለሚኖረው ሕዝብ ግን ESFNA የስፖርትና የባሕል መድረክ ነው። የመተዋወቂያና የመጠያየቂያ ማማ ነው። የሀገር ናፍቆትና የልጅነት ትዝታ ማጽናኛ ነው። መተላለፊያ ድልድይ ነው። ድሮ ይሄንን ማኅበር እነሰብስቤ የመሰረቱት ለዚያ ዓላማ ነው። ሕዝቡም ዓመቱን እየጠበቀና ስንትና ስንት ኪሎሜትሮች አቋርጦ በበጎ ፈቃደኝነት ከተፍ የሚለው ለፍቅር ብሎ ነው። የዜጎችን የዋህነት እንደ ሞኝነት ቆጥረው፣ በዜጎች ነፍስ በሚጫወቱ ስግብግቦች ለመገሽለጥና፤ የጨቋኞችን ፖለቲካ ባናት ባናቱ ለመጨለጥ አይደለም።

ከዳላሱ ውድድር ፍጻሜ በኋላ “ይህ የሕዝብ ስፖርት ፌዴሬሽን እነዚህን ከመሰሉ ጥቂት ሰዎች መጽዳቱ ትልቅ ድል ነው። ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ይደጋገሙ የነበሩ ችግሮች ተነቅለው ወጥተዋል። ዋናው ችግሩ፣ ዛሬ ‘All Ethiopian Sports Association-ZERO’ የሚባል ፎቶኮፒ ድርጅት ያቋቋሙ ግለሰቦች እንጂ፣ ተሳታፊው ወይም ፍቅር-ወዳዱ አመራር እንዳልሆነ 29ኛው ዓመታዊ ውድድር ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል” የሚባል ሪፖርት የምናነብበት ወይም የምንሰማበት ሁኔታ ያለ ይመስላል።

ሰብሰብ ብለው የሚሳሳቁ ወጣቶች’ጋ ጠጋ አልኩኝ። በጣም አሪፎች ናቸው።

“አቶ አብነት የተባሉ የድሮ ጥሩ ስፖርተኛ ያሉትን ሰምተሃል?” ጠየቀ አንዱ። ጸጉሩን ተሰርቶታል። ጥቁር መነጽር አድርጓል። በአንገቱ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሸብ አድርጓል። በቀኝ እጁ ላፕቶፕ በሌላኛው እጁ አይፎን ይዟል። የጥርስ መጎርጎሪያ ነክሷል። ወገቡ ላይ ካሜራ ታጥቋል። ሰውነቱ ሁሉ ቢዚ ሆኗል።

“የዛሬው የፖለቲካ-ስፖርተኛ ምን አሉ? መናገር ይችላሉ እንዴ?!” ጓጓ ሌላው ወጣት።

“አዲስ በተቋቋመውና All Ethiopian Sports Association-ZERO ተብሎ በተሰየመው ማኅበር የቦርድ ስብሰባ ላይ እንዲህ አሉ” ብሎ ላፕቶፑን ከፈተ። የሆነ ዌብሳይት ላይ ገባና አቶ አብነትን ከላፕቶፑ እያሳየ የሚናገሩትን ያሰማቸው ጀመር።

“……በጥቂት ሰዎች ምንመራ ከሆነ ራሳችን የት እንዳለን ቆም ብለን ማሰብ መቻል አለብን። ሁላችንም ለቤታችን ትልልቅ ሰዎች ነን። ስለዚህ ማንም ሊመራን፣ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ወደ ስህተት ውስጥ ሲመራን …..እንደው ዝም ብለን ….እንደ ቦይ ውኃ ዝም ብለን የምንሄድ ከሆነ፣ ራሳችንን ቆመን መፈተሽ አለብን…..” ሲሉ ሰማዋቸሁ። ነባሩ የስፖርት ፌዴሬሽን የወሰደው አቋም እሳቸው ከሚሉት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ስለመሆኑ በዚያ የቦርድ ስብሰባ ላይ ሳያውቁት ተናግረዋል። ወይም አፈንግጠው የወጡት የAesa-ZERO አመራር አባላት፣ የራሳቸው የሆነ ትክክለኛ አቋም መያዝ እንጂ በባለሀብቶች ወይም በፖለቲከኞች መመራት እንደሌለባቸው መክረዋል። ምክራቸው ደግ!

