መለስ ዜናዊ ከጋዳፊ ውድቀት ቢማር….

By. Dagem Ahunem

ሊቢያን ለአርባ ሁለት ዓመታት ቀጥቅጠው የገዙት ኮሎኔል ጋዳፊ በትውልድ መንደራቸው ስርት ውስጥ እጎርፍ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ተገኙ። እንደተባለው ከሆነ ከወርቅ የተሠራ ሽጉጣቸውን የመጠጣት እድል እንኳን ሳያገኙ በአልባሌ ጥይት ቆሰሉ። “አይጦች፣ በረሮዎች፣ ሃሽሻሞች፣ ዱርየዎች” እያሉ በሰደቧቸው እና የመድፍ ናዳ ሲያወርዱባቸው በነበሩ ወጣት አብዮተኞች ጫማ ተረገጡ፣ ተጎሸሙ። በጥፊ ተመቱ፤ ተዋረዱ። በመኪናም ታስረው ተጎተቱ:: እየጮሁ በአሳዛኝና በአዋራጅ ሁኔታ ህይወታቸው አለፈ። … እጅግ አሳዛኝና አዋራጅ የሆነ አጨራረስ!!!

ጋዳፊ ስልጣንና ከስልጣን የሚገኝን ጥቅማ ጥቅም በዘመድ አዝማድ በማከፋፈላቸው በእሳቸው ላይ የተነሳውተቃውሞ ጦስም ለመላው ቤተ-ዘመዶቻቸው ደርሷል። በአሁኑ ሰዓት የቤተዘመዶቻቸው አባላት አንድም ተገድለዋል፤ አልያም ተሰደዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጋዳፊ አሟሟት እንዲመረመር በመፈለጋቸው የእስልምና ሃይማኖት በሚጠይቀው መሠረት በሞቱ ሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አልተቀበሩም። ይህም ለቀሪ ቤተሰቦቻቸው ሌላ ሞት ነው።

“ይወደኛል!!! ህይወቱንም ለኔ ሲል አሳልፎ ይሰጣል!!!” ያሉት ህዝብ ግን በጭፈራ ላይ ነው። የጋዳፊ አስከሬን በአልባሌ ምንጣፍ ላይ ተዘርሮ ለሥጋ ማቆያነት ይውል በነበረ የብረት ሣጥን (ኮንተይነር) ውስጥ ለቀናት ተቀምጦ ለእይታ በቅቶአል። በአገዛዝ ዘመናቸው በአካል ቀርበው ሊያዩዋቸው ያልበቁ ሁሉ አስከሬናቸውን በገዛ ዓይኖቻቸው ለማየት ወረፋ ይዘው ታይተዋል። ይህ ወረፋ የተያዘው በሌላ ሃገሮች እንደሚደረገው ለተከበሩ መሪዎች የመጨረሻውን ክብር ለመክፈል የተያዘ ወረፋ አይደለም። የጋዳፊን በውርደት የተሞላ አፈጻጸም ለመመልከት እንጂ። እንዲያውም የጋዳፊን አስከሬን በማየት ለመደሰት ሲሉ ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው የመጡ ሰዎችም ነበሩ ተብሏል። የሚስራታ ነዋሪዎች የጋዳፊን አስከሬን በማየት ቢደሰቱም በከተማቸው ውስጥ እንዲቀበሩ ግን አልፈቀዱም።

በሌላው ዓለምም ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው። ምናልባት ብዙዎች ጋዳፊ ህግ ፊት ቀርበው ቢያዩዋቸው ይመርጡ ነበር ይሆናል። ያም ሆኖ በመሞታቸው አልተከፉም። ዓለም ከተንሰራፉባት አምባነነኖች አንድ ቀንሶላታልና በጋዳፊ ሞት ተደስታለች።

