ክቡር ጠ/ሚኒስትር ላለመደራደር በቂ ምክንያት ካለዎት ቢነግሩን? (ከአስራት ጣሴ የአንድነት ዋና ፀሐፊ)

 

ከ2ዐዐ2 ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ አሁንም ድረስ ያልበረደ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንበ (ለነገሩ ህግ ነው) ለምን አትፈርሙም ከኢህአዴግ የሚቀርብ ያልተቋረጠ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን እንከን የለሽ የምርጫ ሥነ- ምግባር ደንብ ካልፈረማችሁ ንግግር ብሎ ነገር የለም በማለት በፓርላማ ቀርበው ጠቅላየ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ተናግረዋል፡፡ አሁንም ሌሎች እየነገሩን ያሉት ቃል በቃል ይህንኑ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከመድረክ ጋር ላለመደራደር፣ ላለመወያየት ይህ ምክንያት እስካለ ድረስ ሌላ መፈለግ አይጠበቅባቸውም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለሕዝብ ዝርዝሩን ማሳወቅ ተገቢ ስለሆነ ዘሬ በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

ለመነሻነት ግን ስለ ምርጫ ሥነ-ምግባሩ ደንብ አጠር ያለ አስተያየት ቢሰጥ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው የምርጫ ሥነ-ምግባሩ የተዘጋጀው ሲውዲን አገር በሚገኘው International Institute for Democracy and Electoral Assistance በአጭሩ International IDEA በሚለው ድርጅት ነው፡፡ ሰነዱ የተሟላ ይሆን ዘንድ ሁለት ክፍሎች ይጎሉታል፡፡ አንዱ Code of Conduct for the Ethical and Professional Observation  of Election (የምርጫ ታዛቢዎች የሥነ-ምግባር ደንብ)  ሲሆን ሌላው ደግሞ Code of Conduct for the Ethical and Professional Administration of Elections (የምርጫ አስተዳደር የሥነ ምግባር ደንብ) የሚሉ ናቸው፡፡ ሦስት ክፍሎች ከአሉት ሰነድ አንዱን ብቻ ለይቶ ፈርሙ ማለት በራሱ ገና ከመነሻው ችግር ያለበትና እንከን እንዳለው በግልጽ የማያሳይ ነው፡፡ ለምርጫው ነፃና ፍትሓዊ መሆን ሦስቱም  ክፍሎች ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በተለይም ያልተካተቱ ሁለት ክፍሎች ከምርጫ ሥነ ምግባሩ በተሻለ ሁኔታ ለምረጫው ፍትሓዊነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ሁለቱን ሰነዶች ትቶ በአንዱ ላየ ብቻ እንፈራረም የማለት መብት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይገባም፡፡