ይሁንና የሳቸው ንግግር መልእክት ‘ለሚቀጥለው ሶስት ዓመት ለምታካሂዱት ዝግጅት ሙሉ ወጪውን ስለምንችል ከኢሕአዴግ ውጭ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት በመሃላችሁ አይግባ! በራችሁን ወጥራችሁ ያዙት! መስኮታችሁንም አደራ! እኛ ብቻ ካልሆንን ሌላው ሲመራችሁ እንደ ቦይ ውኃ ዝም ብላችሁ አትሂዱ! ወግድልኝ! በሉ። ጎርፍ ሁኑበት! አውሎ ነፋስም ቀላቅሉበት! መብረቅም ጣሉበት!’ የሚል ነው የሚመስለው። ‘ገለልተኛ ሁኑ!’ አይደለም።

በዓመት ለ7 ቀናት ኳስ ተጫውቶ ለሚቀጥሉት 358 ቀናት አንዱ ከአንዱ ለማይተያይበት ስፖርት፣ ኢሕአዴጋዊ የሆነ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከሌለው ከኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ ይህን ያህል ብር መዘርገፍና እንቅልፍ ማጣት ምን አመጣው? የገንዘብ እርዳታ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የወጣትና የሴቶች ራስ አገዝ ማኅበራት ‘የእርዳታ ያለህ?!’ ብለው እንደሚጮኹ ይሰማል። እነሱን ለምን አይረዷቸውም! አልያም ደግሞ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት፣ ‘ባለሀብቱ ከመንግሥት የወሰዱትን መሬት አጥረው ቁጭ ብለዋል …..ከንግድ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ አልከፈሉም’ እያለ ሲጮህ፣ እነ አቶ አብነት አለመስማታቸው ለምንድ ነው? መፍትሄ ለመስጠት፣ መሃል አዲስ አበባ ላይ አፉን ከፍቶ የሚያዛጋው የታጠረው ቦታ ይቀርባል ወይስ አሜሪካ? …..የስፖርት ፌዴረሽኑን መርዳት ከፈለጉስ ለምንድ ነው የራሳቸውን አጀንዳና የራሳቸውን ሰው የሚመርጡበት?

ደግነቱ፣ አሁን የራሳቸውን All Ethiopian Sports Association-ZERO የተባለ የኢሕአዴግ ክንድ የሆነ ማኅበር ስላቋቋሙ፣ በገንዘባቸው የፈለጋቸውን ማድረግ ይችላሉ። የኢትዮጵያውያንን ልብ ግን ማግኘት ሕልም እንደሆነባቸው ይቀራል። እነቾምቤም ማሊያቸውን ለብሰው ይጠፋሉ። በገንዘብ በማታለል የተገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር በየትኛውም ዘመን ስለመኖሩ በበኩሌ እጠራጠራለሁ። ባዶ ስቴዲዮም፣ በገንዘብ ሽታ የሰከሩ አመራርና ለመስከር የሚዳዳቸው ዘፋኞችን ታቅፈው ከዓመት ወደ ዓመት መገለባበጥ ሱስ ሆኖ እንዳይቀርባቸው ብቻ!

