ሀዘን ለመግለጽ የተሰበሰቡ አርቲስቶች የእዝን መዋጮ ተጠየቁ

ሰራዊት ፍቅሬና እቁባይ በርሄ ሚና ተጫውተዋል

ልዩ ሪፓርታዥ (ከአዲስ አበባ)

Ethiopia Zare (ማክሰኞ  ነሐሴ 22 ቀን 2004 .. August 28, 2012)፦ የአቶ መለስ ሞትን ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ዜጎች ሀዘናቸውን በአደባባይ ወጥተው እንዲገልጹ በድርጅታዊ አሰራር እየተገደዱ መሆኑ ሲታወቅ በየመስሪያ ቤቱና በየዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉ ሰራተኞችና ተማሪዎች ጥቁር ለብሰው በተወሰነ ሰዓት እንዲሰባሰቡ የታዘዙባቸው ደብዳቤዎች ለይፋ እይታ በቅተዋል። በተመሳሳይ መልኩ ለገዥው መንግስት ሁነኛ አገልጋይ በሆኑት በሰራዊት ፍቅሬ እና በእቁባየይ በርኸ  አስተባባሪነት የተሰባሰቡ አርቲስቶች የእዝን ገንዘብ ቃል እንዲገቡ መደረጉን በስፍራው የተገኘው የኢትዮጵያ ዛሬ ተባባሪ ሪፖርተር አመልክቷል።

በተያያዘም ታዋቂ አትሌቶችም ካሜራ ተደቅኖባቸው አስተያየት እንዲሰጡ መደረጉና ይህም ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መዋሉ ሳያንስ የተወሰኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችም አደባባይ ወጥተው “ጎዳና የወጣነው መለስን አምነን ነው” እያሉ የሚሳለቁበት ድራማ ብዙዎችን ያነጋገረ ሆኖ አልፏል።

ኢህአዴግ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ለማግኘት ካቀደው የፖለቲካ ትርፍ ጋር በተገንኘ የስርአቱ ታማኝ የሆኑ አርቲስቶችም በተመሳሳይ መልኩ ሀዘናቸውን መግለጽ የሚችሉበት መድረክ እንዲፈጠር ሸብ ረብ እየተባለለት ነው።

ይህ በህወሀት አባሉና  ለረጅም አመታት የሜጋ ስራ አስኪያጅ በነበረው  በእቁባይ በርኸና የስርአቱ አቀንቃኝ በሆነው በቀድሞው ብሄራዊ ወታደር በሰራዊት ፍቅሬ አጋፋሪነት በተጀመረው ሽር ጉድ ላይ የሙያቸውን ውጤት አደባባይ ለማውጣት የገዥው ፓርቲ በጎ ፈቃድ የግድ ያስፈልገናል በሚል ፍርሀት ሰልፋቸውን ያሳመሩ አንዳንድ አርቲስቶችም ተገኝተውበታል።

ዝርዝር ሂደቱን አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዛሬ ተባባሪ ሪፖርተር እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቲያትር በተደረገው የአርቲስቶች ውይይት ላይ፤ አቶ ዕቁባይ በርሄ እና ሠራዊት ፍቅሬ እንደዚሁም የቶም ቪዲዮ ባለቤት መሆናቸው የተነገረው አቶ ቶማስ ባቀረቡት የመዋጮ ጥያቄ መሠረት ተሰብሳቢዎቹ አርቲስቶች ከ300ብር እስከ 20ሺህ ብር ለአቶ መለስ ዜናዊ የዕዝን መዋጮ አዋጥተዋል።