በመሠረቱ መድረክ በሥነ-ምግባር ደንቡ ላይ አልነጋገርም አልፈርምም አላለም፡፡ ተደራዳሪ ስለነበርኩ ጉዳዩን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ የሥነ ምግባርን ደንብ መፈረም የሚጠቀም ከሆነ ዋናው ተጠቃሚ መድረክ ነው፡፡ ምክንያቱም በጽሑፍ ደረጀ ከሆነ የምርጫ ሥነ ምግባሩ ዋና ዓላማ ምርጫው ግልጽ፣ ነፃ ሠላማዊ ህጋዊና ዴሞክሪሱያዊ ሆኖ በሕዘብ ተቀባይነት እነዲያገኝ ለማስቻል ነው ስለሚል፡፡ ታደያ ነገሩ ሁሉ የእውነት ከሆነ መድረክ ከዚህ ሰነድ መፈረምና በተግባር መተርጎም በላይ የሚፈልገውና የሚያስደስተው ምን ነገር ሊያገኘ ነው አልፈርምም የሚለው? መድረክ ከምርጫ 2ዐዐ2 በፊት ጀምሮ በተደጋጋሚ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በተለይም የኡትዮጵያ አጋር ቡድን (Ethiopian Partners Group) ከተባለው  የበርካታ አገሮች ዲፕሎማቶች ስብስብ ጋር በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይቶች አካሂዷል፡፡ የመድረክ ጥያቄ ግልጽና አጭር ነበር፡፡ ከምርጫ ሥነ-ምግባሩ በተጨማሪ የ2ዐዐ2 ዓም ምርጫን ነፃና ፍትሓዊና ተአማኒ ሊያደርጉ በሚችሉ ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይም እንደራደር ነው ያለው፡፡ የጉዳዮቹን ዝርዝር መድረክ ነሐሴ 22 ቀን 2ዐዐ1 ዓም ጳግሜ 4 ቀን 2ዐዐ1 ዓም መስከረም 25 ቀን 2ዐዐ2 ዓም ለኢህአዴግ በፃፈው ደብዳቤ ግልጽ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ ግን እንደ ፓርቲ ከሌለው ሥልጣን ውጭ እኔ ካቀረብኩት አጀንዳና ከያዝኩት የድርድር ስልትና አካሄድ ውጭ መነጋገር አይቻልም አለ፡፡ ታማኝ ተቃዋሚዎችና የተቃዋሚዎች ተቃሚዎችን ይዞ መድረክን አግሎ የምርጫ ሥነ-ምግባሩ ተፈረመ፡፡ ቆየት ብሎም የሥነ ምግባሩ ደንብ በፓርላማ ፀድቆ አዋጅ ሆኖ በነጋሪት ጋዜጣ ወጣ፡፡ በማንኛውም መመዘኛ የሥነ ምግባር ደንቡን ፈርሙ ድራማ እዚህ ላይ መቆም ነበረበት፡፡ ምክንያቱም መደረክ ሆነ አባል ፓርቲዎች እንደ ሕጋዊና ሠላማዊ ድርጅቶች የአገሪቱን ሕግ ተቀብለውና አክብረው ነውና የሚንቀሳቀሱት፡፡ አምርረን የምንቃወማቸውንም ፀረ-ሽብርተኛ  ሕግ፣ የሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕግ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕግ ሆኑ ሌሎች ሕጎችን የምንታገለው በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ  ውስጥ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱ ሕገ ሆኖ በወጣ ሕግ ላይ የመፈረም መብትም ግዴታም የለባቸውም፡፡ ፈርሙ ከተባለ ደግሞ ለምን በሌቹ በፖርላማ ፀድቀው በሚወጡ ሕጎች ላይ እንዲፈርሙ አልተጠየቁም፡፡ ጉዳዩ መድረክን የማንበርከክ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ስሌት ነው፡፡ ድርድር ግን የጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win) ስሌት ነው፡፡

(አስራት ጣሴ የአንድነት ዋና ፀሐፊ)