የዛሬ አንድ ዓመት ሊቢያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ዛሬ ካለው ጋር ማስተያየት እንደምን ያለ ከባድ ነገር ነው!? የዛሬ ዓመት ጋዳፊ ሊቢያን ብቻ ሳይሆን መላውን አፍሪቃ እና መካከለኛውን ምሥራቅ የሚያርበደብዱ ብርቱ ሰው ነበሩ። የዛሬ ዓመት ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ እደጃቸው ነበር። ለስብሰባው አንዱ አገር ጎራ ሲሉ ዓይኖቻቸው እሳት የሚተፉ በሚመስሉ ሆኖም ግን ቆነጃጅት በሆኑ አጃቢዎቻቸው መሃል እንደ አንባሳ ደቦል ይንጎማለሉ ነበር። የዛሬ ዓመት እንኳንስ በአካል ፊት ለፊት፤ በቴሌቪዥን እንኳን ምስላቸውን ማየት የሚያስፈራ ነበር። የዛሬ ዓመትና ከዚያ በፊት በነበሩ አርባ ዓመታት ሁሉ የጋዳፊ ቃል የፈጣሪ ቃል ያህል ነበር።

ዛሬ ግን ያ ሁሉ ተቀይሯል። ጋዳፊ በተለይ በሊቢያውያን የተናቁ፣ የተዋረዱ፣ የተጠሉ ሰው መሆናቸው ተረጋግጦአል። በአርባ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ “ገነባሁት” ብለው ይኮሩባቸው ከነበሩ ነገሮች ውስጥ እሳቸውን ተከትሎ ለሚመጣው ትውልድ፣ ህዝብና መንግሥት የሚተላለፍ ነገር የለም። የገነቡት ሁሉ ፈርሷል። “አል ጀምሃሪያ” ወይም “የህዝብ አስተዳደር” ይሉት የነበረው የአገዛዝ መዋቅር ተንዷል። የጋዳፊው “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ” መጽሃፍ ማለትም “አረንጓዴው መጽሃፍ” በአደባባይ ተቃጥሏል። በውጭ አገራት በጥሬ ገንዘብና በኢንቬስትመንት መልክ ያስቀመጡት በ120 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል። ጋዳፊ ያወደሱት ሁሉ ረክሷል። ጋዳፊ የሰቀሉት ባንዲራ ወርዶ፤ በእሳት ተማግዷል።

ከአርባ ሁለት ዓመታት አገዛዝ በኋላ ሊቢያ እንደገና እንደ አዲስ ሃገር ነፃነቷን አውጃለች። ሊቢያውያን ገና ብዙ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል፤ ቢሆንም ግን የችግሮቻቸውን ሰንኮፍ ነቅለዋል። ለዚህም ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቢያዊያንን “እንኳን ደስ ያላችሁ!” ይላል።

መለስ ዜናዊ ከጋዳፊ ውድቀት ቢማር ለራሱም፣ ለቤተሰቦቹም፣ ለዘመዶቹም ምንኛ በበጀ! መለስ ዜናዊ ሆይ! በውሸትና በጉልበት የቆመ ሥርዓት እንዲህ በጥቂት ወራት ውስጥ ይደረመሳል። በውሸት እና በጉልበት የቆመ ሥርዓት ሲደረመስ ተጠርጎ ከሚጣል ፍርሽራሽ ውጭ ቀሪ ነገር አይኖረውም። ይህንን የምንለው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አይደለም፤ አንተም እኛም በዓይኖቻችን እያየነው ነው።

ግንቦት 7፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊቢያ ላይ እንደረሰው ዓይነት የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ሳይከፈል የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ያምናል። ለዚህ ግን የመለስ ዜናዊና ዘረኛ ቡድኑን ፈቃደኝነት ይጠይቃል። ስለሆነም በመለስ ዜናዊ ዙርያ ያላችሁ ሁሉ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ እንላለን። እብሪት የትም እንደማያደርስ ከጋዳፊ አይተነዋል።

በጋዳፊ ላይ የደረሰው ሁሉ ለመለስና ዘረኛ ቡድኑ ማስጠንቀቂያ ሊሆነው ይገባል። እኛ ነፃነታችንን እናከብራለን፤ እንወዳለን። እኛም እንደ ሊቢያውያን ለነፃነታችን የህይወት ዋጋ ጭምር ለመክፈል ዝግጁዎች ነን። ቆርጠናል፤ አምርረናል። መጨረሻችሁን ማሳመር ወይም ማበላሸት የእናንተ ምርጫ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close