እነአቶ ሰብስቤም ምን ቸገራቸው። አይፈረድባቸውም። ከኪሳቸው የሚወጣ ዜሮ አምስት ሳንቲም የለም። ይህንን መሄጃ አጥቶ መከራውን የሚያየውን በነአቶ አብነት በኩል እየሮጠ የሚመጣውን የሼሁን ገንዘብ፣ ሲፈልጉ የአፍሪካ-አሜሪካ ታዋቂ፣ ሲፈልጉ የኢትዮጵያ ከሃዲና አለቅላቂ ዘፋኝ እየገዙበት፤ እግራቸውን ሰቅለው ይዝናኑበታል። ቲኬት እየቆረጡ አዲስ አበባ ይመላለሱበታል። ሼራተን ሆነው በመስኮት ውጭውን እያዩ፣ አገጫቸውን እያሻሹና ጣታቸውን እየጠነቆሉ፤ “የድሮ ሰፈራችን እዚያ’ጋ ነበር…..አይደለም እንዴ?!” ይባባሉበታል። ልዩ፣ ልዩ ኮፍያና ከነቴራ እያሰፉና ዓርማ እያስለጠፉበት ‘ተመልከቱ! የሼሁ ባሮች ነን!’ እያሉ ይሽቀረቀሩበታል። ውድ ስቴዲየም፣ ሆቴል፣ ሊሞዚንና አውቶቡስ እየተከራዩበት፣ ጭንቀት በጭንቀት የሆነውን የሰሜን አሜሪካ ነፍሳቸውን ያስደስቱበታል። ምቾታማ ወንበር ላይ ወደ ኋላ ለጠጥ ብለው፣ ከዘራ የሚያካክል የኩባ ትምባሆ ከንፈራቸው ላይ ለጉመው፣ እግራቸውን እየወዘወዙና ለስለስ ብሎ የተከፈተ ‘የጌታችን የጋሽ አብነት እድሜ ይርዘምልን’ የሚል ሲዲ እያዳመጡ፤ ይላጡበታል። ሀብታም ባይሆኑም ሀብታም፣ ሀብታም ይሸቱበታል። አንዱ ወገን እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ ሞኝ የሚበትነውን ገንዘብ የነአቶ ሰብስቤ ቡድን እንደለመደው መሰብሰብ እንጂ ምን አገባውና ለማቆም ይሞክራል? …..አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው። እንደ አዲሱ ማኅበራቸው፣ እነሱም  የኢትዮጵያውያንን ልብ ማግኘት ሕልም እንደሆነባቸው ይቀራል። አጀንዳቸውንም ብብታቸው ሥር ሸጉጠው ከመዞር ውጭ በፌዴሬሽኑ አፍቃሪ ሕዝብ መሃል ተወሽቀው መርዛቸውን መነስነስ አይችሉም። ፌዴሬሽኑ የቀበሮዎች ዋሻ የሚሆንበት ምክንያት የለም። ሌላው ደግሞ፣ የሼሁ ገንዘብ ‘ሻሞ!’ መባል የቀረ ቀን ምን እንደሚሆኑ!? …..ወይኔ! እሱንስ አያምጣባቸው!

ኢሕአዴግ በደም እጆቹ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕርማዶ፣ በአንድ አምባገነን እዝ ሥር ሊውሉ የማይችሉ አልበገር ባይ ድርጅቶችን ጠምዝዞ ለመውሰድ መፈራገጥ ዋና ሥራው ነው። ያንን በተለያየ ጊዜ ሲያደርገው ያየነውና ወደፊትም እንዳናየው የሚያረጋግጥ ምንም ፍንጭ የለም። ESFNA ላይ የደረሰው ያ ነው። ኢሕአዴግ የተቆጣጠራቸው ድርጅቶች በሙሉ “ገለልተኛ” ይባላሉ። እውነተኛና ገለልተኞች ግን ሌላ ስም ይለጠፍባቸዋል። የፖለቲካ ድርጅትን፣ ቤተክርስትያንን፣ መስኪድን፣ የሰብአዊ መብቶች ድርጅትን፣ የባሕል መድረክን፣ የስፖርት፣ የማኅበረሰብ፣ እድርና እቁብን፤ በአጠቃላይ ማኅበራት የሚባሉትን በጅምላ መቆጣጠርና ቀን ያለፈበትን አጀንዳ በውስጣቸው በመንዛት እድሜውን ለማሻቀብ መከራ ማየቱ ግልጽ ነው።