ስለ የምርጫ ሥነ-ምግባሩ ደንብ ስንነጋገር ሌሎችም መነሳት ያለባቸው ነጥቦችም አሉ፡፡

  1. አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀጽ 1ዐ5 ለምርጫ ቦርድ የሚሰጠው መብት በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ‹‹ቦርዱ የሚመለከታቸውን አካላት በማማከር ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ማከናወን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ተጨማሪ ዝርዝር የምርጫ ደንብ ሊያወጣ ይችላል›› ይላል፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ በምርጫ ሥነ-ምግባሩ ዝግጅተ ወቅት የፈፀመው ተግባር የምርጫ ቦርድ ሥራን መንጠቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ደንብ ተብሎ የተዘጋጀውን አዋጅ አድርጎ በም/ቤት ማፀደቅ ያስፈለገው፡፡ ይህም የሚያሳየው ዘግይቶም ቢሆን  ለአቀደው ድብቅ ዓላማው ማስፈፀሚያ ሲል የተጠቀመበት አካሄድ መሆኑ ነው፡፡ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድም እንደተለመደው ሁሉ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን  በአግባቡ ባለመጠቁሙ የዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግር አባብሶታል፡፡ ለነገሩማ ተጋኖ የሚነገርለት የምርጫ ሥነ-ምግባሩ ደንብ ሲታይ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 1ዐ1 እስከ 1ዐ5 ባሉት የምርጫ ሥነ ምግባር መርሆዎች ከአስፈረውና ለፓርቲዎች ካሰራጨው ሰነድ ብዙም የተለዬ ቁም ነገሮችን ያልያዘ ነው፡፡
  1. International IDEA  የተሰኘው ድርጅት የምረጫ ሥነ-ምግባሩን ደንብ የሚመለከተው በተለያየ ሁኔታ ነው፡፡ የሥነ-ምግባሩ ደንብ በምርጫ ወቀት ብቻ ሊያገለግል የሚችል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በአማራጭ ከምርጫው ቅስቀሳ ጀምሮ ውጤቱ እስከሚገለጽበት ጊዜ ብቻም ሊሆን ይችላል፡፡ በጊዜ ገደበ የሚያለግል ማለት ነው፡፡ የአገሪቱ የመርጫ ህግ አካል ሆኖም ሊወጣ ይችላል፡፡ በምርጫ ሥነ ምግባሩ የሚጠቀሱት ጥፋቶች በአገሪቱ በወጡ የተለያዩ ሕጎች አማካኝነትም ሊዳኙ ይችላሉ፡፡
  1. የምርጫ ሥነ-ምግባሩ ደንብ በዋናነት የሚያተኩረው ለምርጫ ዘመቻ ጥቅም ላይ ስለሚውል ቋንቋ ይዘት፣ ስለ ማስፈራራትና አመጽ ስለመቀስቀስ፣ ስለ ፓርቲዎች ምልክቶች፤ ለመራጭ መደለያ ስለመስጠት፣ አለመግባባቶች ስለሚፈቱበትና ስለ አቤቱታዎች አቀራረብ ወዘተ ነው፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ  ልዩ ቦታና አቅም ያለው የሚያስመስለው የሥነ-ምግባር ደንብ በጣም የተጋነነ ከመሆኑም ባሻገር ይህ ነው የሚባል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ አጀንዳ ለማስለወጥ ካልሆነ በስተቀር፡፡
  1. የምርጫ ሥነ-ምግባሩ አመጣጥ ይዘት ጠቀሜታና ሕግ ሆኖ በአዋጅ መውጣቱን ስንመለከት አንድ ተገቢ፣ አሳሳቢና መሠረታዊ ጥያቄ ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ለመሆኑ ኢህአዳግና በአሱ የሚመራው መንግሥት መድረክን የሥነ-ምግባሩን ደንብ ካልፈረማችሁ አንደራደርም አንወያይም የጋራ ጉዳይም የለንም የሚለው ለምንድ ነው?  የሚለውን ማለት ነው፡፡

የዚህ ጥያቄ መልስ ቀላልም ግልጽም ነው፡፡ ለመሻነት ግን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‘’ African Development: Dead Ends and New Beginnings’’ በተባለው ጽሑፋቸው ያሰፈሩትን መመልከት ይገባል፡፡

‘’Developmental Policy is unlikely to transform a poor country into a developed one within the time frame of the typical election cycle. There has to be continuity of policy if there is to be sustained and accelerated economic growth. In democratic polity uncertainty about the continuity of policy is unavoidable. More damagingly for development, politicians will be unable to think beyond the next election e.t.c it is argued therefore that the developmental state will have to be undemocratic  in order to stay in power long enough to carry out successful development’’ (ሰረዝ የራሴ) ትርጉሙም በግርድፉ የልማት ፖሊሲዎች በአንድ የምርጫ ዘመን ውስጥ ደሀ አገርን ወደ ሀብታም አገር ሊለውጥ አይችልም፡፡ የተፋጠነና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የፖለሲዎች ቀጣይነት አሰፈላጊ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የፖሊሲዎች ቀጣይነት ማጣት ደግሞ የሚያስወግዱት ነገር አይደለም፡፡  ለልማት ትልቁ አደጋና ጥፋት ደግሞ የፖለቲከኞች  ከሚቀጥለው የምርጫ ዘመነ በአሻገር መመልከት አለመቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ክርክር ልማታዊ መንግሥት የተሳካ እድገት ለማምጣት ይችል ዘንድ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በመሆን የተፈለገውን የተሳካ ልማት ለማምጣት እስከሚያስችለው  ጊዜ ድረስ በሥልጣን ላይ መቆየት ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ (ሰረዝ የራሴ)፡፡

