ጥቂት ምክር ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ከመለስ ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና ያሰተውሉ።

 

ዳንኤል መኩሪያ ከኖርዌይ

ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፤የእግዚአብሔርም ድካም  ከሰው ይልቅይበረታልና።(1ኛ ቆሮንጦስ 1፥25)

Because the foolishness of God is wiser than men, and the weakness of God is stronger than men.

ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅድሚያ የታላቂቷ ሀገር የኢትዮጵያ መሪ እንዲሆኑ እግዚአብሔር ይህን ታላቅ እድል ስለሰጠወት እንኳን ደስ ያለወት እላለሁ።
ይህችን አጭር መልዕክት እንድጽፍልዎ ያነሳሳኝ  የኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለማህላ በፈፀሙበት ዕለት ያደረጉት ንግግር ሲሆን ፥ይህንኑ ጽሁፍ በማዘጋጀት ላይ እያለሁ ደግሞ የመጀመሪያውን ንግግርዎን የሚያጠናክር ቃለ ምልልስ በኒዮርክ የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ለመካፈል በሄዱበት ከአሜሪካ ድምጽ ሬድዬ ጋር እንዳደረጉ አደመጥኩ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ በመሆንወና እኔም የእርሥዎን እምነት ስለምጋራ ምክሬንም ከዚሁ መጽሐፍ አደርጋለሁና እንደሚቀበሉኝ ተስፉ አደርጋለሁ አስተዋይ ምክርን ቀለቡ ያደርጋል ይላልና ቃሉ።
የኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሀገርዎን ማገልገል ሲጀምሩ ከፊትዎ እጅግ አስቸጋሪና ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩ ውስብስብ ማህበራዊ፥ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንደተረከቡ እገነዘባለሁ።እንዳለመታደል ሆኖ አገራችንን በተከታታይ ያስተዳድሩ የነበሩት የንጉሱም ሆነ የኮሎኔል መንግሥቱ ወታደራዊ ጥበብ የጎደለው አመራር አገራችን አሁን ላሉባት ውስብስብ ችግሮች የራሳቸው ሚና የነበራቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ችግሮች ግን ሀገራችንን ለ21 ዓመታት ሲመሩ በነበሩት በቅርቡ፥ በሞቱትና እርሥዎ በተኳቸው በአቶ መለስ ዜናዊ አንባገነንነትና ከእኔ ሌላ አዋቂ ለአሳር ከሚል አስተሳሰብ የተነሣ የተከሰቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ አይነት የራስን ስልጣን ከማደላደልና ከፉፍሎ ለረጅም ጊዜ ለመግዛት ከነበራቸው የጠለቀ ፍላጎት የተነሳ፥ችግሮቹ በትውልድና በአገር ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት መዘዝ እየታወቀ ታስቦባቸው የተከሰቱ ናቸው።
እነዚህ ችግሮች በብዙ የአገራችን ምሁራን የተተነተኑና መፍትሔም የተጠቆላቸው ከመሆኑ ባሻገር ለእርሥዎ እነዚህን  ችግሮች መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናልና ለተነሳሁበት ዓላማ እንደማሣያ የሚጠቅሙኝን ጥቂቶቹን ልጥቀስ፧
፨ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የክልል አወቃቀርና የአንዱን ቋንቋ ተናጋሪ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ፥ልዩነታችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ውበት መሆኑን ተገንዝበን እርስ በእርሥ ተዋድደን እንድንኖር ከመጣር ይልቅ እንዳንተማመን ታስቦበት የተዘራ የጥላቻ ዘር
፨በተሳሳቱ የኢኮኖሚ ፓሊሲዎች የተነሳ እጅግ ደካማ ኢኮኖሚ፥ስራ አጥነት፥እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ግሽበት
፨በሙስና የተዘፈቀ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም አመራር
፨ከአንድ አካባቢና ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት የተያዘ ኢኮኖሚ፥የሀገር መከላከያና የደሕንነት ተቋም
፨ሕዝብ ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ እንዳይችል ሁሉም አይነት የመገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቁጥጥር ስር የሆነበት፥ጥቂት የነበሩት የግል ጋዜጦች ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ የተዘጉባት የጋዜጦች አዘጋጆችና አምደኞችም ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጽ በመጻፋቸውና በመናገራቸው የሚታሰሩባትና የሚሰደዱባት አገር
፨እውነትን ለመናገር የቆረጡ ለአገርና ለሕዝብ ድምጽ የሆኑ ሰዎች በሀሰት እየተከሰሱ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት እንዲፈረድባቸው የሚያደርግ የፍትሕ ተቋማት ያሉባት አገር
 