እነአቶ ሰብስቤ የደርግ መንግሥት ጨቋኝ በመሆኑ ነበር በውጭ ሀገር ጥገኝነት ለመጠየቅ የተገደዱት። ዛሬ፣ ባለተራ የሆነውን ጨቋኝ የኢሕአዴግ ሥርዓትን በስፖርት ስም ከፊት ፊት እየመሩ ያሽሞነሙናሉ። ያንን ወጥረው የሚሰሩት፣ ኢሕአዴግ የወጣለት ጨቋኝ ስለመሆኑ ለመናገር ወኔና ፍላጎት አጥተው ሳይሆን የደም ገንዘብ ጠፍሮ ስለያዛቸው ነው። ለነገሩ ‘በፌዴሬሽኑ ስም የኢሕአዴግን የጀርባ አጥንት እንክት የሚደርግ ፖለቲካ ተናገሩልን!’ ብሎ  የወተወታቸውም ማንም የለም። እሳት የበሉ ፖለቲከኞች ስደቱን ሞልተውት የለም እንዴ! ‘ገለልተኛ ሁኑ፣ ሕገ-ፌደሬሽኑን አክብሩ፣ እንደ ጌቶቻችሁ የድምጽ ኮሮጆ አትገልብጡ’ መባላቸው እርግጥ ነው። ያንን ማንም አይክድም። እነሱ፣ የኢሕአዴግ ሥውር እጆች ሆነው፣ ESFNA’ን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው፣ መላወሻ እስትንፋስ ሲያሳጡት፤ በነሱ አመለካከት ያ አድራጎታቸው ጥሩ ነበር። “ገለልተኛ” ናቸውና!  …..ESFNA ራሱን ነጻ አውጥቶ ከርቀት የሚታይ፤ የሕዝብ፣ የባሕልና የስፖርት ምሰሶ ሲሆን፤ ይከፋቸዋል። ከፍቷቸውም ሌላ ድርጅት ከማቋቋማቸው በፊት ESFNA’ን ለመውሰድ ተፈራግጠዋል። ግን አልተሳካላቸውም። ምክንያቱም ያሉበት ሀገር ላይ ያለው ሕግ፣ የኢሕአዴግ መጫወቻ አይደለምና።

ጥቂት ሰው ሆኖ የፈለጉትን ዓይነት ማኅበር ማቋቋም በሚቻልበት ሀገር፣ ማኅበር መመስረታቸው አስገራሚ ባይሆንም፤ አሁንም ‘እኛ ገለልተኛ ነን!’ ብለው የውሸታቸውን መጠን በሁለት ዲጂት አሳድገው ሲደጋግሙት፣ ‘እንዴ! እነዚህ ሰዎች እድሜያቸው ስንት ነው?’ ያሰኛል።

ወንድምና እህቶች፣ ትናንሽ ጆሯችን ላይ ‘ሰብስቤ ኢትዮጵያዊው ፔሌ ተባለ’ የሚባል ትላልቅ ሞገድ ተለቆብን፣ የልጅነታችንን ጊዜ ስንታለል አሳልፈናል። ዛሬ “እነሰብስቤ ኢትዮጵያዊው ፔሌ ተባሉ!” መዝሙርን በአፍሪካ-አሜሪካ ሳይሆን ከማርስ በመጡ የዩፎ የሙዚቃ ባንድ አሳጅበው ቢያቀርቡ እንኳ፤ ‘የጌታ ያለህ!’ እየተባለ ወደ ESFNA ይሮጣታል እንጂ፤ ‘እስቲ ያቺን አጭርና መላጣ ዩፎ ጊታሪስት እንያት’ ብሎ የሚታደም ዜጋ የለም። ከESFNA ጎራ፣ የሕዝብ ፍቅር ካልሆነ፣ የሼሁ ተራራ የሚያክል ገንዘብ፣ የነሰብስቤ አቀባይ ክንድና የጨቋኞች አጀንዳ አይሰራም! እንደፈረደባቸው ከገንዘባቸው ጋር ተቃቅፈው፣ የኩባ ትምባሆ እየማጉ ከኩሪ ጋር ‘እጥፍ ዘርጋ’ ማለታቸውን መቀጠል ይችላሉ። በAesa-ZERO የግፈኞች መድረክ ላይ መደነስ የሚፈልግ አስመሳይ ካልሆነ በቀር ገለልተኛ የሆነ ስፖርት አፍቃሪ አያገኟትም!