ዋናው መመሪያና አቋም ይህና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሆኖ ሳለ ታዲያ ከምን ሥነ-አመክንዮ (logic) ወይም ምክንያት ተነስቶ ነው ኢህአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባሩን  ፈርሙ የሚለው፡፡ እረ እንዲያውም ምርጫ ማካሄድስ ለምን ያስፈልጋልል? እዚህ ላይ ተረስተው ከሆነ ማስታወስ ያለብን ቁም ነገሮች አሉ፡፡ በ1997 ዓም ምርጫ ወቅት እኮ በኢህአዳግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች  መካከል የምርጫ ሥነ ምግባር ሰነድ ተፈርሞ ነበር፡፡ ምርጫውን በፍፃሜው ከታየው ቀውስ አላዳነውም እንጂ፡፡ በ2ዐዐ2 ዓም ምርጫ ወቀትም የሥነ ምግባሩን ደንብ ከፈረሙት ፓርቲዎች መካከል ዘግይቶም ቢሆን ደንቡን መፈረሙ ከችግር ስለአላዳነው መኢአድም ከስምምነቱ እራሱን ማግለሉ ይታወቃል፡፡ እንዲያው ለነገሩ ሁለትን አጋጣሚዎች አነሳሁ እንጂ የአገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ላለፉት ሃያ ዓመታት እንደተፈለገው እየተጣሰ አይደለም ወይ? በቅን መንፈስ (in-good-faith) ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለታሪክ ታምነን ካልሰራን በስተቀር በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ሰነዶች ቢፈረሙ ከኢህአዴግ ጥቃት ያድናሉ ማለት ሞኘነት ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግንም አለማወቅ ማለት ነው፡፡

የምርጫ ሥነ-ምግባሩን ፈርሙ ጥያቄን በብዙ መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ በአንድ መልኩ ሲታይ ኢህአዴግ ከ1997 ዓም ምርጫ በኋላ በግልጽና በጉልበት ሲመቸውም በስልት የሚያካሄደው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክሪሱ ቅልበሳ አካል ነው፡፡ ለሠላማዊ ሕጋዊ ፖለቲካና ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ግንባታ ያለው ከፍተኛ ጥላቻ አካልም ነው፡፡ በአጠቃላይ መድረክን አስፈላጊ መስሎ ሲያገኘው አባል ፓርቲዎችን ነጥሎ ፀረ-ሠላም፣ ፀረ-ሕዝብ ሽብርተኞች፣ የሻዕቢያ ተላላኪ ወዘተ ብሎ የማጥቂያ ስልቱ አካል ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ተቃዋሚ ፓርቲን መፍቀድ በተግባር ግን ለኢህአዴግ አስጊ የሚባሉ ፓርቲዎች ውጤት አልባ እንዲሆኑ የማኮላሸት አካሄድ አካል ነው፡፡ ወዳጆቻችን ይህንን ስትረዱት ጠ/ሚኒስትሩም ሌላ ምክንያት ማዘጋጀት የግድ ይላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን  እግር ሲያወጡ ግን አንቆርጣለን›› ያሉት አነጋገር አካል ነው፡፡ ሀቀኛ ተቃዋሚዎችን ተቀባይነትና ተደማጭነት የማሳጣትና ከሕዝብ የመነጠል ድርጊት አካል ነው፡፡