ታዲያ እነዚህ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታትና አገራችንን በተገቢው መንገድ ለመምራት ከሰው ማስተዋልና ጥበብ ያለፈ የእግዚአብሔር ማስተዋልና ጥበብ ያስፈልጋል ብየ አምናለሁ።እግዚአብሔር ደግሞ ማንም ጥበብ የጎደለው ቢኖር ሳይነቅፍ በልግስና የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን ለእርሱም ይሰጠዋል(ያዕቆብ 1፥5) ይላል።ታላቁ የእሥራኤል ንጉስ ሰለሞን ጠቢቡ የሚለውን ስም ያገኘው ከአባቱ ከንጉስ ዳዊት የመሪነት ወንበሩን በተረከበ ጊዜ ይህን ታላቅ ሕዝብ  ለመምራት የሚያስችለውን ማስተዋልና ጥበብ እንዲሰጠው እግዚአብሔርን በመለመኑና እግዚአብሔርም ስለሰጠው ነበር።ንጉስ ሰለሞን በአገዛዝ ዘመኑ እጅግ ታላላቅ ስራዎችን የሰራ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያ ንግስት እንኳ ሩቅ አገር አቋርጣ የጥበቡ ተቋዳሽ እንደነበረች ተፅፏል ፣ይህ ደግሞ ከአገሩ አልፎ ለሌላ አገርም በረከት እንደነበር ያሣያል።
ራሱ ንጉሥ ሰለሞን ስለ ጥበብ አስፈላጊነት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ።(ምሳሌ 4፥7)
 
 ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሆይ እርስዎ  ከእሥራኤል ንጉስ ሰለሞን ተምረው አገራችንና ሕዝባችንን ከገቡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አውጥተው በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ ውስጥ ከጠቢባኑ ተርታ ይሰለፉሉ የሚል ተስፉ ነበረኝ፥ይሁን እንጅ የታላቁና የአስተዋዩ መሪ የመለስ ዜናዊን ራዕይ ሳይበረዝና ሳይከለስ አጠናክሬ እቀጥላለሁ የሚለው ንግግርዎ ስጋት ላይ ጥሎኛል።ለመሆኑ ይህን ማለት ከላይ በጥቂቱ የጠቀስኳቸውን ችግሮች አጠናክሮ መቀጠል መሆኑን እንዴት ማስተዋል ተሳነዎት?
 ንጉስ ሰለሞን እኮ የአባቴን የንጉስ ዳዊትን አመራር አጠናክሬ እቀጥላለሁ አላለም ይልቅስ የተሻለ ለመስራት የሚያስችለውን ህያው ጥበብ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ የራሱን ድርሻ አበርክቶ አለፈ እንጅ ከሟች አባቱ ከዳዊት መንፈስ ጋር የሙጥኝ አላለም፥፥ለዚህ ነው እኔም ከሟቹ መለስ ዜናዊ የማያዋጣ ራዕይ ጋር ሙጥኝ ማለት አይጠቅምምና ያስተውሉ ዘንድ  ከመለስ ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና ያሰተውሉ። የሚለውን ርዕስ ለመልዕክቴ የሰጠሁት።
 
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሆይ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰ ጠቃሚ ምሣሌ የሚሆን ሌላ ንጉስ ታሪክ ጥቂት ልጥቀስና መልዕክቴን  ልቋጭ (ታሪኩ በነገስት መጽሐፍ ቀዳማዊ ምዕራፍ 12 ይገኛል)።እንዲህ እንዳሁኑ እኛ እንዳለንበት እርሥዎ ወደ ስልጣን እንደመጡበት ዐይነት፥ የእስራኤል ንጉስ ሰለሞን ከሞተ በኋላ በእሱ ምትክ ነግሶ ወደነበረው ወደ ልጁ ወደ ሮብዓም ሕዝቡ መልዕክተኞችን ልከው እንዲህ  ብለው ተናገሩት፦ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን እኛም እንገዛልሃለን።ንጉሱም ለሕዝቡ የሰጠው ምላሽ እንዲህ ነበር፦አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፡፦አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር እኔ ግን በጊንጥ እገርፉችሁአለሁ

ይህም ጥበብ የጎደለው ድርጊቱ ለእሥራኤል መንግስት መከፉፈል ምክንያት ሆኖ አልፏል።

ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርስዎመልዕክት እንዲህ የሚል ነው፦አባትዎ መለስ ዜናዊ ቀንበር አክብደውብን ነበር አሁንም አርስዎ ጽኑውን የአባትዎን አገዛዝ በላያችንም የጫኑትን የከበደውን ቀንበር አቃልሉልን እኛም እንገዛልዎታለን።ታዲያ የእርስዎ መልስ ከፓርላማ  ንግግርዎና ከአሜሪካ ድምጽ ሬድዬ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ወስጀ ስመዝነው ቁርጥ የሮብዓምን ንግግር ሆነብኝ፧እንዲህ የሚል፦ አባቴ  መለስ ዜናዊ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፡፦አባቴ  መለስ ዜናዊ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር እኔ ግን በጊንጥ እገርፉችሁአለሁ።
    
ይህ ደግሞ ለሃገርም ለህዝብም አይበጅምና ያስተውሉ።እንደ ንጉስ ሰለሞን ለሃገርም ለህዝብም የበረከት ምክንያት ወይም እንደ ንጉስ ሮብዓም የመከፉፈል ምክንያት የመሆን ምርጫ እግዚአብሔር በፊትዎ አስቀምጧል፥መልካሙን እንዲመርጡ እግዚአብሔር ማስተዋል ይስጥዎት
ሕዝቡን ከአጥፊዎች ለመታደግ አስቦ አስቴርን በነገስታት ቤት ያስገባት እግዚአብሔር እርስዎንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመታደግ ወደ አራት ኪሎ አምጥቶዎታልና ያሰተውሉ፥ባይሆን ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ መዳን ከሌላ ሥፍራ ማዘጋጀቱ የማይቀር ነው።
በቀጣዩ ደብዳቤ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!!
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close