አንድ ግለሰብ ለርካሽ ኢሕአዴጋዊ ዓላማ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በትኖ በተከራየው ውድና ውብ ሜዳ ላይ ጥቂትና ፀረ-ፍቅር ሆነ ከመዋል፣ ምንም ገንዘብ ባልተረጨበት ነገር ግን ብዙ ዜጎችና ፍቅር እጅ ለእጅ በተያያዙበት መካከለኛ ስቴዲዮም ላይ መገኘቱ ቃላት ሊገልጸው ከሚችለው በላይ እጅግ ያስፈነድቃል። ዳላስ ላይ የተደረገው ያ ነው።

የሕዝብ ፍቅር በዳላስ ሲያሸንፍ!

እጅ ለእጅ ታያያዝ!

ተያያዢ!

በሉ እንዘምር፣ እንደንስ!

Aesa-ZERO ይፈር!  ….. ESFNA ዳግም ይንገስ!!

*****

አንድ ከኮሎራዶ የመጣ ተሳታፊ እንዲህ አለኝ…..

“ውስጣቸው መግባት ያስፈልጋል።”

“የነማ ውስጥ?”

“የAesa-ZERO ውስጥ

“ለምን?”

“የስቴዲየሙን ሁኔታ ለመቃኘት፣ ማን ምን እንዳለ ለማወቅ፣ ቪዲዮ ለማንሳት፣ ከፍ ሲልም ገንዘባቸውን ይዞ ወደ እዚህ ለመምጣት ብልጥ መሆን አለብን። አየር ላይ እንዲበተን የፈለጉት ገንዘብ የትም መበተኑን ለማወቅ ከውስጥ ሆኖ አበታተኑን በኃይለኛ ማገዝ ያስፈልጋል።”

እነ ቾምቤ ትዝ አሉኝ።

“እባክህ ይሄንን መልእክት ለAesa-ZERO አስተላልፍልኝ። የመጣሁትም ከኒው ሜክሲኮ ነው” ያለኝ ሰው ገጥሞኛል። መልእክቱም ይህ ነበር…..

“ተመሳሳይ ሥራ እየሰራን፣ ከአንድ ዓይነት ገበያ አስቤዛ እየሸመትን፣ የፈለግነውን የቴሌቪዥን ጣቢያ እየተመለከትን፣ በየከተማው፤ የራዲዮ፣ የጋዜጣና የመጽሔት ሥርጭቶችን እያካሄድን፣ የፈለግነውን አጀንዳ የሚያንጸባርቅ የኢንተርኔት ሚዲያ እየከፈትን፣ በቀን ሁለቴ ሻወር እየወሰድን….. በአጠቃላይ ሥራ ሰርተን ማደር ከቻልን ምንም ነገር ለማድረግ በምንችልበት ሀገር ውስጥ መሆናችን ብቻ ሳይሆን፣ ‘ነጻነት’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እየገባን….. 10 ሺ ማይልስ ገደማ ርቆ ለሚገኘው ጨካኝ የአንድ ሰው አምባገነን ሥርዓት መጫወቻ መሆንን ምን አመጣው? በእንደዚህ ዓይነት መንግሥት፣ ግፍ በጫንቃቸው ላይ የተጠመደባቸውን ዜጎች ነጻ ለማውጣት አነስተኛም ቢሆን የራስን ጥረት ማድረግ ሲገባ፤ ግፉ በነዚያ ዜጎች ላይ ረጅምና ወፍራም እንዲሆን ሌት ተቀን መፍጨርጨር ምን የሚባል ፈሊጥ ነው?”

የኒው ሜክሲኮው፣ ያው አስተላልፊያለሁ።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close