በሌላ በኩልም ሁኔታው ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ አንፃርም ይታያል፡፡ በምርጫ ላይ የተመሠረተ አምባገነናዊ ሥርዓት (Electoral Authoritarian) የመፈጠር መርህ አካል ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የይስሙላ ደሞክራሲ ነው፡፡ ለመኖር የሚፈቀድላቸው ፓርቲዎች የአጋርነት ሚና ወይም የማስመሰል ሚና የሚጫወቱ የምርጫ ጨዋታዎችን የሚያሳምሩ ሕልውና የሌላቸው አሻንጉሊቶች ብቻ ናቸው፡፡  የአውራ ፓርቲ አገልጋይ መሆን አለባቸው፡፡ ጠንካራነትና ተቀናቃኝነትን አይፈቅድም፡፡ ድርጊቱ በተግባር የአንድ ፓርቲ ሥርዐት የመፍጠር እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ እስከአሁን ካልተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የዴሞክራሲ አዋላጅ ዋና መሣሪያ የሆነውን ነፃና ፍትሓዊ ምርጫን አይቀበልም፡፡ በአፍሪካ ተሞክሮ ላይ ጥናት ያካሄዱ ዲያመራድ የተባሉ ምሁር ፍሪደም ሀውስ (Freedom House) በተባለው ተቋም ጥናት ላይ በመመርኮዝ የአፍሪካን መንግሥታት አራት ቦታ ላይ ይመድቧቸዋል፡፡ እኚሁ ምሁር ኢትዮጵያን የመደቡት በይስሙላ ዴሞክራሲ (Pseudo-Democracy) ምድብ  ውስጥ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያልጠበቁ የመድብለ ፓርቲ ምርጫዎችን ለይስሙላ የሚያካሂዱ ማለት ነው፡፡ ዋና ዓላማውም አንድን አምባገነን ፓርቲን ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ ሲሆን በሌላ በኩልም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት ተቀባይነት እንዲያኙና የተሻለም ገጽታ እንዲኖርራቸው ለማድረግ ነው፡፡  ‘’Index Politics ’’   በ2ዐ1ዐ ባወጣው የዴሞክሪሱ ደረጃ Democracy index-The Economist Intelligence unit 60 መመዘኛዎችን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን በአምባገነንነት ሥርዓት ውስጥ ያለች አገር ብሎ መድቧታል፡፡

በሌላ በኩል ሲታይም ኢህአዴግ አንዳንዴ በግልጽ ሌላ ጊዜ በተዘዋዋሪ ልማትንና የዴሞክራሲን ትስስርና ቁርኝት ለማደብዘዝ እንዲያውም ለመለያየት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካልም ነው፡፡ እራሱን ልማታዊ መንግሥት ብሎ በመሰየም ዋናው የአገራችን ችግር የልማት፣ የዳቦ ጥያቄ ነው የሚለው አካሄድ አካል ነው፡፡ ይህም ዴሞክራሲን ለማኮላሽት የሚቀጠምበት ስልቱ አካል ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ዓመታት የፈጁ ስለ ዴሞክራሲ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች የሚያሳዩት እውነታዎች አሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትና የኢኮኖሚ እድገትና ልማት መካከል ቀጥታ ግንኙነት አለ፡፡ እንደያውም ሁለቱ አይለያዩም ማለት ይቀላል፡፡ ዴሞክራሲ ልማትን ያሳድጋል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲ ለኢኮኖሚ እድገትና ለልማት የሚያስፈልጉ የፖለቲካ ተቋማት በጥሩ ሁኔታ እንዲሰሩ ያደርጋል  ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበራል፣ የግለሰቦች ሰብዓዊና የሲቪል መብቶችና ነፃነቶች ይከበራሉ፣ መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓትን ያረጋግጣል፣ ሙስናን ይከላከላል ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ለእድገትና ልማት ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መሠረቱ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት መኖር ነው፡፡ ይህም መድበለ ፓርቲ ሥርዓትን፣ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫን፣ ነፃ የብዙሃን መገናኛዎችን መኖርና በብቃት መስራትን ያካትታል፡፡