በዚሁ የመዋጮ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ  ከታደሙት መካከል የ300ብሩን ልግስና የሰጡት የሃገር ፍቅሩ ተዋናይ ችሮታው ከልካይ ሲሆኑ፤ ፍቅር አዲስ ነቅአ ጥበብ፣ ኪሮስ ኃይለ ስላሴንና ሃመልማል አባተን ጨምሮ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል አርቲስቶች የአንድ አንድ ሺህ ብር መዋጮ አድርገዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ ሳምሶን ማሞ 10ሺህ ብር፣ታምሩ ብርሃኑ 5ሺህ ብር፣ የደራሲያን ማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በግላቸው አንድ ሺህ ብር ሲለግሱ በሚሰሩበት አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት ስም 5 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የጋላክሲ ፊልም አምራች ድርጅት ባለቤት ነኝ ያሉ ግለሰብ በበኩላቸው 10 ሺህ ብር በጥሬው ገቢ ያደረጉ ሲሆን ሌሎችም እሳቸውን በመከተል ከሦስት እስከ 5 ሺህ ብር “አለን” ያሉትን ጣል ጣል አድርገዋል።

መድረክ መሪዎቹ አቶ ቶማስ እና አቶ ዕቁባይ በርሄ አምስት አምስት ሺህ ብር፣ ሠራዊት ፍቅሬ በበኩሉ 10 ሺህ ብር እንደሚያዋጡ ቃል ገብተው ባስጀመሩት የዕዝን ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ቃል የተገባውን ሳይጨምር 120 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ከ 10 ደቂቃ ባልዘለለው የማሰባሰቢያ ዝግጅት መገንዘብ ተችሏል።

ዋና ዓላማው አርቲስቶች ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ከስፖርት ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሃዘናቸውን ነሐሴ 23 ቀን 2004 ዓ.ምህረት በቤተ-መንግሥት እንደምን መግለጽ ይገባቸዋል… በሚለው ላይ መወያየት የነበረውና በተለይ በዕሁዱ የቀብር አፈጻጸም ሥርዓት ላይ ሚናቸው ምን ሊሆን እንደሚገባው ማስረዳት የነበረው የነሐሴ 22 ቀኑ የአርቲስቶች ስብሰባ ወደ ዕዝን መዋጮ ሥነ- ሥርዓትነት መለወጡ ብዙዎችን ያስገረመ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉት አርቲስቶች ያለ ይሉኝታና በመልካም ፈቃደኝነት ነበር የዕዝን መዋጮውን ሲለግሱ የነበሩት።

ከመዋጮው ባሻገር የአርቲስቶቹን የሃዘን መግለጫ ሥነ-ሥርዓት ፤ሠራዊት ፍቅሬ፣ጌትነት እንየው፣ ደበሽ ተመስገን፣ሙሉዓለም ታደሠ፣ፍቅር አዲስ ነቅአ ጥበብና ንዋይ ደበበ እንዲመሩት ፍቃድ የተሰጣቸው መሆኑ ተጠቁሟል።

በወጣውም ቅድመ ፕሮግራም መሠረት ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ምህረት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ወንዶች  ሙሉ በሙሉ ጥቁር ለብሰው፣ ሴቶች ጥቁር ለብሰውና ባለ ጥቁር ጥለት  ነጭ ነጠላ አዘቅዝቀውና ቋጥረው በመልበስ በብሔራዊ ቲያትር ደጃፍ ላይ በመገኘት ወደ ቤተ-መንግሥት ለሚደረገው ጉዞ ዝግጁ እንዲሆኑ ተነግሮአቸዋል፡፡ በዕለቱ ዝናብ ቢዘንብም ሆነ ዶፍ ቢጥል ለጠቅላይ ሚንስትር ሞት ክብር ሲባል ማንኛውም አርቲስት ዣንጥላ መያዝ እንደሌለበት ተደጋግሞ ተነግሮታል።

እንደዚሁም ሁሉ፤ ከብሔራዊ ቲያትር ወደ ቤተ-መንግሥት በሚደረገው የዕግር ጉዞ ወቅት ማናቸውንም ዓይነት ንግግርም ሆነ ቀልድ ነክ ጉዳይ በማንሳት የሃዘን መግለጫ ሥነ-ሥርዓቱን እንዳያውክና ማረም ለማይቻለው የመገናኛ ብዙሃን ካሜራ ሰለባ እንዳይሆን ሠራዊት ፍቅሬ መላልሶ  አርቲስቶቹን አስጠንቅቋል።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close