በሌላ አንፃር ሲታየ ደግሞ አምባገነናዊ ሥርዓት ለንብረት ባለቤትነት አደገኘነት አለው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት (በኢህአዴግ ትንታኔ) የተወጠናወተው ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን አያሰፍንም፡፡ አምባገነኖች  በታሪክም ሆነ ዛሬ የሚታወቁት የመንግሥት ሥልጣን ጠቅልሎ በመያዝና ከዚህም የሚመነጨውን ጥቅማ ጥቅሞች ለራሳቸውና ደጋፊዎቻቸው በተለይም በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚረዱዋቸውን  በማበልፀግ ነው፡፡ ሙስና የተንሰራፈበት ሥርዓት ነው፡፡ የነፃ ገበያን ያዛባሉ በመሆኑም ለልማትና ለእድገት አመቺ አይደለሙ ብቻ ሳይሆን ፀር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ በልማታዊ መንግሥት ስም እየተፈፀመ ያለው ፀረ-ልማትና እድገት ሥራዎች ናቸው፡፡ ልማትና እድገት ያመጣ መንግሥት ወይም ገዢ ፓርቲ ምርጫን ለማሸነፍ ሕዝብን ማስፈራራት፣ ሕዝብን በአንድ ለአምስት መጠርነፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና አባሎቻቸውን ማሰር ማዋከብ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎች በስልትና በዘዴ መከልከል፣ የምርጫን ሥርዓት ሚሰጥራዊነት ለማሳጣትና የቡድን ሥራ ማድረግ አያስፈልገውም ነበር፡፡

በአጠቃላይ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈርሙ ድራማ ምክንያቱ ግለጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ለመቆየት (ስንት ዓመት እንደሆነም የሚታወቅ አይመስልም)

ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ አሠራር የመጠቀም ስልቱ አካል ነው፡፡ ጽሑፌን በቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ አነጋገር አጠቃልላለሁ፡፡ ‘’Those who make peaceful revolution impossible will make violent revolution inevitable’’ ከሞላ ጎደል ሲተረጎም ሠላማዊ ለውጥን የማይቻል የሚያደርጉ ሰዎች የአመጽ ለውጥን የማይቀር ያደርጉታል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ ደግሞ የሚያስፈልጋት ሠላማዊና ሕጋዊ ለውጥ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ በብዙ ችግሮች የተተበተበች ናት፡፡ ስለዚህ መፍትሔው የምርጫ ሥነ-ምግባር ፈረሙ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከምርጫ በላይ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሥልጣን በላይ ነው፡፡ ጉዳዩ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የታሪክም የሕግም ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬም ከረፈደም ቢሆን ኢህአዴግና እሱ የሚመራው መንግሥት በሰከነ አዕምሮና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድረሻ አካላት ጋር ቅድመ ሁኔታ የሌለው ድርድርና ውይይት ማድረግ አለበት እላለሁ፡፡ ወይም  ከሥነ ምግባር ደንቡ የተለየ በቂ ምከነያት መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የሚያገናኘን፣ የሚያወያየን የጋራ አጀንዳ የለንም ማለት ጠቃሚም ተገቢም አይደለም፡፡ የጋራ አገር አለን፣ የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ከፍተኛ ችግር አለብን፣ አብዛኛው ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ ጥቂቶች የሚበለጽጉባት፣ የሚንደላቀቁባት አገር ውስጥ ነን ያለነው፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥሰት ተንሰራፍቷል፣ የብዙሃን መገናኛ አውታሮች የአንድ ፓርቲ መገልገያዎች ሆኗል፡፡ ነፃ ፕሬስ በሞት አፋፍ ላይ ነው፣ ቅድመ ሳንሱር በጓሮ በር እየመጣ ነው፣ የአሜሪካ ድምጽና የጀርመኝ ሬዲዮኖች እየታፈኑ ነው፡፡ የቡድኖች የመጨቆን ስሜት የመከፋት ስሜት እየጨመረ ነው፣ ሙስና ተንሠራፍቷል፡፡ ወ.ዘ.ተእነዚህ ጉዳዮች እንድንወያይ፣ እንድንነጋገር ካነሱ ሊያወያዩን የሚችሉ ጉዳዩች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? አገራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢህአዴግ በለመደው የግትርነት አቋሙ ቀጥሎ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ‹‹ ሁለም ነገር የሚከለሰው፣ የሚለወጠው፣ በመቃብሬ ላይ ነው›› የሚል ከሆነ ይህው ይፈፀም ዘንድ የግድ ይሆናል፡፡

 

(ከአስራት ጣሴ የአንድነት ዋና ፀሐፊ)

          በፍትሕ ጋዜጣ  ሰኔ 22 ቀን 2ዐዐ4 ዓም የወጣ ጽሁፍ

 

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርካት! ይጠብቃትም !

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close